የማስታወቂያ ስራ በአሁኑ ግዜ ለሀገራችን የሚሰጡ ጠቀሜታ ትልቅ አስተዋጾ እንዳለው ይታወቃል:: በተለይም በአሁኑ ሰዓት ቁጥሩ እየጨመረ ለመጣው ሥራ አጥ፤ በሙያው ተሰማርቶ ሰሪና አሰሪ እንዲገናኝ የሚያደረገው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ እንደሆየ ይታወቃል::
ለዚህም ነው በቴሌቨዥን፣ በቴሌግራም፣ በፌስ ቡክ፣ በማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ መልክቶች ሲተላፍ የምናየው። ለመግቢያ ያክል ስለጠቀሜታዎቹ በትንሹ ይህን ያህል ከገለፅሁ በዚህ ዙሪያ ስዘዋወር የተመለከትኳቸውን የማስታወቂያ አለጣጠፍ /አቀማመጥ/ የታዘብኩትን በትንሹ ላካፍላችሁ ወድጃለሁኝ::
እንግዲህ ከላይ የተጠቀስሁት እና ሌላም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የማስታወቂያ ሥራዎች በአግባቡ ባለመለጠፋቸው ምክንያት በሀገራችን ብሎም በክልላችን ላይ የአካባቢን ገፅታ በማበላሸት ላይ ይገኛሉ። ለአብነት ያህል ለመጥቀስ፤ የራስን ጥቅም ብቻ በማስቀደምና በአካባቢያችን ላይ የማፈጥረውን የገፅታ ግንባታ ወደኋላ በመተው የማስታወቂያ ጋጋታዎች በየመብራት ፖሉ፣ በግለሰሶች የመግቢያ በር ሥር፣ የስልክ ሳጥኖች /ተርሚናሎች/ ላይ፣ በተንቀሳቃሽና ተንቀሳቃሽ ባልሆኑ ዕቃዎች ተለጠፈው ይታያሉ::
እንዲሁም በየመዝናኛ ክበቡ እና ሌላው ቀርቶ በአስፓልት ዳር ላይ ለቆሻሻ ማጠራቀሚያ ተብለው በተተከሉ ላይ ወ.ዘ.ተ ሳይቀር እንደፈለጉና በማን አለብኝነት ተለጣጥፈው እናያቸዋለን። ሌላውና አስገራሚው በህንፃዎች ደረጃ ሳይቀር ተለጥፈው በማየቴ ምን እየሆነ እንዳለ ግራ ተጋብቼ አለሁኝ ለአብነትም፣ ቁጭት ገበያ አዳራሽ፣ አገዳና ምርቶች የገበያ ማዕከላት ላይ፣ እንዲሁም ወደ ገጠር መንገድ መሳፈሪያው (ታክሲ መያዥው) ባለው የሞባይል አክሰሳሪ መሸጥና፣ ጥገና ክፍሎች የመውጫ ደረጃውችን መመለከት ብቻ በቂ ይመስለኛ::
እንደኔ ሀሳብ ከሆነ ለምን መልእክቶች ተላለፉባቸው የሚለው ሳይሆን መልክት፣ የምናስተላልፍባቸውን ቦታዎች ለይተን አለማወቃችንና ገና ለገና የሰው ክምችት አለበት በሚል ብቻ እንዲህ አይነት አሰራሮች እየተለመዱ መሄዳቸው ከቀን ወደቀን ግራ የሚያጋባ ሁኔታ እየሆነ መቀጠሉ ነው:: ለቀጣይስ? የሚለው ለማሰብ ተገቢ ነው። ትኩረት ቢሰጠው መልካም ይመስለኛል እላለሁኝ እናንተስ?
ሌላውና አስገራሚው ደግሞ የግለሰቦች ቤት ላይ (በር ላይ) ማስታወቂያዎች የመለጠፋቸው ጉዳይ ነው። በሚለጠፉበት ወቅት ደግሞ መብታቸውን እየጣስን መሆኑን ለይተን አለማወቃችን ነው። ያለአግባብ ማስታወቂያዎችን ያለ ፍቃድ መለጠፍ ብዙም የሚያስጠይቅ ባለመሆኑ እንደልምድ ተይዟል። ይህም እኔን በጣም አሳዝኖኛል:: ለዚህም የመፍትሄ አቅጣጫ ከሁላችንም ይጠበቃል ባይ ነኝ::
ችግሩ ተባብሶ እንዲቀጥል ያደረገው ደግሞ በሕጉ መሰረት የሚከለክል አልያም አስተማሪ የሆነ ቅጣት የሚወስድ አካል ባለመኖሩ ነው:: ህብረተሰቡም ለመንግሥት ድጋፍ አለማድረጉንና ቸልተኝነት ማሳየቱ ለዚህም በቤቱ በር ላይ ሲለጠፍ እንኳን ለምን ብሎ አለመጠየቁና መብቱን አለማስከበሩ ምክንያቱ ይህ ነው:: ሌላው በየከተሞች የተለያዩ የማስታወቂያ መለጠፊያ ቦታዎችን በማዘጋጀት አስራሩ በህጋዊ መንገድ እንዲቀጥል ማድረግ አለመቻሉ ነው። ማስታወቂያ መለጠፊያ ቢዘጋጅ በአግባቡ የሚለጥፍ ሰራተኛን ይፈጥራል:: ይህ ደግሞ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደማለት ነው:: ሕብረተሰቡም ማስታወቂያዎች ህግን ባልተከተለ ሁኔታ ሲለጠፉ በሚያይበት ጊዜ ከተቻለ ለማስቆምና ሕጋዊነትን እንዲከተሉ ማድረግና ማስተካከል ይጠበቃል እላለሁ።
ሌላው ደግሞ እነዚህን የተዝረከረኩ ማስታወቂያዎች አግባብነት በሌለው ቦታ ላይ ሆነን ስንመለከት ሀሳባችን መሰረቁን የሚያዩ እና እነሱም አንባቢ መስለው ነገር ግን የእጅ ቦርሳ እንዲሁም ኪሳችንን የሚፈትሹ ሊኖር ስለሚችሉ መጠንቀቅ ይበጃል እላለሁ። እንዲሁም ከጤና አንፃርም በአካባቢው በርካታ ሰው ተሰብስቦ ስለሚቆም በትንፋሽ አማካኝነት የሚመጡ ቀላል መስለውም ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደማይድን በሽታ ሆነው ይከሰታሉ::
ለዚህም ጤናችንን በቀላሉ እናጣለን ማለት ነው:: ስለዚህ ጠንቀቅ እንበል እላለሁ ሌላውና ዋና የወቅቱ ችግር እየሆነ በመጣውና የሰው ልጅ ቀጣፊ፣ በሆነው የትራፊክ አደጋም ተጋላጭ መሆናችንን ማሰብ ይገባል::
እንዲሁም እነዚህ ማስታወቂያዎች ከላይ እንደጠቀስኩት አግባብ ባልሆነ ቦታ ላይ በሚለጠፉበት ግዜም፤ ግለሰቦች ሆነ ብለውና ጨለማን ተገን በድረግ መቅደድ ወይም ማበላሸት ሆነ ብለው ስርዝ ድልዝ የማድረግ፣ በአቧራና ዝናብ በመሳሰሉት ስለሚበላሹ በዚህ ምክንያት ሰሪና አሰሪ የሚባሉት ሁለት አካላት ሳይገናኙ መቅረታቸው ደግሞ ሌላኛው ራስ ምታት ነው::
በመጨረሻም በመንግሥት በኩል በተለይ የግንዛቤ ፈጠራ የሚሰጥበትን ሁኔታ እንዲመቻች ቢደረግ። እንዲሁም ነገ ዛሬ ሳይባል በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ቅጣት ቢተላለፍ የተሻለ ለውጥ ይምጣል ባይ ነኝ::
ሕብረተሰቡም ለዚህ ትብብርና ድጋፈ በማድረግ ውብና ፅዱ ዘመናዊ የሰለጠነ ከተማን መፍጠር ይጠበቅበታል ባይ ነኝ:: እንደ ዜጋም ቢሆን ሀገር የጋራ በመሆኗ ተቆርቆሪ ነታችንን ልናበዛው ይገባል አላለሁኝ ለዛሬ በዚህ አበቃሁኝ:: ለቀጣይ በሌሎች የትዝብት ፅሁፍ እስከምንገናኝ መልካም ጊዜ ይሁንላችሁ እላለሁኝ የዘወትር ደንበኛችሁ::
ዳንኤል ሙሉጌታ ነኝ ከባህርዳር
በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም