እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1908 በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ 15 ሺህ ሴቶች ወደ አደባባይ ወጡ:: ምን ፈልገው? ለሚለው ለልፋታቸው ተመጣጣኝ ደመወዝ፣ ምቹ የሥራ ቦታ፣ መምረጥም ሆነ መመረጥ …እንዲፈቀድላቸው ለመጠየቅ ነበር:: ከዓመት በኋላ የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ ዕለቱን ብሔራዊ የሴቶች ቀን ብሎ ጠራው:: ይህ በሆነ በሁለተኛው ዓመት ክላራ ዚክተን የተባለች ሴት በዓሉ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉ እንዲከበር በዴንማርክ ኮፐንሀገን በተደረገ ጉባኤ ላይ ሀሳብ አቀረበች:: በጉባኤው ከ17 ሀገራት የተውጣጡ መቶ ሴቶች ተሳትፈውበታል::
ከተሳተፉት ሀገራት መካከል የክላራን ሀሳብ የተቀበሉት ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ኦስትሪያ እና ዴንማርክ በቀጣዩ ዓመት በዓሉን አከበሩ:: ይህን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ይዘት ኖሮት መከበር የጀመረው ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕለቱን የሴቶች ቀን ብሎ ማወጁን ተከትሎ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጠር በ1975 ነበር::
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ አካባቢ እ.አ.አ በ1917 የሩሲያ ሴቶች “ሰላም እና ዳቦ!” የሚል መፈክር ይዘው የሞስኮና የፒተስበርግ ከተሞችን አጥለቅልቀው ለአመጽ ወጡ:: አመጹ ቶሎ ሳይበርድ ለአራት ቀናት የዘለቀ ነበር:: በወቅቱ የነበሩት የሩሲያው መሪ ቄሳር አማራጭ አልነበራቸውምና ሴቶች የመምረጥ መብት እንዲኖራቸው ፈቀዱ::
ይህ ጊዜ ታዲያ በጁሊያን ዘመን አቆጣጠር የካቲት 23 ነበር:: ይህ ዕለት በጎርጎሮሲያዊያኑ ሲመነዘር ማርች 8ቀን በየዓመቱ የሴቶች ቀን እንዲከበር ምክንያት መሆኑን ቢቢሲ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ109ኛ ጊዜ ሲከበር ቀኑን ለማሰብ ያሰፈረው መረጃ ያሳያል:: ታዲያ ዕለቱ እ.አ.አ 2024 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ ዘንድሮ ይከበራል::
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ ምጥን ብርሃኑ እንደሚገልፁት ስለሴቶች ለረጅም ጊዜ ማህበረሰቡ ባለው የተዛባ የሥርዓተ ፆታ አመለካከት የቁጥራቸውን ያክል በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስክ ባለመሳተፋቸው ለሀገራቸው ማበርከት የሚገባቸውን ሳያበረክቱ ራሳቸውንም ተጠቃሚ ሳያደርጉ ቆይተዋል:: አጠቃላይ የሴቶች መብት እና ደህንነት ተብለው የሚነሱ ጉዳዮች ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ሊያገኛቸው የሚገቡ መብቶች ቢሆኑም የተዛባ የሥርዓተ ፆታ አመለካከቱ ግን የሴቶችን መብት ሲገፈፍ መቆየቱን አስታውሰዋል::
ወ/ሮ ምጥን እንደሚሉት በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታም ለረዥም ጊዜ ስር ሰዶ በቆየው የተዛባ የስርዓተ ጾታ አመለካከት ምክንያት ሴቶች ለከፍተኛ የሥራ ጫና፣ መድሎ እና ዝቅተኛ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው አድርጓል::
ከ19ነኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በተደረገው እንቅስቃሴ ግን ሴቶችን የተመለከቱ የተለያዩ ሥራዎች እና የሕግ ማዕቀፎች ወጥተዋል:: የወጡ የሕግ ማዕቀፎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ደግሞ ሴቶች እውቀታቸውን የማሳደግ (ማሳወቅ) ተግባር ተካሂዷል::
ይህንን ችግር ለመፍታት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከልም ሁነቶችን ወቅታዊ ችግሮችን ባገናዘበ አግባብ ሕዝብን ማንቃት (በንቅናቄ)አንዱነው:: በዚህም በየዓመቱ የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ከወቅታዊ የሴቶች ችግርና ፍላጎት በመነሳት ትርጉም ባለው መልኩ ሲከናወን መቆየቱን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ተናግረዋል::
እንደ ወ/ሮ ምጥን ማብራሪያ በዓሉን አንድ ቀን አክብሮ መተው ሳይሆን እንደየ ዘረፉ በማህበራዊውም ሆነ በፖለቲካው ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ በሚችሉበት መንገድ የማብቃት ሂደት አስፈላጊ ስለሆነ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ተከናውኗል:: እንደ ሀገርም ሆነ ክልል የሚከበርበት ሂደት ወቅትን ያገናዘበ አጀንዳ እንደሚነሳበት ወ/ሮ ምጥን ጠቁመዋል:: መሪ ቃልም የሚሰየመው ዓመቱን ሙሉ ከሚሠራው ሥራ በመነሳት ነው::
እንደ ወ/ሮ ምጥን ገለጻ ቀኑ ሲከበር ግን በእለቱ የተለያዩ ተቋማት የሴቶችን ጉዳይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ሴቶች ያሉበት ሁኔታ እየተገመገመ የተሻለ ሁኔታ እስኪመጣ እውቅና የሚፈጠርበት መንገድ ነው:: በዚህም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል በሚፈለገው ልክና መጠን ባይሆንም የተወሰኑ ለውጦች ተመዝግበዋል::
እስካሁን የሴቶችን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሚወጡ የሕግ ማእቀፎች በትክክል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ፣ የሃብት፣ የንብረት እና የመሬት ባለቤትነታቸው መረጋገጡ፣ ከምጣኔ ሃብት ጋር ተያይዞ የቁጠባ ባህል ማዳበር እና በብድር በገቢ ማስገኛ ሥራ በመሰማራት የገንዘብ አቅማቸውን ማሳደግ፣ ልፋትና ጉልበት ሊቀንሱ የሚችሉ የተሻሻሉ ቴክኖሎጅዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የጤና እና የትምህርት ተደራሽ መሆን ችለዋል:: እነዚህም መደበኛ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን /ማርች 8/ ትርጉም ባለው መልኩ በተለያዩ ዝግጅቶች በንቅናቄ መከበሩ ደግሞ እንደ ክልል ካስገኛቸው ለውጦች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው::
ባለፈው ዓመት ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን ሲከበር እንደ ሀገር የፆታዊ ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበት ወቅት ስለነበር “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ቃል የሴቶችን ጥቃት ለማስቆም የሁሉም አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ግንዛቤ የተፈጠረበት እንደነበርም ወ/ሮ ምጥን ጠቁመዋል:: በዚህ ዓመትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ “ሴቶችን እናበቃለን፤ ልማትና ሰላምን እናረጋግጣለን” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል::
አሁን ላይ በሀገራችን በተከሰተው የሰላም እጦት ሴቶች በሰላሙ ግንባታ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ከቤታቸው ልጆቻቸውን ከመቅረጽ ጀምሮ እስከ ሀገር ዓቀፍ ደረጃ የሚፈለግባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ዓመቱን ሙሉ በዚህ ዙሪያ እንደሚሠራም ኃላፊዋ ገልፀዋል:: ዕለቱን አስመልክቶም ሴቶች ጤናቸው እንዲጠበቅ የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ ለሰባት ቀናት ከፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ጋር በመተባበር ይከናወናል::
ሴቶች በአብዛኛው “አልችልም” የሚለውን አመለካከት ከመቀየር ባሻገር በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚታየውን አመለካከት ሙሉ ለሙሉ ባይባልም እየተቀየረ የመጣበት ሂደት መፈጠሩንም ወ/ሮ ምጥን ጠቁመዋል:: ይህም የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ ጥቅሙ ለሀገር እድገት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ጠይቀዋል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም