የመጀመሪያዉ ጥቁር ፕሮፌሽናል ተጫዋች

0
19

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ እግር ኳስ  በእንግሊዝ እያደገ እና ተወዳጅነትን እያገኘ በነበረበት ወቅት አንድ ስሙ በታሪክ ገጽ  በደማቁ የተጻፈ አፍሪካዊ ኮከብ ብቅ አለ::ይህ ኮከብ አርተር ዋርተን ይባላል::በወቅቱ የነበረውን ጽንፍ የረገጠ ዘረኝነት በመጣስ በእንግሊዝ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ሊግ የተጫወተ የመጀመሪያው ጥቁር ተጫዋች በመሆን አዲስ ታሪክ ጽፏል::

አርተር ዋርተን እ.ኤ.አ በ1865  የብሪታንያ ቅኝ ግዛት በነበረችው ጋና አክራ ከተማ ውስጥ ተወለደ::አባቱ ሄንሪ ዋርተን ከግሪናዳ የመጣ ሚስዮናዊ ሲሆን እናቱ ደግሞ አና ፍሎረንስ የጋና ንጉሣዊ ቤተሰብ ልጅ ነች::ይህም ዋርተን ከልጅነቱ ጀምሮ የተሻለ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ አስችሎታል::እናም በ12 ዓመቱ ለትምህርት ወደ ለንደን እንዳቀና የታሪክ ማህደሩን ጠቅሶ ጎል ዶት ኮም አስነብቧል::በእንግሊዝ ቆይታውም  በተለይም በእግር ኳስ እና አትሌቲክስ ስፖርቶች በመማረክ ከስፖርት ጋር ተዋውቋል፡፡ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ በሩጫ እና በዝላይ ልዩ ተሰጥኦ እንዳለው ማሳየት ጀመረ።

ዋርተን በመጀመሪያ ትኩረቱን በአትሌቲክስ ላይ ነበር ያደረገው ::በ1886 እ.አ.አ በስታምፎርድ ብሪጅ በተካሄደው የአማተር አትሌቲክስ ማህበር ሻምፒዮና ላይ የ100 ሜትር ሩጫን በዐስር ሴኮንድ በመጨረስ በወቅቱ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር አሸናፊ ሆነ::ይህ ስኬቱ በመላው እንግሊዝ ስሙ እንዲታወቅ እና “የዳርክሊንግተኑ በራሪ” የሚል ቅጽል ስም እንዲያገኝ አስችሎታል::ምንም እንኳን በአትሌቲክስ ስኬታማ ቢሆንም የዋርተን ልብ ግን ወደ እግር ኳስ ያዘነብል ነበር::እናም እ.አ.አ በ1885 ለዳርሊንግተን ክለብ በመፈረም የእግር ኳስ ሕይወቱን በይፋ ጀመረ::በመስመር ተጫዋችነት ቢጀምርም ብዙም ሳይቆይ በግብ ጠባቂነት ቦታ ላይ ያለውን ልዩ ችሎታ አሳየ።

ዋርተን በዘመኑ ከነበሩት ግብ ጠባቂዎች የተሻለ እና የተለየ ነበር::ኳስን በእግሩ ከመምታት ይልቅ በእጁ በመወርወር ለቡድን አጋሮቹ በማድረስ ይታወቅም ነበር::እንዲሁም ወደፊት የመውጣት እና ተቃራኒ ተጫዋቾችን የማስደንገጥ ልምዱ ተመልካቾችን ያስደምም  እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል::በዳርሊንግተን ክለብ ውስጥ ባሳየው ድንቅ ብቃትም የበርካታ ታላልቅ  የእንግሊዝ ክለቦችን ቀልብ መሳብ ጀመረ::በ1886 እ.አ.አ ወደ ፕሬስተን ኖርዝ ኤንድ ክለብ ተዘዋወረ::በወቅቱ ፕሬስተን ኖርዝ ኤንድ በእንግሊዝ ውስጥ ካሉ ምርጥ ክለቦች አንዱ ነበር::ዋርተን ለዚህ ክለብ በመጫወት በኤፍኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ላይ መሳተፍ ችሏል::ይህም በታሪክ በኤፍኤ ካፕ ግማሽ ፍጻሜ ላይ የተሳተፈ የመጀመሪያው ጥቁር ተጫዋች ሆኖ ስሙ ተመዝግቧል።

በ1889 እ.አ.አ ዋርተን ሕጋዊ የተጫዋቾች ውል በመፈረም የመጀመሪያው ጥቁር ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ሆነ::ይህ ክስተት በእንግሊዝ እግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በነጮች ምድር የቆዳ ቀለማቸው ጥቁር ለሆኑ ሰዎች ቦታ የማይሰጥ የነበረ በመሆኑ ለበርካታ ጥቁር ተጫዋቾች በር ከፍቷል::ግብ ጠባቂው ከዚያ በኋላ ሮተርዳም ታውን፣ ሼፊልድ ዩናይትድ እና ስቶክፖርት ካውንቲን ጨምሮ ለተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል።

በሼፊልድ ዩናይትድ ቆይታው ቡድኑ ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል::ይሁን እንጂ ሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ ከባድ የዘረኝነት ጥቃቶች ይደርስበት እንደነበር ሜል ስፖርት ያስነብባል::ነገሮችን ከባድ እና ውስብስብ የሚያደርጋቸው ደግሞ በተገቢው መንገድ የራሱ ቡድን ተጫዋቾች አለመተባበራቸው  እንደሆነ  መረጃው  ያስነብባል፡፡ የዋርተን ታሪክ የእግር ኳስ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የጥንካሬ፣ የጽናት እና የትግል ተምሳሌት መሆኑን ጎል ዶት ኮም ያስነብባል።

ከንጉሣውያን ቤተሰብ የተገኘው ዋርተን በ1902 እ.እ.አ ከእግር ኳስ ከተገለለ በኋላ አስቸጋሪ ህይወትን ለመምራት ተገደደ::ኑሮውን ለማሸነፍ በከሰል ማዕድን ማውጫ ውስጥ በሰራተኝነት ተቀጥሮ ይሠራ እንደነበር ተነግሯል::

በ1930 እ.አ.አ በ65 ዓመቱ አርተር ዋርተን በኤድሊንግተን ዮርክሻየር ውስጥ በድህነት ሕይወቱን ከመራ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ::የተቀበረውም ማንም በማያውቀው መቃብር ውስጥ ነበር::ለረጅም ዓመታትም የእርሱ ታሪክ ተረስቶ መቆየቱን መረጃዎች አመልክተዋል።

ምንም እንኳን በሕይወት ዘመኑ የሚገባውን ክብር ባያገኝም ከጊዜ በኋላ ጀግንነቱ መወራት ጀመረ::በ1997 “ፉትቦል አንብሎክድ” የተባለ የፀረ-ዘረኝነት ድርጅት የዋርተንን  መቃብር ለማግኘት ዘመቻ ጀመረ::በመጨረሻም መቃብሩ ተገኝቶ የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምለት ተደርጓል::

ለዚህ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጫዋች የተለያዩ የእግር ኳስ ተቋማት ዕውቅና ሰጥተውታል፡፡ በ2003 እ.አ.አ በእንግሊዝ እግር ኳስ የክብር መዝገብ (English Football Hall of Fame) ውስጥ ስሙ ተካቷል::እ.አ.አ በ2014 ደግሞ በእንግሊዝ  እግር ኳስ ሙዚየም ቅጥር ግቢ ውስጥ የነሐስ ሐውልት ቆሞለታል::

ዛሬ ላይ የአርተር ዋርተን ታሪክ በእንግሊዝ ውስጥ ላሉ ጥቁር ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን በአራቱም የዓለም ማዕዘን ለሚገኙ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ወጣቶች መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡ ዋርተን  ምንም  እንኳን በሕይወት ዘመኑ ብዙ መከራዎችን ቢያሳልፍም ስሙ በታሪክ መዝገብ በክብር ተቀምጧል::አርተር ዋርተን የአፍሪካውያን ፈር ቀዳጁ የቀድሞ ተጫዋች የእግር ኳሱ ጀግና እና የትግል ተምሳሌት ሆኖ  ይታወሳል፡፡ እኛም የጥቁር ሕዝቦች መታሰቢያ በሆነው በዚህ ወርሀ ጥቅምት እንዲህ አስታውሰነዋል፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here