የማርበርግ ቫይረስ በሽታ

0
79

በሕዳር ወር ሁለተኛ  ሳምንት  በደቡብ ክልል ኦሞ ዞን ምንነቱ ያልተረጋገጠ በሽታ መከሰቱን የሀገሪቱ ጤና ሚኒሥቴር አሳውቆ ነበር:: በዚሁ  በሽታ ከተጠረጠሩ ሰዎች በተወሰደ የላብራቶሪ ምርመራ  የማርበርግ ቫይረስ መሆኑን   ሚኒሥቴሩ በያዝነው ሳምንት  አረጋግጧል። በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዘረመል ትንተና ቫይረሱ ቀደም ሲል በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ተከስቶ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ነው የገለጸው::

ማርበርግ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በጎርጎሮሳዊያኑ በ1967 በጀርመን ማርበርግ እና ፍራንክፈርት ነበር::  በመቀጠልም በቤልግሬድ እና ሰርቢያ ውስጥ ሁለት ጊዜ ተገኝቷል:: በወቅቱ ለወረርሽኙ መከሰት ምክንያት ናቸው የተባሉት ከኡጋንዳ ወደ አውሮፓ የተወሰዱ የአፍሪካ አረንጓዴ ዝንጀሮዎች ናቸው።

በአፍሪካ በአንጎላ፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በኢኳቶሪያል ጊኒ፣ በጋና፣ በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ (በቅርብ ጊዜ ወደ ዚምባብዌ የጉዞ ታሪክ ያለው ሰው)፣ በታንዛኒያ ፣ ኡጋንዳ እና ሩዋንዳ ውስጥ መከሰቱም ተረጋግጧል::

የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ምንድን ነው?

የማርበርግ ቫይረስ በማርበርግ ቫይረስ የሚከሰት ከባድ እና ብዙ ጊዜ ለሞት የሚያበቃ በሽታ ነው:: በሽታው የሚመጣው ከሌሊት ወፍ   (fruit bats) ነው:: የግብፅ የሌሊት ወፍ ብዙውን ጊዜ ቫይረሱን ትሸከማለች:: የቫይረሱ ዝርያ ፊሎቫይረስ (filoviruses) የሚባል ሲሆን የቫይረሱ ሽፋን እና ዘረመል በቅባታማ ሽፋን የተጠቀለለ ነው::   ቫይረሱ በሌሊት ወፎች ላይ  በሽታ አያመጣባቸውም::  ጉዳት የሚያደርሰው  ወደ ሰው ከተላለፈ በኋላ ነው::

 

የማርበርግ ቫይረስ እንዴት ይተላለፋል?

በሌሊት ወፍ ሽንት፣ ኩስ እና ምራቅ የተበከሉ ነገሮች ቫይረሱን ሊያስተላልፉ ይችላሉ። የሌሊት ወፍ በሚገኙበት ዋሻ ውስጥ ለማዕድን ቁፋሮ  እንዲሁም ለጉብኝት የሚገቡ ሰዎች ለቫይረሱ የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

በበሽታው ከተያዙ ሰዎች የሰውነት ፈሳሽ ወይም ከተበከሉ ቁሳቁሶች ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባላቸው ሰዎች መካከል ይተላለፋል። ይህ ማለት ቫይረሱ የሚዛመተው ከታመመ ሰው ደም እና የሰውነት ፈሳሽ ፣ትውከት፣ ሰገራ፣ ሽንት፣ ምራቅ፣ ላብ፣ የጡት ወተት፣ የብልት ፈሳሽ ወዘተ ጋር በቀጥታ ንክኪ ሲኖር ነው። በቫይረሱ የተያዘ ሰው የተጠቀመባቸውን መርፌ፣ ልብሶች(አንሶላ ፣ብርድልብስ…) ወዘተ ቫይረሱን እንደሚያስተላልፉ ልብ ሊባል ይገባል::

 

የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ምልክቶች

ከዓለም ጤና ድርጅት ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስገነዝበው ቫይረሱ ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ የሕመም ምልክት ለማሳየት  ከሁለት  እስከ 21 ቀናት ይቆያል:: ምልክቱ ሲጀምር ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ ራስ ምታት ፣ ከባድ ድካም እና የጡንቻ ሕመም የተለመዱ  ናቸው:: ውኃማ ተቅማጥ፣ የሆድ ሕመም እና ቁርጠት፣ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ቀጥለው የሚከሰቱ ምልክቶች ናቸው:: የሕመም ምልክቶች ከታዩ ከሁለት እስከ ሰባት ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥም በሕመምተኞች ላይ የማያሳክክ ሽፍታ ይወጣል::

ሕመሙ መሰማት ከጀመረበት አምስተኛ  ቀን ጀምሮ ሕሙማኑ የደም መፍሰስ ምልክቶች ሊታዩባቸው ይችላሉ:: እነዚህም ትኩስ (የሞቀ) ደም ማስታወክ፣ በሰገራ መልክ ፣ ከአፍንጫ፣ በድድ እና በብልት ውስጥ  መፍሰስ ይኖራል::  ግራ መጋባት፣ ብስጭት እና ጠበኝነት ህሙማኑ ላይ ሊያስከትል ይችላል:: የአንድ ወይም የሁለቱም የወንድ የዘር ፍሬዎች እብጠት መከሰትም አልፎ አልፎ  ሪፖርት ተደርጓል:: የደም ግፊት ይቀንሳል፣ የጉበት፣ ኩላሊት እና ሌሎችም የሰውነት ክፍሎች ጉዳት ያደርሳል::

ምልክቱ ከታየ ከስምንት እስከ ዘጠኝ ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥም ሞት ይከሰታል:: አብዛኛውን ጊዜ ለሞት የሚያበቃውም በከባድ የደም መፍሰስ እና ድንጋጤ ነው:: በተጨማሪም ከበሽታው የተረፉ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ለማገገም ከቀናት እስከ ሳምንታት ሊወስድባቸው ይችላል።

 

ተጋላጮች እነማን ናቸው?

በቫይረሱ ከተጠቃ ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው ቤተሰብ ወይም አስታማሚዎች ጥንቃቄ እስካላደረጉ ድረስ ለቫይረሱ የመጋለጥ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው:: ሕሙማን በሚታከሙበት ወቅት የጤና ባለሙያዎች ጥንቃቄ ካላደረጉ በተደጋጋሚ በቫይረሱ ሊያዙ ይችላሉ::

 

ሕክምናዎቹ

ማርበርግ ቫይረስ በሽታ ምንም ዓይነት ክትባት ወይም የፀረ-ቫይረስ ሕክምናዎች የሉትም፤ ነገር ግን የተለያዩ ክትባቶች እና የመድኃኒት ሕክምናዎች በጥናት ላይ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል:: ድርጅቱ የሕክምና ባለሙያዎች ሆስፒታል ለሚገኙ ሕሙማን ብዙ ፈሳሽ (ግሉኮስ) በመስጠት እና የፈሰሰውን ደም በመተካት እና የሕመም ማስታገሻዎችን በመስጠት ለማከም እንደሚሞክሩ ነው የጠቆመው::

 

መከላከያ መንገዶች

ለማሕበረሰቡ ቫይረሱ በምን ሁኔታ ሊከሰት እና ሊተላለፍ እንደሚችል ግንዛቤ ማሳደግ የመጀመሪያው ተግባር ነው::  ሰዎች ሊወስዷቸው የሚችሏቸውን የመከላከያ ርምጃዎች ማሳወቅ እና እንዲተገብሯቸው ማስቻልም ስርጭቱን ለመቀነስ ውጤታማ መንገድ ነው።

የሌሊት ወፎች ወደ ሚኖሩበት  ዋሻዎች አለመሄድ፣ ወረርሽኙ በሚከሰትበት ጊዜ  የእንስሳት ውጤቶችን  አብስሎ መመገብ፣ በሕብረተሰቡ ውስጥ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ አጋጣሚን ለመቀነስ በበሽታው ከተያዙ ሕሙማን ጋር በቀጥታም ሆነ በቅርብ ግንኙነት (በተለይም ከሰውነታቸው ፈሳሽ ጋር) አለመፍጠር ይመከራል። ከሕሙማን  ጋር የቅርብ አካላዊ ንክኪን ማስወገድ፣ የተጠረጠሩ ወይም ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠባቸውን ታካሚዎች ለቅድመ እንክብካቤ እና በቤት ውስጥ ቫይረሱ እንዳይተላለፍ የሕክምና ማዕከል ውስጥ ተለይተው መቀመጥ አለባቸው::

በወረርሽኙ ሕይዎታቸው ያለፈ ሰዎችን  በአስተማማኝ እና በክብር መቅበርም ይመከራል:: ከሟቹ አካል ጋር ቀጥተኛ ግንኙነትን የሚያካትቱ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ለማርበርግ ቫይረስ መተላለፍ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ::  በበሽታው  ተይዞ ከነበረ ሰው ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች በመለየት ለ21 ቀናት ለይቶ ጤናቸውን መከታተልም፣ ለሕሙማን ራስን ጠብቆ እንክብካቤ ማድረግ እና  ንፅህናን መጠበቅ በሽታው እንዳይስፋፋ ይረዳል::

የጤና ባለሙያዎች ታማሚዎችን በሚንከባከቡበት ጊዜ የእጅ ጓንት፣ የአፍ እና የዐይን መሸፈኛ ጭምብል/ማስክ/ ማድረግ እና  መላ ሰውነትን ፈሳሽ በማያስገባ የሕክምና አለባበስ መሸፈን ተገቢ ነው:: የተጠረጠሩ ወይም ቫይረሱ  ያለባቸውን ታካሚዎች የሚንከባከቡ የሕክምና ባለሙያዎችም በታካሚው ደም እና የሰውነት ፈሳሽ ከተበከሉ ቁሳቁሶች ማለትም ከልብስ እና አልጋ ልብስ ንክኪ ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን መተግበር አለባቸው።

የታመመን ሰው በቤት ውስጥ ከማከም ይልቅ  ወደ ጤና ተቋም ሄዶ እንዲታከም ማድረግ፣ እያንዳንዱ ሰው እጁን በአልኮል ወይም በሳሙና በደንብ በመታጠብ ንጽህናውን  መጠበቅ እንደሚገባም ጤና ባለሙያዎች መክረዋል::

 

የሀገራት ተሞክሮ

ጋና የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መኖሩን ያረጋገጠቸው እ.አ.አ በሐምሌ7/2022 ነበር::  ከዚያም ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ጋር በመሆን በሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒሥቴር እና በጋና ጤና አገልግሎት (ጂኤችኤስ) መሪነት አጠቃላይ የሕዝብ ጤና እርምጃዎችን በመተግበር እ.አ.አ. በ2022 የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ወረርሽኝን በተሳካ ሁኔታ ተቆጣጥራለች። ወረርሽኙ ከ42 ቀናት በኋላ ነበር ማብቃቱን ያወጀችው።

የበሽታውን መንስኤዎች እና መከላከያዎችን ለማሳወቅ  ለአካባቢው ማሕበረሰብ በሬዲዮ፣ በማሕበረሰብ መረጃ ማዕከላት እንዲሁም በባህል መሪዎች አማካኝነት የሕብረተሰብ ጤና ግንዛቤ ማስጨበጫ  ዘመቻዎች ተደርገዋል።  ማሕበረሰቡ ከዋሻዎች የበሽታ አምጪዎችን እንዲያስወግድ እና የእንስሳት ምርቶችን በደንብ አብስለው እንዲመገቡ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል:: በተጨማሪም ደኅንነቱ የተጠበቀ እና የተከበረ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች በሕዝብ ጤና መመሪያዎች መሠረት ተፈጻሚ ሆነዋል።

ሌላዋ ሀገር ሩዋንዳ ስትሆን የማርበርግ በሽታን ለመከላከል የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅትን ጨምሮ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የረዴት ድርጅቶች ጋር የቅርብ ትብብር በማድረግ በመከላከሉ ዙሪያ ከፍተኛ ሥራዎችን ተግብራለች:: ቤት ለቤት የሚደረጉ ምርመራዎችን ያካተተ ሁለገብ የጤና  የክትትል ስርዓትም ዘርግታለች። በማዕድን ማውጫ አካባቢዎች ወረርሽኙን መከላከል የሚያስችል ክሊኒኮችን በመገንባት የማዕድን አውጪዎችን ጤና ለመቆጣጠር ሞክራለች:: የእንስሳት እና የሰው የጤና ባለሙያዎችን አቀናጅታ በአንድ እንዲሠሩ አድርጋለች::

 

ጤና አዳም

ከማርበርግ ቫይረስ በሽታ  የተረፉ ሰዎችን፣ አጋሮቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ፍቅር እና ርህራሄ ሊሰጧቸው ይገባል። የተረፉ ሰዎች በሁለቱም ማለትም በአካል እና በስነ ልቦና  ሊሰቃዩ ይችላሉና።

*ማርበርግ ቫይረስ ከበሽታው ካገገሙ አንዳንድ ሰዎች ላይ  የወንድ የዘር ፍሬ እና የዐይን ውስጠኛ ክፍል ላይ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያስረዳል::

* በማርበርግ ቫይረስ የተያዘ ሰው ካገገመ በኋላ እስከ ሰባት ሳምንታት ድረስ በዘር ፈሳሹ ላይ በተደረገ ምርመራ ቫይረሱ እንዳለበት ተረጋግጧል። በመሆኑም ሁለት ጊዜ  በምርመራ ቫይረሱ በዘር ፈሳሽ ውስጥ አለመኖሩ አስኪረጋገጥ ድረስ ኮንዶም እንዲጠቀሙ ይመከራል:: የወንድ የዘር ፈሳሽ ምርመራ ፕሮግራም በማይኖርበት ጊዜ ከበሽታው የተረፉ ወንዶች ለ12 ወራት ጾታዊ ግንኙነት መፈጸም ያለባቸው በኮንዶም ብቻ ነው::

 

ምንጭ፡- የዓለም የጤና ድርጅት

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሕዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here