የሚሊዮኖች ጥያቄ እና ምላሹ

0
155

ለምጽዋት የተዘረጉ እጆች እርፍ እንዲጨብጡ፣ አረም እንዲነቅሉ፣ ሰብሉን ተንከባክበው ወደ ጎትራ ለማስገባት አውድማ ወደ ማዘጋጀት እንዲሸጋገሩ ከወዲሁ በትኩረት መሥራት ካልተቻለ ነባሩ ችግር ቀጥሎ አዳዲስ ተመጽዋች እጆች መዘርጋታቸው አይቀርም፡፡ በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነበራዊ ሁኔታ ከ15 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች እጆች ከአምራችነት ወደ ድጋፍ ጠባቂነት ተሸጋግረዋል፡፡ ከእዚህ ውስጥ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ከአምራችነት ወደ ጠባቂነት የመጡት ግን የማልፈልገውን ሥራ አልሠራም ብለው ሥራን በማማረጣቸው  አይደለም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ እና የቀጠሉ በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች ከሞቀ ቤታቸው እና ከአምርቶ መጋቢ መሬታቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉ፤ ተፈጥሮ ፊቷን አዙራ መሬት በድርቅ እና በጎርፍ እንድትከርም ማድረጓ እንጂ፡፡

የሰላም ጉዳይ የማይጨበጥ ጉም መሆን እና ተፈጥሮ የክረምት ወቅቱን ወደ በጋነት መቀየሯን ተከትሎ በአማራ ክልል ትናንት አምርተው ሚሊዮኖችን ይቀልቡ፣ ገበያው ሞልቶ ከተሜው ሳይሳቀቅ እንዲኖር የተትረፈረፈ ምርት ያመርቱ የነበሩ እጆች ታጥፈው ከወገን ድጋፍን ሽተው ተዘርግተዋል፡፡ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው በግጭት የተፈናቀሉትን ጨምሮ ድርቁ ባስከተለው ተጽእኖ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከእዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው በ2015/16 የምርት ዘመን ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት በተፈጠረው ድርቅ ከምርት ውጪ ሆነው የከረሙ ወገኖች ናቸው፡፡

ዘጠኝ ዞኖችን ያካለለው ድርቅ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዜጎችን ተጎጂ እንዳደረገ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ በተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰተው ድርቅ ክልላዊ የምርት አቅርቦት እንዲቀንስ፣ በረሀብ ምክንያት የሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ፣ በውኃ እና በመኖ አቅርቦት እጥረት ምክንያት በርካታ እንስሳት ለሞት እና ለስደት እንዲዳረጉ አድርጓል፡፡

በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉት እና በድርቅ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚደረገው ድጋፍ በጸጥታ ችግር እና በሌሎች ተፈጥሯዊ ምክንያቶች በወቅቱ መድረስ አልቻለም፤ ድጋፉም በቂ አይደለም፤ ሁሉም ድጋፍ የሚሹ ወገኖችም ድጋፍ እያገኙ አይደለም የሚል ወቀሳ ይቀርባል፡፡

የዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪ ጽ/ቤት በበኩሉ እየቀረበ ያለው ሰብዓዊ ርዳታ በቂ ካለመሆኑም በላይ በተለያዩ ምክንያቶች በወቅቱ እየደረሰ አለመሆኑን አስታውቋል፡፡ የጽ/ቤቱ ኃላፊ ምህረት መላኩ እንዳስታወቁት በብሄረሰብ አስተዳደሩ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉትን ከዘጠኝ ሺህ በላይ ወገኖች ሳይጨምር በድርቅ ብቻ 425 ሺህ 130 ወገኖች እጃቸውን ለድጋፍ ዘርግተዋል፡፡

ባለፉት 11 ወራት በአጠቃላይ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከተለዩ ወገኖች ውስጥ መደገፍ የተቻለው 316 ሺህ 218 ወገኖችን ብቻ እንደሆነ አቶ ምህረት ገልጸዋል፡፡ ይህ ድጋፍ የቀረበው በበርካታ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ሌሎች በጎ አድራጊ ማኅበራት እና ድርጅቶች፣ የልማት ድርጅቶች፣ በፌደራል ስጋት ሥራ አመራር እና በአማራ ክልል አደጋ መከላከል ኮሚሽኖች በኩል ነው ተብሏል፡፡ አሁንም ግን 228 ሺህ በድርቅ ተጋላጭ የሆነ የማኅበረሰብ ክፍል ምንም ድጋፍ እንዳላገኘ ጽ/ቤት ኃላፊዉ ገልጸዋል፡፡ ዋናው ችግር የተጋላጪ ወገኖች ቁጥር መብዛት እና የአቅርቦት እጥረት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የተከሰተው ድርቅ በተለይ በሰሀላ ሰየምት ሙሉ በሙሉ፣ ዝቋላ እና አበርገሌ ወረዳዎች በከፊል ከ791 ሺህ 580 በላይ እንስሳት በከፋ ስጋት ውስጥ ሲወድቁ ወደ 171 ሺህ የሚሆነውን እንስሳት ውኃ እና መኖ ወዳለባቸው አጎራባች ወረዳዎች በተለይ ወደ ደኀና እንዲገቡ በማድረግ ሕይወት የማዳን ሥራ መሠራቱን አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ተሰደው የነበሩ እንስሳትን ወደ አካባቢያቸው የመመለስ ሥራ እየተሠራ ሲሆን 14 ሺህ 397 እንስሳት መሞታቸውን ኃላፊዉ ጠቅሰዋል፡፡  አሁንም የእንስሳት መኖ በሰፊዉ እንዲቀርብ መምሪያው በተደጋጋሚ እያሳወቀ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ብሄረሰብ አስተዳደሩ ከወፍላ፣ ኮረም፣ ዛታ ወረዳዎች፣ ከኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ክልሎች የተፈናቀሉ ከዘጠኝ ሺህ በላይ ወገኖችን እያስተናገደ ነው፡፡ አንድ ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ከቀየው በተፈናቀለ ከ72 ሰዓታት በኋላ ሰብዓዊ ድጋፍ ሊያገኝ እንደሚገባ በሕግ ስለመቀመጡ አቶ መላኩ ጠቁመዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ተፈናቃይ ወገኖች በመንግሥት በኩል እንዲደገፉ በመምሪያው በተደጋጋሚ ቢጠየቅም የመንግሥት ፍላጎት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ነው የሚል መሆኑን ኃላፊዉ ገልጸዋል፡፡

“ረሀብ እስካሁን ራሱን ችሎ ሰው አልገደለም” ያሉት ኃላፊዉ፣ አሁናዊ እየታየ ያለው ምልክት ግን ድርቁ ወደ ረሀብ መቀየሩን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በዓመቱ ሊከሰቱ ይችላሉ ከተባሉ አምስት አይነት በሽታዎች ውስጥ አራቱ መከሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ከምግብ እጥረት እና ከኑሮ መጎሳቆል ጋር በተገናኘ የሚከሰተው የኩፍኝ በሽታ በዓመቱ ሲከሰት 24 ሰዎችን ለሞት መዳረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

እንደ ኃላፊዉ አካባቢው በክረምት ዝናብ ብቻ ተመርኩዞ የሚያመርት በመሆኑ የድጋፍ አቅርቦቱን ማሻሻል ካልተቻለ ቀሪ ሦስት ወራት ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ሰብዓዊ ድጋፎች ሳይቆራረጡ በሚፈለገው መጠን ተደራሽ እንዲሆኑ መሰናክሎችን ለይቶ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግሮች እና የተከዜ ድልድይ በወቅቱ አለመጠገኑ ሰብዓዊ ድጋፎች አሁንም በወቅቱ እንዳይደርሱ እክል መሆናቸውን በማሳያነት አንስተዋል፡፡ ኃላፊዉ ለበኲር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መረጃውን እየሰጡ በነበረበት ሰኔ 19 ቀን 2016 ዓ.ም የተከዜ ድልድይ ማሻገር ባለመቻሉ ሰብዓዊ ድጋፍ የጫኑ 22 ተሳቢ ተሸከርካሪዎች  ባሉበት እንደቆሙ ናቸው፡፡ ሰብዓዊ ድጋፉ የግድ በረሀብ ውስጥ ላሉ ወገኖች መድረስ ስላለበት የክልሉ አደጋ መከላከል ኮሚሽንም ሆነ መንግሥት በጀልባ ለማሻገር የጀልባ ኪራይ ወጪን ከመሸፈን ጀምሮ የስርጭት ጊዜውን ማራዘም፣ የድልድይ ግንባታውም በወቅቱ እንዲጠናቀቅ ጫና ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኃላፊዉ ማሳረጊያም ከመፈናቀል እና ከድርቅ ጋር በተገናኘ የሚነሳው ችግር የሰው ሕይወትን እንዳያሳጣ ባለሐብቶች እና ረጂ ድርጅቶች አሁናዊ የሰብዓዊ ድጋፍ ላይ በስፋት እንዲረባረቡ እንዲሁም አርሶ አደሮች ወደተሟላ የመኸር እርሻ እንዲገቡ ማስቻል ነው የሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በድርቁ ለተጎዱ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወረዳዎች የሚውል የሦስት ሺህ 889 ኩንታል ምርጥ ዘር ድጋፍ ማድረጓ ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት ያጋጠመው የዝናብ እጥረት በደቡብ ጎንደር ዞንም 232 ሺህ 894 ወገኖችን ተጋላጭ አድርጓል፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ እና አሁንም ድረስ የቀጠሉ ግጭቶች ዞኑ በአሁኑ ወቅት 49 ሺህ 204 ተፈናቃዮችን እንዲያስተናግድ ማድረጉንም ያስታወቁት የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አበባው አየነው ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ 35 ሺህ 281 የሚሆኑት ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ናቸው፡፡

እንደ ባለሙያዉ በዞኑ የሚገኙት ሁሉም ተፈናቃይ ወገኖች ተጠልለው የሚገኙት በግለሰብ ቤቶች ነው፡፡ ይህም አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ ተፈናቃይ ወገኖች በግለሰብ ቤት መኖራቸው ምቾት እንዳልሰጣቸው በመግለጽ፣ ወደነበሩበት አካባቢ እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

እንደ ባለሙዉ በድርቅ ተጋላጭ ለሆኑ እና በጸጥታ ስጋት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን በሕይወት ለማቆየት የሚያስችል ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በግለሰብ ቤቶች ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖች በሁለተኛ ዙር ድጋፎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ ለእነዚህም ወገኖች የተመደበው ድጋፍ ስምንት ሺህ 116 ኩንታል ነው፡፡

በድርቅ ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖችም የሚደረገው ድጋፍ መቀጠሉን ባለሙያው አስታውቀዋል፡፡ በስድስት ወረዳዎች ለሚገኙ 89 ሺህ ወገኖች 14 ሺህ 614 ኩንታል የዕለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ ተመድቦ የማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ባለሙያው ጠቅሰዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር በመቀጣዋ ወረዳ በድርቅ ለተጎዱ 19 ሺህ 200 ወገኖች ድጋፍ መደረጉን ባለሙያው አስታውሰዋል፡፡

ለተጎጂ ወገኖች ድጋፎችን ተደራሽ ለማድረግ ጨራታ ያሸነፉ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች የጸጥታ ችግሩን እንደ ደኅንነት ሥጋት በማንሳት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ድጋፎች ለሚፈለገው ወገን በሚፈለገው ጊዜ እንዳይደርስ ፈተና መሆኑ ተመላክቷል፡፡ ይህም የተራብን ጥያቄ ከተጎጂ ወገኖች እንዲነሳ ማድረጉ ነው የተጠቀሰው፡፡ የዞኑ አደጋ መከላከል የተጎጂ ወገኖችን ሕይወት ለመታደግ በአካባቢዉ ከሚንቀሳቀሰው ኮማንድ ፖስት ጋር በመተባበር ድጋፍ የማድረሥ ሥራውን እያከናወነ መሆኑም በባለሙያው ተገልጿል፡፡

እንደ ባለሙያዉ በድርቅ ለተጎዱትም ሆነ ለተፈናቀሉ ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ አይደለም፡፡  ይህም የሆነው በመንግሥት በኩል እየቀረበ ያለው ድጋፍ ከተረጂዉ ጋር የተመጣጠነ ባለመሆኑ ነው፡፡ የጸጥታ ችግሩ ድጋፍ ለማድረስ የሚደረገውን ሂደት እየፈተነው መሆኑን ያስታወቁት ባለሙያዉ፣ በሚፈለገው ወቅት ለሚፈለገው አካል እየደረሰ አለመሆኑን በመጠቆም ነው፡፡ ከጸጥታ ችግሩ ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት ታሪፍ በከፍተኛ ደረጃ መጨመርም ድጋፍ የሚያገኘው አካል ድጋፉን ለመውሰድ የሚያወጣው ወጪ እና የሚያገኘው ድጋፍ እንዳይጣጣም ማድረጉን አንስተዋል፡፡

አምራች ኀይሉን ከተረጂነት እና ከጠባቂነት ማውጣት እንደ ሀገር ከምርት አቅርቦት ጋር በተያያዘ እያጋጠመ ያለውን የኑሮ ውድነት በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል፡፡ ምንም እንኳ ከመፈናቀል ጋር የተያያዘው ችግር የሀገሪቱ ሰላም እና ደኅንነት በአስተማማኝ ደረጃ ሲረጋገጥ የሚመለስ ቢሆንም በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የመጣውን ችግር ግን ወቅታዊ ምቹ አማራጭ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመጠቀም መመለስ ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ የደቡብ ጎንደር ዞን በድርቅ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በዕለት ደራሽ ምግብ ከመደገፍ ባለፈ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያደርጉ አማራጮች ተግባራዊ እንዲደረጉ እያደረገ ይገኛል፡፡ እንደ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዉ በድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ፈጥነው ሊደርሱ የሚችሉ ሰብሎች እንዲዘሩ ሲደረግ፣ ይህም ከጉና ዘር ብዜት ኢንተርፕራይዝ ጋር እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የማዳበሪያ ግብዓት በሚፈለገው መጠን ማቅረብ ችግሩ በቀጣይ ዓመት እንዳይቀጥል ሊያደርግ እንደሚችል በምክረ ሐሳብ ደረጃ ተጠቁሟል፡፡ አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን ተፈናቃይ ወገኖችን ወደነበሩበት መመለስ ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን በዓመቱ ለተከሰቱ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እና በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸዉ በሚሰሩ የጋራ ተግባራት ዙሪያ ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም በባሕር ዳር ዉይይት አካሂዷል፡፡  የምግብ እህል አቅርቦት ውስንነት፣ የጸጥታ ችግር፣ ቅንጅታዊ አሰራሩ ደካማ መሆን፣ የተረጂነት አመለካከት ከፍተኛ መሆን፣ የተረጂ ቁጥር መብዛት እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች በዓመቱ ለተከሰተው ችግር ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ሂደት  የፈተኑ አንኳር ጉዳዮች እንደነበሩ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋዉ ባታብል አስታውቀዋል፡፡ በአጠቃላይ የተረጅነት አስተሳሰብን በመቀየር ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ከችግር የመውጫ ዋና መፍትሄ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አብዱ ሁሴን ባለፉት 11 ወራት በክልሉ ዉስጥ ለተከሰቱ የተፈጥሮ እና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎች “ምን አልባትም ፈጥነን ምላሽ ባንሰጥ ኖሮ የሚደርሰዉ ጉዳት የከፋ ይሆን ነበር” በማለት የተሰጠው ምላሽ የሰዎች ሕይወት መታደግ እንደቻለ ገልጸዋል፡፡

የአቅርቦትና ድጋፍ ዉስንነት መኖር፣ የተፈናቃይ ወገኖች መጠለያ ምቹ አለመሆን፣ የቅንጅታዊ አሰራር በሚጠበቀዉ ልክ አለመኖር፣ በዕቅዱ እና በተቀመጡ ግቦች ልክ አለመሥራት፣ ተግባሩን ለአንድ ተቋም መተዉ፣ የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎች ደካማ መሆንን በችግር ማንሳታቸውን ከኮሚሽኑ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ዋቢ ነው፡፡

ሊከሰቱ የሚችሉ የተፈጥሮ እና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎችን በመተንበይ ማወቅ እና መረዳት፣ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ በችግሩ ልክ ጉዳቱን ሊቀንስ የሚችል ሐብት በማሰባሰብ ምላሽ ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ መሆን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ በቀጣዩ የክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ፣ የዉኃ ወለድ በሽታዎች እና ተያያዥ ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችል የገለጹት ም/ርእሰ መስተዳድሩ፣  ቀድሞ የመከላከል ሥራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here