በዛሬው ሽርሽራችን የውጪ ሀገር ጎብኝዎቿ ከዜጎቿ ቁጥር የሚበልጥባትን አፍሪካዊት ውብ ሀገር እናስጎብኛችሁ፡፡ የአሜሪካ ሴንትራል ኢንተለጀንስ (ሲ አይ ኤ) ፋክት ቼክ ያወጣው መረጃ እ.አ.አ በ2024 የዜጎቿ ቁጥር 98 ሺህ ገደማ ነበር፤ በዓመት ግን ከ300 ሺህ በላይ የውጪ ሀገር ዜጎች ይጎበኟታል፡፡ አፍዝ አደንግዝ ያላት፣ በውበቷ ማራኪ እንደሆነች የሀገሪቱ ዜጎችም ሆነ የጎበኟት የውጪ ሀገራት ዜጎች ይናገራሉ፡፡ ይህች በውበት የታደለች ሀገር አፍሪካ ውስጥ መሆኗ ደግሞ ብዙዎችን ያስገርማል፤ ሀገሪቷ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሲሸልስ ናት፡፡
ስለሲሸልስ የተለያዩ አድናቆቶች እና ሙገሳዎች ይሰማሉ፤ አንድ ዜጋዋ ግን የሚከተለውን ብሏል፡- “ሁሌም መሽቶ ሲነጋ እንደ አዲስ እደነቃለሁ፤ በዚህች ውብ ደሴት ላይ እንድነቃ ተጨማሪ እድል ስለሰጠኝ ፈጣሪየን አመሰግናለሁ፡፡ በእንደዚህ አይነት ሰላማዊ እና ውብ አካባቢ ውስጥ የሚኖሩ ደስተኛ ሕዝቦች ቁጥር በዓለማችን ዝቅተኛ ነው፤ ከጥቂቶች መሃል ስላደረገኝ ፈጣሪ ይመስገን፡፡”
ሲሸልስ ደሴት ናት፤ ከኬንያ የባሕር ጠረፍ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር፣ ከማዳጋስካር ደግሞ አንድ ሺህ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ሞሪሺየስ እና ኮሞሮስ የሚያዋስኗት ደሴት ሀገሮች ናቸው፡፡ በውስጧ 115 ደሴቶች አሏት፡፡ የሲሸልስ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ሲሆን የነብስ ወከፍ ገቢዋም 21 ሺህ ዶላር መሆኑን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) መረጃ ያሳያል፡፡ ዓለም አቀፉ የጸረ ሙስና ድርጅት ‘ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል’ በያዝነው ዓመት ይፋ ባደረገው የሀገራት የሙስና ይዞታ ዓመታዊ ሪፖርቱ እንዳመለከተው፡ 72 ነጥብ ያስመዘገበችው ሲሼልስ ከአፍሪካ ሀገራት በሙሉ ዝቅተኛ ሙስና ያለባት ናት፣ በፕሬስ ነጻነትም አንደኛ ናት፡፡
በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ አውሮፓውያን ደሴቶቹን ከማግኘታቸው በፊት ሲሼልስ ሰው አልነበረባትም። በኋላ ፈረንሳዮች ያዟት፤ ከብዙ ትግል በኋላ ፈረንሳይ በ1814 እ.አ.አ ደሴቶቹን ለታላቋ ብሪታኒያ አሳልፋ ሰጠች። ሲሸልስ ከታላቋ ብሪታንያ ጋር በተደረገ ድርድር በ1976 እ.አ.አ ነፃነቷን አገኘች።
ወደ ሲሸልስ ለመግባት ቪዛ አይጠየቁም፡፡ ጎብኚዎች ያለ ቪዛ ገብተው መጎብኘት እንዲችሉ ትፈቅዳለች፡፡ ሲሸልስን ለመጎብኘት የሚያስፈልግዎ ሕጋዊ ፓስፖርት መያዝ፣ የደርሶ መልስ ትኬት መቁረጥ እና ማረፊያ ሆቴል መከራየት እንዲሁም ቢያንስ ለአንድ ቀን ወጪ የሚሆን 150 ዶላር መያዝ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ካሟሉ በኋላ ድረ ገጽ ውስጥ በመግባት ከአንድ ፎቶ ጋር የጉዞ ቅጽ መሙላት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ከተነሱ ከሦስት ሰዓታት የአየር ላይ ጉዞ በኋላ ሲሸልስ ይገባሉ፡፡
ቱሪዝም በሲሸልስ እያደገ የመጣው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 1971 የአውሮፕላን ማረፊያ ከተቋቋመ በኋላ ነው፤ ይበልጥ የተስፋፋው ግን ሲሸልስ እ.አ.አ በ1997 እና 1998 የተካሄደውን የዓለም የቁንጅና ውድድር ካዘጋጀች በኋላ ነው፡፡ ማራኪው ገጽታዋ በዓለም አቀፍ መገናኛ ዘዴዎች ከተላለፈ በኋላ ጎብኝዎች እንደ ጉድ መጉረፍ ጀምረዋል ሲል ኤክስፒሪያንስ ሲሸልስ ድረ ገጽ ያስነብባል፡፡ በአሁኑ ወቅት 30 ከመቶ የሚሆነው የሲሸልስ ሕዝብ ቀጥተኛ መተዳደሪያው ቱሪዝም ነው፡፡
ወደ ሲሸልስ የሚመጡ ጎብኚዎች ወፍራም ኪስ፣ ተረፍረፍ ያለ ሀብት ሊኖራቸው ግድ ይላል፡፡ ሁሉም ነገር በሲሸልስ ውድ ነው፡፡ በሲሸልስ ደረጃቸውን የጠበቁ ከ780 በላይ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች፣ የእንግዳ ማረፊያዎች እና ሎጆች አሉ፡፡ እነዚህ ሆቴሎች እንኳ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ቀርቶ ለሀብታሞቹም ውድ የሚባሉ አገልግሎቶችን ነው የሚሰጡት፡፡ እርካታ እና ምቾት ሰጥተውዎት ኪስዎን ግን ማለባቸው አይቀርም፡፡
በሲሸልስ የሚያጡት ነገር የለም፤ ሲፈልጉ በባለ አምስት ኮከብ ሆቴል መኝታ ክፍል ሆነው የሕንድ ውቂያኖስን ውብ ገጽታ መመልከት ይችላሉ፡፡ አሊያም በውቂያኖስ ዳርቻ ላይ ዘና ማለት ይችላሉ፤ ከፈለጉ ደግሞ ወደ ውስጥ ገብተው ከአሳዎች ጋር እየተጋፉ ዋኝተው ማይረሳ ጊዜ ያሳልፋሉ፡፡ ጠሊቅ ዋና፣ የጫካ ጉዞ፣ የባሕር ምግቦች፣ የባሕል ጉብኝት፣ ገበያ እና ሌሎች ለጎብኝዎች አዝናኝ እና መንፈስን አርኪ ነገሮችን ማግኘት ይችላሉ፡፡
በሲሸልስ ካሉ ደሴቶች ትልቋ ማሄ ትባላለች፤ ስፋቷም 157 ስኩየር ኪሎ ሜትር ነው፡፡ ዋና ከተማዋ ቪክቶሪያ በማሄ ደሴት ነው መገኛዋ፡፡ ቪክቶሪያ ከዓለም ዋና ከተሞች በስፋቷ ትንሿ ናት፡፡ የነዋሪዎቿ ቁጥርም 25 ሺህ ብቻ ነው፡፡ በቪክቶሪያ መሃል ከተማ ለእንግሊዟ ንግሥት ቪክቶሪያ ማስታወሻነት የቆመ የሰዓት ማማ አለ፡፡ ይህ ማማ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1903 የቆመ ሲሆን የከተማዋ መለያ ነው፡፡
ሲሸልስ በሚቆዩባቸው ጊዜያት ቪክቶሪያ የገበያ ማዕከልን መጎብኘት አለብዎት፡፡ ትክክለኛውን የሀገሪቱን ዜጎች መተዋወቅ እና እየተገበያዩ መጫወት እና ወዳጅነትን ማፍራት ይችላሉ፡፡ ገበያው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1840 የተመሠረተ ሲሆን ከእሁድ በስተቀር በሌሎቹ ቀናት ክፍት ሆኖ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ አሳ፣ ኮኮናት፣ ቅመማ ቅመሞች፣ ማንጎ እና ሌሎች ነገሮችን ያገኛሉ፤ ሀገሪቷ ወደ ውጪ ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ዋነኞቹ አሳ እና ኮኮናት መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ሲሸልሳዊያን ተግባቢ፣ ለመተዋወቅ የማይከብዱ እና ተጫዋቾች ናቸው፡፡ እንግሊዝኛ ወይም ፈረንሳይኛ ቋንቋ ከሞከሩ ከሀገሬው ዜጋ ጋር ተግባብቶ ብዙ ነገሮችን ማወቅ አያዳግትዎትም፡፡
የሲሸልስን ደሴቶች በደንብ ተዘዋውሮ ለማየት ተመራጩ መንገድ ሄሊኮፕተር መከራየት ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰዓት ተኩል ተዘዋውሮ ከላይ ለመጎብኘት 800 ደላር ይከፍላሉ፤ ይህ ገንዘብ በእኛ ሀገር ምንዛሬ ስንመታው 111 ሺህ ብር ይመጣል፤ እናስ ይሞክሩታል? ይህ ተወደደብኝ ካሉ ሰባት ዶላር ከፍለው ሞርን ሲሸልስ ኮረብታ ላይ ሆነው ቪክቶሪያን እና ኤደን ደሴትን ማየት ይችላሉ፡፡ ቫሊዲ ማይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበ ጥብቅ ደን ሲሆን ፕራሊን በተሰኘችው ሁለተኛዋ ትልቅ ደሴት ይገኛል፡፡ ሲሸልሳዊያን የመጽሐፍ ቅዱሱ ኤደን ገነት እዚህ ቦታ ነው የነበረው ብለው ያምናሉ፡፡
ኤደን ደሴት ሰው ሰራሽ ናት፡፡ ከዋናው ደሴት ጋር በሰው ሰራሽ ድልድይ ተገናኝታለች፡፡ በደሴቷ ቅንጡ አፓርትመንቶች፣ ቪላዎች እና ሪዞርቶች አሉ፡፡ ጎብኝዎችም አቅም ካላቸው መከራየት ይችላሉ፤ ቤት መግዛትም ይችላሉ፡፡ ቤት መግዛት ከቻሉ ደግሞ ብዙዎች የሚመኙትን የሲሸልስ የባለሀብት የነዋሪነት ፈቃድ ያገኛሉ፡፡ ይህን ካገኙ ደግሞ የሲሸልስን ሕይወት ከዜጎቿ እኩል እንደፈለጉ ወጥተው ገብተው ማጣጣም ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የቤቶቹ ዋጋ እጅግ ውድ ነው፤ ከ350 ሺህ እስከ አምስት ሚሊዮን ዶላር ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ የሲሸልስ ሽርሽራችንን እዚህ ላይ አበቃን፤ ሰላም!
አጭር እውነታ
ሲሸልስ
- ዋና ከተማዋ ቪክቶሪያ ትባላለች፡፡
- በ2024 እ.አ.አ የሕዝብ ብዛቷ 98 ሺህ ነው፡፡
- በዓመት ከ300 ሺህ በላይ የውጪ ሀገር ዜጎች ይጎበኟታል፡፡
- ከኬንያ የባሕር ጠረፍ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ከማዳጋስካር ደግሞ አንድ ሺህ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
- በውስጧ 115 ደሴቶች አሏት፡፡
- የሲሸልስ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ነው፡፡
- የነብስ ወከፍ ገቢዋም 21 ሺህ ዶላር ነው፡፡
- ከአፍሪካ ዝቅተኛ የሙስና መጠን ያለው በሲሸልስ ነው፡፡
- በፕሬስ ነጻነት ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት፡፡
- ሲሸልስ ከታላቋ ብሪታንያ ጋር በተደረገ ድርድር በ1976 እ.አ.አ ነፃነቷን አግኝታለች፡፡
- ወደ ሲሸልስ ለመግባት ቪዛ አይጠየቁም፡፡
- በሲሸልስ ካሉ ደሴቶች ትልቋ ማሄ ትባላለች፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም