የመድኀኒት መላመድ አደጋ

0
309

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ትርጓሜ መድኀኒቶች የሚባሉት ለህሙማን በሚስማማ መልኩ ተዘጋጅተው በሽታን ለመከላከል እና ለማከም የሚያገለግሉ በመርፌ፣ በእንክብል…የሚሰጡትን ነው:: መድሃኒት የተላመዱ በሽታ አምጪ ተሕዋሲያን በዓለም ላይ ካሉ 10 የከፉ የጤና ችግሮች አንዱ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል :: እ.ኤ.አ በ2021 ብቻ በዓለም ላይ ከ700  ሺህ በላይ ሰዎች መድኀኒት ሳይጨርሱ በማቋረጥ እና ከሀኪም ትዕዛዝ ውጪ  በመጠቀም  መድኀኒቱ ከበሽታው ጋር በመላመዱ  ህመሙ ተባብሶ ሕይወታቸው ማለፉን የቪኦኤ ዘገባ አመላክቷል::

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና ግብዓት አቅርቦት ዳይሬክቶሬት የፋርማሲ ሰርቪስ ኦፊሰር እና አንቲ ማክሮ ቫይራል ሪዚስታንስ ፎካል አቶ ጫኔ አድማሴ እምደሚሉት በዓለም ላይ 50 ከመቶ የሚሆኑ ህሙማን በጤና ባለሙያ የታዘዘላቸውን መድኀኒት በአግባብ አይጠቀሙም:: ችግሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥናት ባይሠራም በተቋማት የሚደረጉ ጥናቶች ይሄንኑ እውነታ ያረጋግጣሉ::

እንደ ዘርፉ ባለሙያ ማብራሪያ አጠቃላይ የመድኀኒት አጠቃቀም ችግር በሦስት መንገድ ይፈጠራል:: እነዚህም መድኀኒት የሚያዝዘው የጤና ባለሙያ  በትክክል ካላዘዘ፣  የፋርማሲ ባለሙያው (መድሃኒት የሚሰጠው) መድኀኒቱን መቼ፣ ከምን ጋር እና እንዴት  መውሰድ እንዳለበት ሙያዊ ምክር ካልሰጠ እንዲሁም  መድኀኒት የታዘዘለት አካል  የተባለውን ምክር በአግባቡ ሳይገነዘብ ሄዶ ከተባለው በላይ ወይም የተሻለው ሲመስለው አልያም ህመሙ ሲብስበት   ካቋረጠ መድኀኒት ለተላመደ በሽታ ይጋለጣል::

የመድኀኒት መለማመድ በሽታ የሚፈጥሩ  ፀረ ተህዋስያን  የሚባሉት በቫይረስ፣ በባክቴሪያ፣ በፈንገስ እና በፕሮቶዞዋ አማካኝነት የሚመጡ እንዲሁም  በሽታዎችን ለማከም የሚያገለግሉ መድኀኒቶች ናቸው::

የመጀመሪያው ፀረ  ተህዋስያን   መድኀኒት (ፔንስሊን) እ.ኤ.አ በ1929 ዓ.ም አካባቢ ተሰርቶ ጥቅም ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ድነዋል:: ይሁን እንጂ መድኀኒቶቹ አንድም አዳዲስ የፀረ  ተህዋስያን መድኀኒቶች ግኝት እ.ኤ.አ ከ1970ዎቹ ወዲህ በጣም በመቀነሱ አሊያም  የሰው ልጅ የተገኙ ፀረ ተህዋስያን መድኀኒቶችን በአግባቡ ተጠቅሞ ለሚከተለው ትውልድ ማስተላለፍ ባለመቻሉ ከጥቅም ውጪ እየሆኑ ነው:: በነዚህ ምክንያትም  ዓለም ወደ ቅደመ  ፀረ ተህዋስያን መድኀኒቶች ግኝት ዘመን እንዳትገባ ሥጋት እየፈጠረ መሆኑን ባለሙያው ይናገራሉ:: ይህ ክስተት እንደ ኢትዮጵያ ላሉና የበሽታ ስርጭቱ ከፍተኛ ለሆነባቸው ታዳጊ ሀገራት ትልቅ አደጋ መሆኑንም አስገንዝበዋል::

በሀገራችን ለተለያዩ በሽታዎች መንስኤ በመሆን ለበርካቶች ሕይወት ማለፍ ምክንያት የሚሆኑት በሽታዎች የሚፈጠሩት በማይክሮ ኦርጋኒዝም (ፈንገስ፣ ፓራሳይት፣ ቫይረስና ባክቴሪያዎች) አማካኝነት የሚከሰቱ ናቸው::

ለእነዚህ በሽታ አምጪ ተህዋስያን ማከሚያነት ለረጅም ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት ፀረ  ተህዋስያን መድኀኒቶች ዛሬ ከተህዋስያኑ ጋር በመላመዳቸው ህሙማንን ከበሽታ የመፈወስ አቅም አጥተዋል::  የፀረ ተህዋስያን መድኀኒቶች መላመድ በበሽታ አምጪ ተህዋሲያን አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎችን ለማከምም ሆነ ለመከላከል ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረው አንድ ፀረ ተህዋስ መድኀኒት በቀድሞው  ወይም ከዚያ በላይ በሆነ መጠን ተሰጥቶ ተዋህስያኑ የማይሞቱ ወይም መራባታቸው የማያቆም ከሆነ ተህዋስያኑ መድሃኒቱን ተላምደዋል ይባላል::  ሂደቱም የፀረ – ተህዋስያን መድኀኀኒቶች መላመድ (Antimicrobial Resistance) ተብሎ እንደሚጠራ ባለሙያው አብራርተዋል::

ፀረ ተህዋስያን መድኀኒት መላመድ ሲባል የመጀመሪያው ህሙማን የፀረ ተህዋስያን መድኀኒቶችን በሚወሰዱበት ወቅት በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኙትን በሽታ አምጪ ተህዋስያን ይገድሏቸዋል፤  አንዳንዶቹ ደግሞ እድገታቸውን ይገቷቸዋል::  በዚህ ወቅት በሽታ አምጪ ተህዋሲያኑ የመድኀኒቱን ኬሚካላዊ ባህርይ እንደሰው ያጠናሉ:: ከዚያ በኋላም መድኀኒቱን ለመቋቋምና ከጉዳት ለመዳን በሂደት መለወጥ ይጀምራሉ:: መድሃኒቱንም ይለምዱታል::  በዚህ ጊዜም መድሃኒቱ ጥቅም አልባ ይሆናል ማለት ነው:: ይህም በሽታዎች ከመድኀኒት ጋር የመላመድ ዘዴ (ሬዚስታንስ) እንደሚባል የዘርፉ ባለሙያ አረጋግጠዋል::

አቶ ጫኔ እንደሚሉት  በትክክል ተመርምሮ ምንነቱ ለተረጋገጠ በሽታ ትክክለኛው መድሃኒት በትክክለኛው ጊዜና መጠን መውሰድ  አግባባዊ የመድኀኒት አጠቃቀም መኖሩን ያመለክታል፤ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ የሚወሰድ መድኀኒት ግን አግባባዊ ያልሆነ ነው እንላለን:: ይህም የመድኀኒት መላመድን አስከትሎ ሕይወትን ለአደጋ ያጋልጣል:: ከዛ በተጨማሪ ሀኪም ሳያዝ  እንደፈለጉ እየገዙ መውሰድም ሌላው የችግሩ ምንጭ ነው::

“አንዳንድ ሰዎች በተለምዶ ቀላል ለሚሏቸው  ቶንሲል፣ ሆድ ቁርጠት፣ ራስ ምታት እና ጉንፋን ለመሳሰሉት በፈቃዳቸው መድኀኒቶችን ለራሳቸው አዘው ከየፋርማሲው እየገዙ ይጠቀማሉ:: መድኀኒቶቹ ህመማቸውን ካስታገሱላቸው በኋላ ተገቢውን መጠን ሳይወስዱ ያቋርጣሉ:: ይሄ ደግሞ መድኀኒት የተለማመደ ቫይረስ እንዲራባ በማድረግ ከፍተኛ የጤና ችግሮችን ያስከትላልና ከዚህ መቆጠብ ያስፈልጋል” ሲሉ ባለሙያው  አስገንዝበዋል::

አቶ ጫኔ እንደሚገልፁት መድኀኒት በተላመደ በሽታ የተያዘ ሰው ደግሞ ለመዳን ብዙ ወጭ እና ረጅም ጊዜ ስለሚወስዱ ለታማሚም ሆነ  ለአስታማሚም አስቸጋሪ ነው:: ይህም ታማሚው በህክምና ተቋማት  ረጅም ጊዜ ተኝቶ ስለሚታከም ከፍተኛ ወጭ እና የሰው ኀይል በመጠየቁ ነው:: ዋነው ችግር ግን ለማከም መድኀኒቱ ስለማይኖር ሞትን ያስከትላል፤ በሕፃናት ሲሆን ደግሞ ችግሩ የከፋ እንደሆነ ባለሙያው አስገንዝበዋል::

ይህንን ችግር ለመፍታት ፋርማሲስቶች ስለመድኀኒቱ ዝርዝር እና አወሳሰድ በቃል ከመንገር በተጨማሪ በጽሁፍ እንዲያስቀምጡ፣  በትላልቅ ሆስፒታሎችም ሆነ ጤና ኬላዎች በሳምንት ሁለት ቀናት ስለመድኀኒት አወሳሰድ እና በአግባቡ ሳይወሰዱ ሲቀሩ የሚያስከትሉት እስከ ሞት የሚያደርስ ጥቃት  ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ መጀመሩን  ባለሙያው ጠቁመዋል::

እንደ ሀገር ደግሞ ችግሩን ለመቀነስ  ስለአሳሳቢነቱ ለህብረተሰቡ እና  ለባለሙያ የግንዛቤ ፈጠራ መሠራት እንዳለበት፣ የሚመለከታቸው አካላት ደግሞ የመድኀኒት በሽታ መቋቋም መጠን መጨመሩን እና መቀነሱን በየጊዜው ጥናት እና ምርምር ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያው ጠቁመዋል::  ወደፊት ማህበረሰቡ መድኀኒት መጠቀም ያለበት  ተመርምሮ በሀኪም የታዘዘለትን እንጂ ከየቦታው ገዝቶ ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባው አሳስበዋል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here