የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም
በአማራ ክልል ህፃናትና ታዳጊ ሴቶችን ከማህፀን በር ጫፍ ካንሰር መጠበቅ የሚያስችል ክትባት በዘመቻ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ዘመቻ ላይ የተዘጋጀ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
ክትባቱ ከዘጠኝ እስክ 14 ዓመት የዕድሜ ክልል ለሚገኙ ህፃናትና ታዳጊ ሴቶች በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች ማዕከላት በዘመቻ እንደሚሰጥ ተገልጿል። የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ተምትም እንዳሉት፣ የካንሰር በሽታው “ሂውማን ፓፒሎማ” ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣና ቀድሞ መከላከል ካልተቻለ ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች መካከል አንዱ ነው።
በሽታውን ቀድሞ ለመከላከል ክትባቱን ከህዳር ዘጠኝ እስክ 14/2017 ዓ.ም ለሰባተኛ ጊዜ ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል። በዚህም በክልል ደረጃ ከአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ለሚበልጡ ህፃናት እና ታዳጊ ሴቶች ክትባቱ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በሽታውን ለመከላከል ከክትባትና ህክምና ባሻገር ለህብረተሰቡ በተቀናጀ መንገድ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ለዘመቻው መሳካት ሁሉም እንዲተባበር መልዕክት አስተላልፈዋል።
በክልሉ ምክር ቤት የሴቶች ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ በበኩላቸው፣ የሴቶችን ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት ለማሳካት በጠንካራ ትብብር መስራት ይገባል ብለዋል። የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ ገዳይነቱን ከግምት በማስገባት የመከላከል ሥራው ላይ በጠንካራ ቅንጅት መሠራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ለክትባት የመስጠት ዘመቻ መሳካት የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሌሎች ባለድርሻ እና አጋር አካላት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አመልክተዋል። በክልሉ ባለፈው ዓመት 81 ሺህ ሴቶችን በመለየት በተደረገ ምርመራ ሦስት ሺህ የሚጠጉ ሴቶች የካንሰር ቅድመ ምልክት እንደታየባቸው ማረጋገጥ እንደተቻለ ተጠቁሟል። ዘገባው የኢዜአ ነው፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም