የሚባክን ቀን የለም

0
22

በጸጥታ መደፍረስ ውስጥ  ከሁለት ዓመታት በላይ እያሳለፈ በሚገኘው አማራ ክልል ትምህርትን በተሟላ ሁኔታ ለማስጀመር አሁንም ጥረት እየተደረገ ነው::   የትምህርት ሥራው የአምስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም በተካሄደበት ወቅት እንደተገለጸው አሁንም ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ቤቶች ጋር አልተገናኙም:: እነዚህን ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎችን መመለስ፣ ያልተከፈቱ ትምህርት ቤቶችን ማስከፈት እና በትምህርት ላይ ያሉትን የማብቃት ተግባራት ወቅታዊ የትምህርት ሥራ ሆነው እየተሠራባቸው ነው::

የጸጥታ ችግሩ በትምህርት ሥራው ላይ የፈጠረውን ችግር ተቋቁሞ ለማለፍ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ካሉት አካባቢዎች  የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ አንዱ ነው::

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደስታው ዓለሙ እንደተናገሩት  የብሔረሰብ አስተዳደሩ የትምህርት ሥራ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲታይ ተሸሽሏል:: ላለፉት ሁለት ዓመታት ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶችን በማስከፈት እና ከትምህርት ውጪ ሆነው የከረሙ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ የተሠራው ሥራ መልካም ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል:: ለውጤቱ መገኘትም ከክልል ጀምሮ ያለው የትምህርት መዋቅር ቅንጅታዊ ሥራ እና የማኅበረሰቡ የትምህርት ፍላጎት ጉጉት መሆኑን ጠቁመዋል:: ትምህርት ከማንኛውም እሳቤ ነጻ መሆኑን እና ያልተማረ ትውልድ ሀገር ሊያሻግር እንደማይችልም አስገንዝበዋል::

ብሄረሰብ አስተዳደሩ በትምህርት ዓመቱ መዝግቦ ለማስተማር የስቀመጠው ዕቅድ 467 ሺህ 15 ተማሪዎችን ነው:: ከዚህ ውስጥ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ላይ የሚገኙት 284 ሺህ ተማሪዎች ናቸው:: ይህም የዕቅዱ 61 በመቶ ነው:: ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ የተሠራው ሥራም ከባለፈው ዓመት በ122 ሺህ ብልጫ እንዳለው ነው ያስገነዘቡት::

590 ትምህርት ቤቶች ተከፍተው መማር ማስተማር እያከናወኑ  መሆናቸውን አስታውቀዋል:: ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ290 ትምህርት ቤቶች ብልጫ ያለው ነው:: አሁንም 79 ትምህርት ቤቶች አለመከፈታቸውን እና 39 በመቶ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን አስታውቀዋል::

ጃዊ፣ አየሁ ጓጉሳ እና ምእራብ ጎጃም አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ ቀበሌዎች ደግሞ ትምህርት ያልተጀመረባቸው ናቸው:: ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ግን አሁንም መቀጠሉን እና ዕድሎች መኖራቸውንም አስታውቀዋል::

በሰላም ወቅት ተማሪ መመዝገብ እና ትምህርት ቤቶችን ማስከፈት ተራ ሥራ ነው ያሉት አቶ ደስታው፤ ዋናው ጉዳይ በትምህርት ላይ ያሉት የማብቃት ሥራ ነው ብለዋል:: እያንዳንዱ ተማሪ በሚማርበት የትምህርት ደረጃ ልክ የሚገባውን ዕውቀት እንዲይዝ ማስቻል እና ለፈተና ማብቃት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው:: ተማሪ የማብቃት ሥራው ቀድሞ መጀመሩንም ጠቁመዋል::

የትምህርት መሠረቱ ከአንደኛ ክፍል ይጀምራል ያሉት አቶ ደስታው፣ በዚህ የክፍል ደረጃ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የማብቃት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል::  ክልላዊ እና ሀገራዊ ተፈታኞችን የማብቃት ሂደትም ትኩረት እንደተሰጠው አስታውቀዋል::

አዳዲስ ተማሪ የማብቃት እሳቤዎችን ማስፋት ደግሞ ለውጤት እንደሚያበቃ ተናግረዋል:: በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጣውና ተማሪዎች ለውጤት እንዲበቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው የአዳር ጥናት በብሄረሰብ አስተዳደሩ ትኩረት እንደተሰጠው አስታውቀዋል:: በገጠሩ አካባቢ ተማሪዎች ከትምህርት መልስ ቤተሰብ በማገዝ እና ለተለያዩ ሥራዎች የትምህርት ጊዜያቸውን የሚያባክኑ በመሆኑ የአዳር ጥናት ልዩ ትርጉም እንዳለው ጠቁመዋል::

ባለፈው ዓመት የአዳር ጥናት በተጀመረባቸው ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ሁሉም ማለፋቸውን ለአዳር ጥናቱ መልካም ውጤት ማሳያ አድርገው አንስተዋል:: እርስ በእርስ መረዳዳትን እና መተጋገዝን የሚያበረታታ፣ ማጣቀሻ መጻሕፍትን በቅርበት ለማግኘት ዕድል መስጠቱ ተመራጭ ያደርገዋል ብለዋል:: ክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች የአዳር ጥናት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል::

ብቁ መምህራንን ለተማሪዎች የተሻለ ውጤት ዋና መንገድ አድርጎ መጠቀም ላይም ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል:: እነዚህ መምህራን በማስተማር ሥነ ዘዴያቸው እና በተማሪዎች ፍላጎት የሚመረጡ ሆነው በማካካሻ እና በማጠናከሪያ ትምህርት ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ የሚሠሩ እንደሚሆኑ ገልጸዋል::

ከመደበኛው የትምህርት ሥራ ውጪ ያለውን ጊዜ ጨምሮ ቅዳሜ እና እሁድ የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ደስታው ገልጸዋል:: ይህንንም የሚከታተል እና ግብረ መልስ የሚሰጥ ቡድን መቋቋሙን አስታውቀዋል:: በዚህም አሠራር የተሻለ ልምድ መኖሩንና መልካም ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል::

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምርያ ኃላፊ አቶ ክንዱ ዘውዱ በበኩላቸው ትምህርት ማኅበራዊ ልማት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ልማት ማቀጣጠያ መሳሪያ ነው ብለዋል:: ለዚህም የትምህርት ተሳትፎን ከማሳደግ እና ተደራሽነትን ከማስፋት ባለፈ የተመዘገቡ ተማሪዎችን ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በመሥራት ነው ብለዋል:: ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለው የትምህርት አመራር ተወዳዳሪ ዜጋ የማፍራት ተልዕኮን በቅጡ ተረድቶ መደገፍ እና መሥራት ሲችል እንደሆነ አስታውቀዋል:: መምህራን፣ የትምህርት ቤት አመራሩ፣ የትምህርት ባለሙያው እና ወላጆች ተማሪዎችን ለማብቃት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ጠይቀዋል::

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ  ካሳሁን አዳነ የደብረብርሐን ከተማ ትምህርት መምሪያ የአንስት ወራት ዕቅድ አፈፃጸሙን በገመገመበት ወቅት ያልተማረ ሰው ሕልውናው አደጋ ላይ እንደ ሚወድቅ አስገንዝበዋል:: በመሆኑም ከቅድመ አንደኛ እስከ 11ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው የመመለስ ተግባር ዛሬም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል:: ከዚህ በኋላ የ12ኛ ክፍል ምዝገባ ግን እንደማይኖር አስታውቀዋል::

በትምህርት ላይ ያሉትን ተማሪዎች በሙሉ ለውጤት የማብቃት ሥራ በትኩረት መከናወን እንደሚኖርበት ተናግረዋል:: በተለይ ክልላዊ እና ብሔራዊ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች ልዩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል::

ለትምህርት ጥራት እና ውጤት ትምህርት ቤቶችን ምቹ ማድረግ፣ ማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣  መጻሕፍት ቤቶችን በሁሉም ቀናት ክፍት ማድረግ፣ ፈተናን በዕቅድ መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል:: በአጠቃላይ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ማናቸውንም ስነ ዘዴዎች አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል::

 

ግዕዝ በአማርኛ

ለፈተና እንዴት መዘጋጀት ይቻላል?

 

በጠዋት ወደ ጥናት መግባት

ምን ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ መወሰን

እቅድ ማዘጋጀት

ከፋፍሎ ማጥናት

ራስን በራስ ቶሎ ቶሎ መፈተን

ከተንቀሳቃሽ ስልክ መራቅ

ሙዚቃ መቀነስና በጸጥታ ማንበብ

ቋሚ እረፍትና አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ

በቂ እንቅልፍ መተኛት

መረጋጋትና በጎ በጎውን ማሰብ

ምንጭ፡- https://www.topuniversities.com/

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የታህሣስ 13  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here