እንዴት ሰነበታችሁ ልጆች?ትምህርታችሁንስ በአግባቡ እየተከታተላችሁ ነው? መልካም! በዚህ ሳምንት በባሕር ዳር ከተማ በአየለች ደገፉ መታሰቢያ ትምህርት ቤት (ADMA) ከሚማሩት የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች ውስጥ አንዷ ከሆነችው ከማርካን ….. ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል፡፡
ማርካን በትምህርቷ በጣም ጎበዝ የሆነች ልጅ ናት፤ዘንድሮ ከክፍሏ አንደኛ ደረጃ በመውጣትም ጉብዝናዋን አስመስክራለች፡፡ማርካን ከትምህርቷ በተጨማሪ ድምጻዊነት፣ሥነ ስዕል እና የቴኳንዶ ስፖርት ላይ ልዩ ትኩረት ታደርጋለች፡፡በተለይም በቴኳንዶ ስፖርት ከነጭ ቀበቶ አልፋ ሰማያዊ ቀበቶ ላይ ደርሳለች፡፡
ማርካን የቴኳንዶ ስፖርት ለመልካም ሥነ ምግባር እና ራሷን ከጥቃት ለመከላከል እንደሚያበቃትም ገልጻልናለች፡፡“በቴኳንዶ ስፖርት አሰልጣኞቼ፣ከስፖርት ይልቅ ለትምህርቴ ልዩ ትኩረት እንድሰጥ ተመክሬያለሁ” የምትለው ማርካን የቴኳንዶ ስፖርትን ከትምህርቷ በማይጋጭ መልኩ እንደምትሰለጥንም ነው የነገረችን፡፡
ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በተደረገ የሕጻናት የቴኳንዶ ውድድር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማግኘቷን የገለጸችው ማርካን የጥናት ፕሮግራም አውጥታ ስለምታጠና፣ስፖርቱንም ሆነ ሌሎች ተሰጥኦዎቿን ለመሞከር እንዳልተቸገረችም ገልጻልናለች፡፡
ማርካን አቅሟ በፈቀደ መጠን ወላጆቿንም በሥራ ታግዛቸዋለች፡፡ወደፊት የልብስ ዲዛይነር እና የሕክምና ዶክተር መሆን የምትፈልገው ማርካን አሁን ላላት ጥሩ የትምህርት ውጤት እና የቴኳንዶ ስፖርት ውጤታማነት ወላጆቿ፣አስተማሪዎቿ እና የስፖርቱ አሰልጣኞቿ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱም ገልጻልናለች፡፡
ልጆች፣ማርካን በትምህርቷ እና በቴኳንዶ ስፖርት ውጤታማ ለመሆኗ በፕሮግራም መመራቷ እንደጠቀማት ነግራናለች፤እናንተስ ከማርካን ምን ተማራችሁ?ከትምህርታችሁ በተጨማሪ ላሏችሁ ተሰጥኦዎችስ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ካልሆነ ከማርካን ብዙ ነገሮችን ትማራላችሁ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ልጆች፣ሳምንት በሌላ መጣጥፍ እስክንገናኝ ድረስ መልካሙን ሁሉ እንመኝላችኋለን፡፡
(መሰረት ቸኮል)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም