የመጓጓዣዉ ነገር

0
231

የመጓጓዣ አገልግሎት ማግኘት የከተማችን ሕዝብ የወቅቱ ፈተና ኾኗል:: እስኪ የአንድ ዕለት ገጠመኘን እንደ አብነት ላንሳ ፤ የምሰራበት መሥሪያ ቤት በሰዓቱ ደርሼ የማከናውነውን የዕለት ተግባሬን እያሰላሰልሁ ታክሲ መሳፈሪያ ቦታ የደረስሁት ከጧቱ 1፡30 ነበር፤ ሐሙስ መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓመተ ምሕረት:: ነገር ግን በቦታዉ ታክሲ አልነበረም:: ባንጻሩም ታክሲ የሚጠብቀው ሕዝብ ረዥም ሰልፍ ሠርቶ ይታያል::

ቀደም ባሉት ወራት በዚህ ሰዓት በየታክሲ ፌርማታው ተሰልፎ የሚታየው ተሳፋሪ የሚጠብቅ ታክሲ ነበር:: እናም ተሳፋሪው እንደ ደረሰ በተረኛዉ ታክሲ ተሳፍሮ ወደ ፈለገው ቦታ ይሄድ እንደነበር እናስታውሳለን:: ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ታክሲዎች እየጠፉ ተጓዡ ተሰልፎ መንገድ መንገዱን ማየት ግዴታ ሆኖበታል:: እናም በዕለተ ሐሙስ  በታክሲ ፌርማታው ላይ በታክሲ ፋንታ ተሳፋሪው ረዥም ሰልፍ ሠርቶ ስመለከት ብዙም አልተገረምሁም:: ከኋላየ የቆመች ወረፋ ጠባቂ ወጣት ግን ለክስተቱ አዲስ ትመስላለች፤ “ምንድነው ይሄ ሁሉ ሰልፍ?!” ስትል ጠየቀችኝ::

“እዚህ ፌርማታ ስትሰለፊ ዛሬ የመጀመሪያሽ ነው?” ስል ጥያቄዋን በጥያቄ መለስሁላት::

“እኔ ሁሌም ወደ ሥራ የምገባው ከአራት ሰዓት በኋላ ስለሆነ እዚህ ፌርማታ ይህን ያህል ሰልፍ ገጥሞኝ አያውቅም:: ባይሆን ታክሲ እያጣሁ የምቸገረው ማታ ከሥራ ወደ ቤቴ ስመለስ ነው” ስትል መለሰችልኝ::’

“ኧረ እኛስ ተሰልፎ መዋሉ የዕለት ከዕለት ግዴታችን ከመኾኑ የተነሳ እየለመድነው ነው” በማለት መለስሁላት::

እሷም፣ “እንዲህ ዓይነቱ ነገር ደግሞ ምኑ ይለመዳል ብለህ ነው!” አለች፤ ከፊቷ ቅሬታ እየተነበበ:: ከዚያም ወደ ኋላ ዞራ እየተመለከተች፣ “ ከምኔው ነው ይሄ ሁሉ ሰው ከኋላችን የተሰለፈው? ደግሞ ሰልፉ ንቅንቅ አይልም፤ እስካሁን እኮ ከቆምንበት አልተነቃነቅንም” አለችና ሰዓት ጠየቀችኝ::

“ ለሁለት ሀያ አምስት ጉዳይ” አልኋትና ሰልፉን ዞሬ ተመለከትሁ:: ባምስት ደቂቃ ውስጥ ከኋላችን መጨረሻው የማይታወቅ ሰልፍ ተፈጥሯል::

ወጣቷ ችኩል ብላለች:: ወደ ፊት እንደመንጠራራት እያለች፣ “ለመሆኑ ከፊት ያለው ሰልፍ መጀመሪያ ይታወቃል?” ስትል ጥያቄዋን አስከተለች:: ከኋላዋ የተሰለፈው ጎልማሳ ፈጠን ብሎ፣ “ምናልባት አንድ ሦስት ታክሲዎች ተከታትለው ቢመጡ ይታየን ይሆናል:: አልያ እዚሁ እንደቆምን መጀመሪያው እንደናፈቀን ሳናየው መቅረታችን ነው” የሚል ምላሽ ሰጣት::

ወዲያው አንዲት ታክሲ መጥታ ወደ ሰልፉ መጀመሪያ ስትታጠፍ የሁላችንም ትኩረት እሷ ላይ ሆነ::  ሰልፉ ትንሽ እንደመንቀሳቀስ ብሎ ቆመ::

ለአርባ ደቂቃ ያህል ቆምን:: ሁለት ሰዓት ከአሥር አካባቢ ሁለት ታክሲዎች ተከታትለው መጡ:: ሰልፉ ቀለል አለ፤ የቀደሙት ሰልፈኞች ያሉበት ቦታም ታወቀ:: ወጣቷ ከሰልፏ ወጣ ብላ ፊት ለፊት ስትመለከት ቆየችና ወደ ሰልፉ ተምልሳ፣ “አራት ታክሲ ቢመጣ ወረፋው ይደርሰናል”  አለች::

“አይደርሰንም!” ጎልማሳው የወጣቷን ሀሳብ አጣጣለ::

“ ሦስት ታክሲ ቢመጣ ይደርሰናል” አልሁ::

“ቆጥሬዋለሁ! ስልሳ ሰው ነው የተሰለፈው፤ አራት ታክሲ ካልመጣ አይደርሰንም…” አለች::

ታክሲ በሌለበት ይደርሰናል፤ አይደርሰንም በሚል ክርክሩን አጧጧፍነው:: በዚህ መሀል አንዲት ታክሲ እንዲሁም ሀይሩፍ ተከታትለው መጥተው ቀልባችንን ባይስቡት ኖሮ ክርክራችን በቀላሉ የሚቆም አይመስልም ነበር:: ሁለቱ ተሽከርካሪዎች ተከታትለው እንደመጡ ከፊት ያለው ሰልፍ አጠር አለ:: የኋላው  ሰልፍ ግን እንደ ዓባይ ወንዝ እንደተዘረጋ ነበር:: ይህን  ስመለከት ሕዝቡ በታክሲ እጥረት እንዲህ እየተጉላላ ባለበት ወቅት ሌሎች ተሸከርካሪዎችም ከታክሲዎች ጋር ተሰማርተው ሕዝብን የማጓጓዝ አገልግሎት ይሰጡ ዘንድ የፈቀዱ የስምሪት አካላትን  አመሰገንኋቸው::

የስምሪት አካላቱን በልቤ እያመሰገንሁ ባለሁበት ቅጽበት ጎልማሳው፣ “ሕዝቡ እንደዚህ ከሚጉላላ ከተማ አስተዳደሩ ለሕዝቡ የመጓጓዣ አገልግሎት የሚሰጡ የከተማ አውቶቡሶችን ለምን አይመድብም?” ሲል ሀሳብ አቀረበ:: በዚህ መሀል አንድ ታክሲ እንዲሁም አንድ ኮስትር  ፊት እና ኋላ ኾነው መጡ:: ታክሲዋ በኩርሲውም፣ ባግዳሚውም ሳይቀር ጭና ሄደች:: ወጣቷ እና እኔም ከፊት ስለነበርን ቀድመን ከኮስትሩ ገብተን ከሾፌሩ ጎን ተቀመጥን::  ኮስትሩም እንደ ታክሲው ሰው በሰው ላይ አነባብሮ አሳፍሮ ጉዞ ቀጠለ::

ስድስት ደቂቃ ያህል እንደተጓዝን አንድ ትራፊክ ፖሊስ ቀድማን የሄደችውን ታክሲ ሾፌር ትርፍ ጭነሀል በሚል አስቁሞ የቅጣት ወረቀት ጽፎ ሲሰጠው ተመለከትን:: የኮስትሩ ሾፌር በሁኔታው ብስጭት ብሎ፣ “ሰው በትራንስፖርት ችግር ለሰዓታት ቆሞ ለመጠበቅ እየተገደደ ይሄ ደግሞ ትርፍ ጫንህ ብሎ ይቀጣል?!” ሲል የትራፊክ ፖሊሱን ድርጊት ነቀፈ::

ወጣቷም፣  “ሕጉ እንዲከበር ከተፈለገ መጀመሪያ መንግሥት የነዳጀ አቅርቦት ችግሩን መፍታት አለበት፤ ቅጣት ብቻውን  መፍትሄ አይሆንም ” በማለት የሾፌሩን ሀሳብ አጠናከረች::

ሾፌሩም፣ “እነሱ እኛን አይነኩንም እንጂ ታክሲዎችን አሳድደው ነው የሚቀጧቸው፤ ታክሲዎች ደግሞ ነዳጅ በብላክ ገዝተው ሕግ እናክብር ቢሉ ስለማያዋጣቸው ከተፈቀደላቸው በላይ መጫናቸውን አይተውም” በማለት በየዕለቱ የሚያጋጥመንን ክስተት እንደ አዲስ ተረከልን::

የሾፌሩ ሀሳብ ሕዝቡ በመጓጓዣ እጥረት እንዲህ እየተጉላላ ባለበት ወቅት የታክሲ ሾፌሮች ከተፈቀደላቸውው በላይ ማሳፈራቸው ጥፋት ሆኖ ሊያስቀጣቸው አይገባም የሚል ነው:: ሀሳቡ በከፊል ቅቡልነት አለው:: ሕግ የሚወጣው ሕዝብን ለማገልገል እንደመሆኑ መጠን ሕዝብ ስንት ጉዳዩን ትቶ ተሰልፎ ሲጠብቅ ውሎ ባገኘው ታክሲ እንደምንም ብየ እሄዳለሁ ብሎ በመግባቱ፣ ባለታክሲው ከኪሳራ ለመዳን ብሎ ከተፈቀደለት ሰው በላይ በማሳፈሩ ሕግ ተላልፈሀል በሚል የሚወሰድበት የቅጣት ርምጃ ከችግሩ አንጻር በእርግጥም አስተማሪ ላይሆን ይችላል:: ስለሆነም ሕግ ተላልፈሀል ብሎ ከመቅጣት ባሻገር የታክሲ እጥረቱን የፈጠረውን እና ታክሲዎችም ትርፍ ለመጫን የተገደዱበትን ችግር ከስሩ መርምሮ መፍታቱ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ በማውሳት ብዙ ተወያየን:: እንዲህ እየተወያየንም ከፌርማታው መጨረሻ ደርሰን ኖሮ ረዳቱ፣ ”መጨረሻ! ” ሲለን ወረድን::

ሆኖም መሥሪያ ቤቴ ለመሄድ ሁለተኛ ታክሲ መያዝ ስለነበረብኝ ወደ ሁለተኛው ፌርማታ አመራሁ:: ሁለተኛው ፌርማታ ላይ የባሰ ነገር ገጠመኝ:: ሕዝቡ ተሰልፎ ወረፋ በመጠበቅ ፋንታ አካባቢውን ሞልቶ ታክሲ ባየ ቁጥር በጅምላ ይሮጥና ከታክሲው በር ላይ ሲደርስ ርስ በርሱ ይጋፋል:: ከብርቱ ትግል በኋላም ጉልበት ያለው ሲገባ ሌላው  ሌላ ታክሲ ያማትራል::

ታክሲ በመጣ ቁጥር እየተሯሯጥን የታክሲውን በር አንቀን ስንተራመስ ቆይተን በብዙ ትግል ገባንና ጉዞ ተጀመረ:: ይሁን እንጂ፣ ብዙም ሳንሄድ ትራፊክ ፖሊስ አስቆመንና “ስምንት ሰው ትርፍ ጭነሀል” በማለት መንጃ ፈቃዱን ተቀበለው:: እዚህም እንደ መጀመሪያው ታክሲ ሁሉ ተሳፋሪው፣ “ሰው ታክሲ አጥቶ እየተተራመሰ እንዴት ትርፍ ጫንህ ብሎ አስቁሞ ይህን ያህል ያጉላላናል?!” በማለት ፖሊሱን ይተች ጀመር::

ሌላው ተሳፋሪም፣ “የታክሲ እጥረት በሌለበት ጊዜ ትርፍ ጭነው እንደፈለጋቸው ሲሄዱ ዞር ብለው የማያዩ በዚህ የችግር ወቅት ለቅጣት ይጣደፋሉ” ሲል የፖሊሱን ሕግ የማስከበር ርምጃ ኮነነ::

እንዳይደረስ የለም ከቤቴ አንድ ሰዓት ከሀያ አካባቢ የወጣሁ ሁለቱን ሰዓት ታክሲ በመጠበቅ እና በጉዞ አሳልፌ ሦስት ሰዓት ከሀያ ቢሮ ደረስሁ::

ማታ አሥራ አንድ ሰዓት ተኩል ከቢሮ ወጣሁ፤ ወደ ቤቴ ለመሄድ:: እውነት ለመናገር መጀመሪያው ፌርማታ ላይ ረዥም ሰልፍ አላጋጠመኝም:: በአሥር ደቂቃ  ውስጥ ወረፋ ደርሶኝ  ተሳፍሬ ወደ ሁለተኛው ፌርማታ አመራሁ::

ሁለተኛው ፌርማታ ላይ ጧት መጀመሪያው ፌርማታ ላይ ካጋጠመኝ የሚልቅ እጅግ ረዥም ሰልፍ ጠበቀኝ:: ሰልፉን ሳስተውል ቆይቼ ሰዓቴን ተመለከትሁ:: አሥራ አንድ ሰዓት ከሀምሳ ደቂቃ ይላል:: ግራ እንደተጋባሁ ቆሜ መጀመሪያውም ሆነ መጨረሻው የማይታየውን ሰልፍ በድጋሜ እቃኝ ጀመር:: ያልተሰለፈው ሕዝብ አስፋልቱን ሞልቶ ይተራመሳል:: የባጃጅ ሾፌሮች ባጃጆቻቸውን አሰልፈው ላሥሩ ብር መንገድ ሀምሳ ብር እያስከፈሉ አራት አራት ሰው እያሳፈሩ ይሄዳሉ:: እኔም ሀምሳ ብር በመክፈል ለመሄድ ወሰንሁና  አጠገቤ ወደ ነበረች ባጃጅ አመራሁ::

የዕለት ከዕለት ውሏችን የሐሙስን ውሎ ይመስላል:: ትናንትን፣ ከትናንት ወዲያን፣ ከዚያ ወዲያን… ብናወሳ እያንዳንዱን ዕለት ያሳለፍነው በዚህ መልኩ ሆኖ እናገኘዋለን:: ይህ እውነታ መቀየር ይኖርበታል:: ሀገር የምትለወጠው በልጆቿ የተባበረ ጥረት ነው:: የመንግሥት ሠራተኛው በሰዓቱ በሥራ ገበታው ተገኝቶ የሚጠበቅበትን ተግባር ሲያከናውን፣ ኃላፊነቱን ሲወጣ ሀገር አንድ ርምጃ ወደ ፊት ትሄዳለች:: ተማሪው በሰዓቱ ትምህርት ቤት ተገኝቶ ትምህርቱን ሲማር፣ መምህሩ ሲያስተምር የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ መሠረት ይጣላል:: ሀኪሙ በጊዜ ገብቶ ህሙማኑን ሲያክም የግለሰብ፣ የማኅበረሰብ፣ የሀገር ጤና ይጠበቃል:: ነጋዴው በጊዜ ሱቁን ከፍቶ ሸማቹ የሚፈልገውን ምርት ሲያቀርብ ሕይዎት ትቀጥላለች:: ሌላው ወገንም እንደየተሰማራበት የሥራ መስክ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ሲሰጥ በድምር ውጤቱ ሀገር በዕድገት እና በሥልጣኔ ጎዳና ወደ ፊት ትገሰግሳለች::

ይህን ሁሉ አደራም እንበለው ኃላፊነት የተሸከመ ሕዝብ ይህን ሁሉ አደራም ኾነ ኃላፊነት የሚወጣበትን ወርቃማ ጊዜውን በመጓጓዣ እጦት በየመንገዱ ዳር ቆሞ ሲያሳልፍ ግን ገጣሚው፣

ሀገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ

ነገራችን ሁሉ የእምቧይ ካብ የእምቧይ ካብ

እንዳለው ነገራችን ሁሉ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ከመሆን አይድንም::

ስለሆነም የመጓጓዣ እጥረቱ የተፈጠረበትን መሠረታዊ ምክንያት ለይቶ የአጭርም ሆነ የረዥም ጊዜ መፍትሄ  መስጠት ግድ ይላል:: ካጭር ጊዜ መፍትሄ አኳያ ጎልማሳው እንዳለው ከተማ አስተዳደሩ ለሕዝቡ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት የሚሰጡ የከተማ አውቶቡሶችን ቢመድብ ችግሩን ማቃለል ይቻላል::

የታክሲዎች የስምሪት ጉዳይም ሊስተካከል ይገባል:: በተደጋጋሚ እንደታዘብነው ታክሲዎች የተሰጣቸውን ስምሪት ወይም መስመር እንደፈለጉ ሲቀያይሩ ይስተዋላሉ:: በዚህ የተነሳም በተለይም በሕዝባዊ የበዓል ቀናት ባንዳንድ ፌርማታዎች ታክሲዎች ሲጠፉና ሕዝቡ በመጓጓዣ እጦት ሲጉላላ ይታያል:: ስለዚህ ተቆጣጣሪዎች ስምሪታቸውን እንደፈለጉ በሚቀይሩ ታክሲዎች ላይ ተገቢውን የእርምት ርምጃ መውሰድ እና ስምሪቱን ማስተካከል ለችግሩ መቃለል በእጅጉ ይረዳል::

መሠረታዊው የችግሩ ምንጭ የነዳጅ እጥረቱ እንደሆነ እናምናለን:: ሕዝቡ ረዣዥም ሰልፍ ሠርቶ ታክሲ ሲጠብቅ፣ ታክሲዎች ደግሞ ነዳጅ ለመቅዳት ሀገር አቋራጭ ሰልፍ ሠርተው ውለው ያመሻሉ:: ተሰልፈው ውለው አምሽተው ካሁን አሁን ደረሰን ሲሉ መብራት ይጠፋና መብራት የለም ተብለው የሠሩትን ሰልፍ ያፈርሳሉ:: በዚህ የተነሳም አገልጋይ እና ተገልጋይ ሳይገናኙ ይቀራሉ፤ ችግሩ እየተባባሰ ይሄዳል:: ችግሩ ዘላቂ እልባት ካልተሰጠው መጪው ጊዜ የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም:: ስለሆነም እጥረቱ ለምን ተፈጠረ? ነዳጅ ከቦታ ቦታ ማጓጓዝ ስላልተቻለ? ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይት ስለተስፋፋ?… የችግሩን መሠረታዊ ምክንያት መርምሮ በዘላቂነት መፍታት ያሻል::

(ቦረቦር ዘዳርአገር)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here