ሽምብራ የተለያዩ ዝርያዎች ያሉት ድርቅን ተቋቋሚ፣ ተመርቶ ለምግብነት ሲውልም የኘሮቲን ይዘቱ ከፍተኛ፣ ለመጪው ዘመን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
በኦስትሪያ ቪዬና ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተመራው ዓለም አቀፍ ቡድን ባደረገው ጥናት ሽምብራ የተለያዩ ዝርያዎች ያሉት ከመሆኑ ባሻገር በከተሞች አካባቢም ቢሆን ሊመረት የሚችል፣ ድርቅን ተቋቋሚ ሰብል መሆኑን አረጋግጧል::
በአብዛኛዎቹ ሃገራት ረዘም ላለ ጊዜ በተከሰተው የዓየር ንብረት ለውጥ መንስኤነት የሰብል ልማት ተስተጓጉሏል፤ ምርታማነት ቀንሷል፤ የምግብ ዋስትና መረጋገጥም ስጋት ላይ ወድቋል:: እስከ አሁን የተለያዩ ዝርያ /genetic diversity/ ባላቸው ላይ ከመመርኮዝ ይልቅ በውስን ዓይነቶች ላይ ብቻ ትኩረት ተሰጥቶ መመረቱ የምግብ ዋስትና ላለመረጋገጡ ተጠቃሽ ምክንያት ሆኗል:: ለአብነትም ሰባት ሺህ ከሚደርሱ ለምግብነት ከሚውሉት ምርቶች ውስጥ በዘጠኝ ምርቶች ላይ ብቻ ነው የምግብ ፍላጐቱን ለማሟላት መሰረት ያደረገው::
ተመራማሪዎቹ የአዝርእት የዘር ዓይነት መጥበብ ወይም የተለያዩ ዓይነቶችን መሰረት አድርጐ አለማምረት ከጠቀሜታው የበለጠ ጐጂነቱ እንደሚያመዝን አስታውቀዋል:: ምክንያታቸው ደግሞ ለበሽታ፣ ለተባይ እና ለድርቅ አጋልጦ ምርታማነትን የሚቀንስ መሆኑን ነው ያሰመሩበት::
ዓለም አቀፍ የምርምር ቡድኑ የተለያዩ የሙከራ ተግባራትን፣ ሁለገብ ጥናትና ክትትልን በሽምብራ ላይ አካሂዷል:: በውጤቱም ሽምብራ ለመጪው ዘመን ተስፋ የሚጣልበት አዝርእት ሆኖ ነው የተገኘው:: ለመጪው ዘመን የግብርናው ዘርፍ ዘላቂነት የተለያዩ የዘረመል ልዩነት ያላቸው አዝርእትን ጠብቆ ማቆየት ወሳኝ መሆኑን ነው ተመራማሪዎቹ ያስገነዘቡት።
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም