የመድፈኞች አዲሱ የጨዋታ ስልት

0
46

በአዲሱ የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከየትኛውም ዓመት የተለየ ጠንካራ የዋንጫ ፉክክር ሊያስመለክተን እንደሚችል የክለቦች የተጫዋቾች ዝውውር እንቅስቃሴ ያመለክታል። ሊቨርፑል እና አርን ስሎት የአምና ክብራቸውን ለማስጠበቅ ለተጫዋቾች ዝውውር ከ300 ሚሊዬን ፓውንድ በላይ ወጪ አድርገዋል። የዝውውር እንቅስቃሴያቸው በእስከ አሁኑ ብቻ እንደማይቆም በአሌክሳንደር ኢሳቅ ጉዳይ የኒውካስልን በር በተደጋጋሚ ደጅ መጥናታቸው አመላካች ሆኗል።

የፔፕ ጓርዲዮላው ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ሊያስታውሱት ከማይፈልጉት ፈታኙ የአምና የውድድር ዘመን ወደ ዋንጫ ተፎካካሪነት ለመምጣት ቡድናቸውን አፍርሰው እንደ አዲስ እያዋቀሩ ይገኛሉ። ካሳለፍነው የውድድር ዘመን አጋማሽ እስከ ክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር ወቅት የፔፕ ክለብ ዘጠኝ አዳዲስ ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል።

በወጣት ባለተሰጥኦ ተጫዋቾች የተገነባው ቸልሲም የዓለም የክለቦች ዋንጫን ሳይገመት አሸንፏል። ከዚህ አስደናቂ ድል በኋላም ክለቡ የወደፊት ከዋክብቶችን ማሰባሰቡን መቀጠሉ የቀጣይ ዓመት ዕቅዱ በሁሉም የውድድር መድረክ መንገሥን ያለመ መሆኑን አመላክቷል። ያለፉትን ሦስት የውድድር ዘመን ጠንካራ የዋንጫ ተፎካካሪ የነበረው አርሰናልም በ2025/26 ወደ ሊግ ዋንጫ ድል የሚመልሰውን ውጤት ለማስመዝገብ እየታተረ ይገኛል።

ይህም ባልተለመደ መልኩ ያሳለፈው የዘንድሮው የክለቡ የክረምቱ የዝውውር ወቅት እንቅስቃሴ አመላካች ነው። በግብ ጠባቂ ቦታ ኬፓ አሪዛባላጋን የዴቪድ ራያ ተፎካካሪ ለማድረግ በማቀድ አስፈርሟል። የተከላካይ ክፍሉን ጥራት እና ጥልቀት ከፍ ለማድረግ ወጣቱን ክርስቲያን ሞስኩዌራን በእጃቸው አስገብተዋል። በለቀቋቸው ቶማስ ፓርቴይ እና ጆርጅኒዮ ምትክ ማርቲን ዙቢሜንዲ እና ክርስቲያን ኖርጋርድን የግላቸው አድርገዋል። የግብ ማስቆጠር ችግራቸውን ለመቅረፍ ደግሞ ኖኒ ማዱዌኬን እና ቪክቶር ጊዮኬሬሽን በከፍተኛ የዝውውር ገንዘብ አስፈርመዋል።
የመድፈኞቹ የዝውውር እንቅስቃሴ ግን በእነዚህ ተጫዋቾች ብቻ የሚቆም አይመስልም። የፈጠራ ችግራቸውን ለመቅረፍ ኤብሪቸ ኢዜን ለማዛወር ማቀዳቸውም በስፋት እየተወራ ነው። ይህ ደግሞ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ለሊግ ዋንጫ ክብር ተቃርበው ያልተሳካላቸውን መድፈኞቹን ለስኬት ያበቃል በሚል ታምኖበታል።

መድፈኞቹ ነባር እና አዳዲስ ያስፈርሟቸውን ከታችኛው ቡድን ካገኛቸው ተጫዋቾች ጋር በመቀላቀል ለአዲሱ የውድድር ዘመን ይረዳቸው ዘንድ ወደ ሩቅ ምሥራቅ ተጉዘው በሲንጋፖር፣ ሆንግ ኮንግ እንዲሁም በመቀመጫ ከተማቸው ለንደን ዝግጅት እና የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን አድርገዋል። በተደረጉ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችም አርሰናል በውድድር ዘመኑ በአጨዋወታቸው ላይ ለውጥ ለማድረግ ማሰባቸውን የሚያመላክቱ የጨዋታ አቀራረቦችን አስመልክተውናል። ቀጥተኛ አጨዋወት ስልት መተግበር አርሰናል በእስያ ባደረጋቸው የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ያሳየው አንዱ ለውጥ ነው።

ለዚህ ማሳያ ሆነው ከሚነሱ ምክንያቶች መካከል ቀዳሚው ረጃጅም ኳሶችን ደጋግመው መጠቀማቸው እና በጥቂት ንክኪዎች ወደ ግብ ለመድረስ መሞከራቸው ይገኝበታል። የዚህ ማሳያው ደግሞ ዴቪድ ራያ ረጃጅም ኳሶችን ለአጥቂዎች ለማሻገር መሞከሩ ይገኝበታል። በሌላ በኩል ደግሞ ኳስን ለረጅም ጊዜ ይዞ መቀባበልን በማስቀረት በፍጥነት የተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ ለመገኘት የሚደረጉ ጥረቶች ከፍ ብለው በአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ላይ ታይቷል። ወደ ግብ የሚደረጉ ሙከራዎች መጠንም ካለፉት ዓመታት በተለየ ከፍ ማለቱን በአርሰናል የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች የታየው ሌላኛው ለውጥ ነው።

መድፈኞቹ ከኤሲሚላን ጋር ባደረጉት ጨዋታ 23 የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል። በኒውካስል 15 እና በቶተንሃም ጨዋታ ደግሞ 16 የግብ ሙከራዎችን ማድረጋቸውን ዘ ቴሌግራፍ አስነብቧል። ይህ ደግሞ እ.አ.አ በ2024/25 የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ያነሳው ሊቨርፑል ካስቆጠራቸው ግቦች በ17 ያነሰ ግብ ላስቆጠረው አርሰናል ተጨማሪ የግብ ዕድል የሚያስገኝ የጨዋታ ምርጫ እንደሆነ ያሳያል።
ከአምናው የተለየ የማዕዘን ኳስ አጠቃቀም ምርጫም ሌላው በአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ወቅት የታየ የአርሰናል ለውጥ ነው። ባለፉት ዓመታት በማዕዘን ምት ወቅት በግብ ጠባቂዎች ዙሪያ መሰባሰብን የሚመርጡት መድፈኞቹ በእስያ ባሳለፉት ቆይታ አምስት ተጫዋቾቻቸው ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጭ በመሆን ኳሱ ሲሻማ ተወርውረው ወደ ውስጥ በመግባት ግብ ለማስቆጠር ሲሞክሩ ታይቷል። ይህ ደግሞ የቆሙ ኳሶች አሰልጣኝ ኒኮላስ ጆቨር በአዲሱ የውድድር ዘመን አዲስ ስልት ለመሞከር ማሰባቸው ማሳያ ነው።

አዲሱ መድፈኛ ቪክተር ጊዮኬሬሽ በአቋም መፈተሻ ጨዋታ በርካታ ደቂቃዎች ላይ ተሰልፎ መጫወት ባይችልም ኤምሬትስ መድረሱ አርሰናል በቀጣይ ዓመት የተለየ ሆኖ መቅረቡ እንደማይቀር መረጋገጫ ተደረጎ ይወሰዳል። ከዚህ በፊት ያለ ተፈጥሯዊ አጥቂ ሲቀርቡ ለነበሩት መድፈኞቹ ቪክተር ጊዮኬሬሽ በስፖርቲንግ ሊዝበን ሁለት ዓመታት ቆይታው ጨራሽ አጥቂ መሆኑን አሳይቷል። ታዲያ ሚኬል አርቴታም እሱን ተኮር ጨዋታ ለማድረግ ይገደዳል ተብሏል።

ውስን ደቂቃ ቢሆንም በቶተንሀሙ ጨዋታ ጊዮኬሬሽ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የማይጠፋ፤ ተከላካይን የሚፈትን ተክለ ሰውነት እንዳለው እና ኳስ ለማግኘት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ለአርሰናል አዲስ የአጨዋወት ለውጥ ማስተዋወቁን አይቀሬ ያደርገዋል። ከዚህ ባሻገር ከረጅም ጊዜ በኋላ ከጉዳት ነፃ ሆነው የተጫወቱት አስደናቂው የቤን ዋይት ፣ የማርቲን ኦዴጋርድ እና የቡካዮ ሳካ ጥምረት መመለሱ ወደ ግብ የሚሻገሩ የአየር ላይ ኳሶችን ለመጠቀም ዐይናፋር ለሆነው የአጥቂ ክፍል ሌላ ገፅታ ያላብሳል።

ከእስያ መልስ መድፈኞቹ ኤምሬትስ ላይ ከቪያሪያል እና አትሌቲክ ቢልባኦ ጋር ተጫውተዋል። በቪያሪያሉ ጨዋታ ሦስት ለሁለት ሲሸነፉ በእስያ ቆይታቸው የሞከሯቸውን አብዛኞቹን የጨዋታ ስልቶች ሞክረዋል። ወደ ራሱ የግብ ክልል ተጠግቶ የሚጫወት ክለብ ጋር ሲጫወት ግብ ለማስቆጠር የሚቸገረውን አርሰናልን በዚህ ጨዋታም ተመልክተነዋል።
የተከላካይ ክፍሉ ደግሞ ለመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ተጋላጭ መሆኑ አርቴታ ቀሪ የቤት ሥራ እንደሚጠብቀው አሳይቷል። በአትሌቲክ ቢልባኦው ጨዋታ ደግሞ አርቴታ በቀጣይ ቋሚ ተሰላፊ ተጫዋቾቻቸው የትኞቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጡበት ጭምር ነበር። በብዙ ተንታኞች ዕይታ በቅድመ ውድድር ዝግጅት አርሰናል ከሁለት ቦታዎች ውጭ ቋሚ ተሰላፊዎችን እና የውድድር ዘመኑን አሰላለፍ አሳይቷል የተባለበትን ጨዋታ ሦስት ለባዶ አሸንፏል። በጨዋታው አርቴታ ዴክላን ራይስን እና ማርቲን ዙቤሜንዲን በአማካኝ ተከላካይ ቦታ ላይ አጫውተዋል። ይህ ደግሞ የአማካይ ክፍሉ ላይ ብልጫ እንዲወስዱ አስችሏቸዋል።

ቪክተር ጊዮኬሬሽን ደግሞ ቋሚ አድርገው አሰልፈው ከተጫዋቹ ግብ አግኝተዋል።
አርሰናል በመጀመሪያው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ወደ ኦልትራፎርድ ተጉዞ አንድ ለባዶ ባሸነፈበት ጨዋታ   የአርቴታ ቡድን ከማራኪ  አጨዋወት  ይልቅ አሸናፊ የሚያደርገውን የጨዋታ ስልት አሳይቷል።
ምንም እንኳ ሙሉ በሙሉ የጨዋታ ስልቱ ባይቀየርም የነበረው ስልት ይበልጥ የበሰለ፣ የተጠና እና ለተለያዩ የጨዋታ አቀራረቦች ምላሽ መስጠት የሚችል ሆኖ የቀረበበት እንደሆነ ተመልክተናል። መድፈኞቹ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያጡትን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ራሳቸውን ከፍ ባለ ደረጃ አጠናክረው ከቀረቡት ክለቦች ጋር ተፋልመው ዋንጫውን ያነሳሉ? ትልቁ ጥያቄ ነው።

(ኃይሉ አዳነ)

በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here