በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ በተለምዶ እጁ ወይም እግሩ የሚንቀጠቀጥበትን ሰው “ሀጢያት ሰርቶ ወይም ድመት ገድሎ ነው” የሚል የተዛባ እሳቤ አለ:: ይሁንና እነዚህ ሰዎች እጃቸው ወይም እግራቸው የሚንቀጠቀጠው በሰሩት ግፍ ወይም ሀጢያት ሳይሆን ፓርኪንሰን በሚባል በሽታ በመታመማቸው ነው::
ኒውስ ሜዲካል ኔት ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ስለፓርኪንሰን በሽታ የመጀመሪያ ዝርዝር የሕክምና መግለጫ በመስጠት በጽሁፍ በማሳተም ግንዛቤ የፈጠረው እ.አ.አ. በ1817 እንግሊዛዊው ሐኪም ጄምስ ፓርኪንሰን ነበር:: ከዚያም እ.አ.አ. ከ1825 እስከ 1893 የኖረው ፈረንሳዊው የነርቭ ሐኪም ዣን ማርቲን ቻርኮት ስለፓርኪንሰን በሽታ ዓለም የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖረው አድርጓል::
ሰዎችን ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆነ ሁኔታ ሰውነታቸው እንዲንቀጠቀጥ የሚያደርገው የፓርኪንሰን ሕመም ስርጭቱ ከዕለት ዕለት እየጨመረ ይገኛል:: በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነርቭ ክፍል ኃላፊ እና የነርቭ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ማቲያስ አዱኛ እንደገለጹት ፓርኪንሰን በሽታ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል አንዱ ነው:: የፓርንኪንሰን በሽታ ውስብስብ እና አልፎ አልፎም በቅጡ መረዳት የሚያዳግት ሕመም ነው::
ባለሙያው እንዳብራሩት፤ የፓርኪንሰን በሽታ የነርቭ ስርዓት እንቅስቃሴ መዛባት ሲሆን ቀስ በቀስም ሥር እየሰደደ እና እየተባባሰ የሚሄድ በተለይም የአካል እንቅስቃሴን የሚቆጣጠረውን የአንጎል ክፍል የሚያጠቃ እና ከነርቭ ሥርዓት መታወክ ጋር የተዛመደ የጤና ችግር ነው:: በዋናነት ይህ በሽታ የሚከሰተው ጭንቅላታችን ውስጥ እንቅስቃሴያችንን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የነርቭ ዘንጎች በተለያዩ አጋላጭ ምክንያቶች ተጎድተው ሰውነታችን የእንቅስቃሴ ቅንጅት እንዲኖረው የሚያደርግ በጭንቅላት ውስጥ የሚገኝ ዶፓሚን የሚባል ኬሚካል ማመንጨት ሲያቆሙ ነው::
የፓርኪንሰን በሽታ መንስኤዎች
ዶ/ር ማቲያስ እንደሚሉት የፓርኪንስን በሽታ መንስኤዎች እና አጋላጭ ሁኔታዎች በተጨባጭ በውል ባይታወቁም ነግር ግን የአፈጣጠር ችግር፣ ለፀረ ተባይ እና አረም ኬሚካሎች መጋለጥ፣ አንጎል ላይ በሚደርስ አደጋ፣ የአካባቢ ተጽእኖ እና በዘረመል ከቤተሰብ ቀደም ሲል የፓርኪንሰን ተጠቂ የነበሩ እናት ወይም አባት እህት ወንድም ካሉ ሊከሰት እንደሚችል በጥናቶች እንደተረጋገጠ ይናገራሉ:: በለጋ ወይም በመካከለኛ ዕድሜ (በተለምዶ ከ65 ዓመት በፊት) በፓርኪንሰን በሽታ የተያዙ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በሽታው ከጀመራቸው በኋላ ብዙ ዕድሜ ይኖራሉ:: አንዳንድ ጊዜ ከ 20 እስከ 30 ዓመታት ከበሽታው ጋር ሊኖሩም ይችላሉ:: ይሁንና ሕመማቸው ቀስ በቀስ እየጨመረ ሊሄድ ይችላል:: አንድ ሰው ፓርኪንሰን አለበት የሚባለው ምልክቶችን ማሳየት ሲጀምር ነው:: እንዲሁም አንድ ሰው ፓርኪንሰን በሽታ በ60 ዓመቱ ጀመረው ማለት በ40ዎቹ እድሜ ላይ እያለ ነበር ምልክቶቹ ጀምረውት የነበረው ማለት ነው::
የፓርኪንሰን በሽታ ምልክቶች
የፓርኪንሰን በሽታ ምልክቶች ለሁሉም ሰው አንድአይነት ያለመሆን አጋጣሚው ቢኖርም አብዛኛዎቹ ግን ተመሳሳይ ናቸው:: በሽታው ሲጀምር ላይታወቅ ይችላል:: ምክንያቱም የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች ቀላል በመሆናቸው በቀላሉ ሊስተዋሉ አይችሉምና::
ዶ/ር ማቲያስ እንዳስገነዘቡት ምልክቶቹ ቀስ በቀስ ይጀምራሉ:: የመጀመሪያው ምልክት በአንድ እጅ ላይ ብቻ ወይም አንዳንዴም በእግር ወይም መንጋጋ ላይ በቀላሉ የማይታይ መንቀጥቀጥ ሊኖር ይችላል። መንቀጥቀጥ በፓርኪንሰን በሽታ የተለመደ ነው። ነገር ግን ሕመሙ ግትርነት(እንደፈለጉት መንቀሳቀስ አለመቻል)፣ የእንቅስቃሴ ዝግ ማለት በፍጥነት ይራመዱ ከነበረ ርምጃዎ ዝግ ያለ ይሆናል::
እጅዎትን እያወራጩ የሚያወሩ ከሆነ ያንን ማድረግ አይችሉም:: እንደበፊቱ መናገር እና መጻፍ አለመቻል፣ ጭንቀት፣ በተደጋጋሚ የሆድ ድርቀት ያጋጥመዎታል:: እንቅልፍ ይቸገራሉ። ለመቀመጥ ወይም ለመነሳት፣ ለመታጠብ ወይም ለመልበስ መቸገር፣ ይህም ቀላል ሥራዎችን የበለጠ ከባድ ያደርግበዎታል:: የሰውነት ሚዛን መጠበቅ ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል:: ይህም የመውደቅ አደጋን ይጨምራል። እንዲሁም ቶሎቶሎ መሽናት፣ የአስተሳሰብ(የማሰላሰል) እና የማስታወስ ችግር ያጋጥመዎታል። እንዲሁም በጣም የድካም ስሜትን ሊያካትቱ ይችላሉ። ታዲያ ይህን ሁኔታ የሚያስተውሉት በጊዜ ሂደት ነው፤ በአንዴ ማወቅ አይችሉም:: የመንቀጥቀጥ ሂደቱ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ይሄዳል::
ሕክምናዎቹ
የፓርኪንሰን በሽታ አንዴ ከጀመረ በኋላ እስከ ሕይዎት ፍጻሜ አብሮ የሚኖር በመሆኑ ስር ሳይሰድ በጊዜ ተለይቶ ሕክምና መጀመር ተገቢ እንደሆነ ነው የተናገሩት:: ፓርኪንሰን መዳን ባይችልም መታከም ግን ይችላል::
ፓርኪንሰን ያለባቸው ሰዎች ሁልጊዜ በመድኃኒት ወዲያውኑ እንደማይታከሙ ልብ ማለት ያስፈልጋል።
ለፓርኪንሰን የሚታዘዙ መድሃኒቶች አብዛኛውን ጊዜ ምልክቶችን ለተወሰነ ዓመት መቆጣጠር እንደሚያስችል የተናገሩት ዶ/ር ማቲያስ የዶፓሚን መጠን መቀነስ ስለሆነ በሽታውን የሚያስከትለው አብዛኛዎቹ የፓርኪንሰን በሽታ ያለባቸው ሰዎችም በዋነኝነት ሌቮዶፓ የሚባል መድኃኒት ያስፈልጋቸዋል። ሌቮዶፓ በአንጎልዎ ዶፓሚን ኬሚካል እንዲመረት የሚያስችል መድሃኒት ነው:: ይህም የተዳከመውን እንቅስቃሴን በሚቆጣጠሩ የአንጎል ክፍሎች እና ነርቮች መካከል መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ያገለግላል። በተጨማሪም ለአንዳንድ ታማሚዎች የነርቭ ቀዶ ጥገና ሕክምናዎች ሊደረግላቸው ይችላል:: ከዚህ ውጭ ንግግራቸው እንዲሻሻል (speech therapy) እና ሌሎች የሰውነታቸው ክፍሎች እንዲፍታቱ የፊዚዮቴራፒ ሕክምናዎች እንዲያደርጉ ይመክራሉ::
መከላከያው
የፓርኪንሰን በሽታ መንስኤው በውል ስለማይታወቅ ለመከላከል የሚያስችሉ ምንም የተረጋገጡ መንገዶች የሉም:: ይሁንና አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሰው ለፓርኪንሰን በሽታ ተጋላጭነቱ ዝቅተኛ ነው። ምክንያቱም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሰውነትን በሽታን የመከላከል አቅም ይጨምራልና:: አንዳንድ ጥናቶች ደግሞ እንደ ቡና እና አረንጓዴ ሻይ ያሉ ካፌይን ያላቸውን መጠጦች በመጠጣት የፓርኪንሰን በሽታ ተጋላጭነትን እንደሚቀንሱ ባለሙያው ይመክራሉ።
ጤና አዳም
ሕብረተሰቡ ከሄሞራጂክ ፊቨር ራሱን እንዲጠብቅ ተጠቆመ
የጤና ሚኒሥቴር በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጅንካ ከተማ የሄሞራጂክ ፊቨር (Hemorrhagic Fever) በሽታ መከሰቱን የቅኝት መረጃዎች ማመላከታቸውን አስታውቋል፡፡
ከሚኒሥቴሩ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው /ዘገባው እስከተጠናቀረበት 4/3/2018/ ሚኒሥቴሩ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበሽታውን መንስኤ ለማወቅ ፣ ስርጭቱን ለመግታት እንዲሁም ለመቆጣጠር ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ወደ ቦታው በመላከ የመስከ ግምገማዎች እና የላብራቶሪ ምርመራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ በተጨማሪም የማሕበረሰብ ቅኝት፣ የንከኪ ልየታ፣ የቤት ለቤት ልየታ እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን እያጠናከረ ይገኛል።
ሰዎች በአፍ፣ አፍንጫ እና በሌሎች የሰውነት ክፍሎች የመድማት፣ ትኩሳት፣ ማስቀመጥ እና ማስመለስ ምልክት ሲኖር ወደ ሕክምና ተቋማት መሄድና በወቅቱ የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ሚኒሥትሩ ጠቁሟል፡፡ ምልክት ከታየበት ማንኛውም ሰው ጋር ንክኪ በሚኖርበት ጊዜም ሁልጊዜ እጅን በሳኒታይዘር ወይም በውሃና በሳሙና በመታጠብ ማጽዳት ተገቢ እንደሆነም መረጃው አመላክቷል፡፡
ማንኛውም ጤና ተቋም በታካሚዎች ልየታ በየአካባቢው ልዩ ትኩረት በመስጠት የቫይራል ሄሞሬጅክ ፊቨር (Viral Hemmoragic Fever) መሰል በሸታ መለየት፣ መመርመር፣ ማከም እና ሪፖርት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ሚኔሥቴር መሥሪያቤቱ አሳስቧል፡፡
ስለበሽታው ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት እንዲያስችልም በ 8335 እና በ952 ነጻ የስልክ መስመሮች በመደወል ማግኘት እንደሚቻል ተቋሙ አስታውቋል፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


