“የማይታየዉ  ፈረስ” ስንብት

0
23

የዓለማችን እግር ኳስ  ካስመለከታቸው ድንቅ አማካዮች መካከል አንዱ ስፔናዊው ሰርጅዮ ቡስኬትስ ነው:: የአማካይ ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ቡስኬትስ ከሰሞኑ ከእግር ኳስ ተጫዋችነት በፈረንጆቹ 2025 መጨረሻ ላይ እንደሚገለል አሳውቋል:: 20 ዓመታትን በአስገራሚ የጨዋታ መንገድና ክብሮች ያሳለፈው ስፔናዊ በክለብ ደረጃ በባርሴሎና፤ በሀገር ደግሞ ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ጋር የማይረሳ ታሪክ ፅፎ የመጨረሻ ጊዜ ላይ መድረሱን በማህበራዊ ሚዲያ ባሰራጨው አጭር የተንቀሳቃሽ ምስል መልእክት ሲያሳውቅ  “አሁን ከምወደው ሙያ ለመሰናበት ጊዜው ደርሷል::  20 ዓመታትን ልረሳቸው በማልችላቸው ስኬቶችና ትዝታዎች አሳልፌያለሁ::

በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ከኔ ጋር የነበራችሁትን ሁሉ አመሰግናለሁ” ነበር ያለው:: በዚሁ ተንቀሳቃሽ ምስል መልእክቱም አሁን እየተጫወተበት ያለው ኢንተር ሚያሚ ከስፔን ውጪ እንዲጫወት የሰጠው እድል ልዩ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ የሜጀር ሊግ ሶከር ውድድር በወርኃ ታህሳስ ሲጠናቀቅ ቡስኬትስና የእግር ኳስ ተጫዋችነቱ የተዋሃዱትን ያህል እህል ውሃቸው እንደሚያበቃለት ግልጽ አድርጓል::

የ38 ዓመቱ አማካይ 18 ዓመታትን ባሳለፈበት ባርሴሎና ዘጠኝ የላሊጋ፣ ሶስት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ክብርን ጨምሮ በስፔን የሀገር ውስጥ ውድድር በአውሮፓና በዓለም ደረጃ የሚዘጋጁ የክለብ ውድድሮችን ሁሉ አሸንፏል:: ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ጋር ደግሞ የ2010 የዓለም ዋንጫና የ2012ቱን የአውሮፓ ዋንጫም አሸንፏል:: በአጠቃላይ በእግር ኳስ ተጫዋችነት ህይወቱ 36 ዋንጫዎችን በማሸነፍ አይረሴ ታሪክን ፅፏል::

በስፔን ካታሎኒያ ግዛት ሳባዴል የተወለደው ተጫዋቹ የባርሴሎና ወጣት ቡድንን ከ20 ዓመት በፊት የተቀላቀለበትን ጊዜ የተጫዋችነት ዘመኑ ዋነኛ መነሻ አድርጎ ይወስደዋል:: በሁለት ዓመት የወጣት ቡድን ቆይታውም በዚያን ጊዜ የቡድኑ አሰልጣኝ የነበሩት ፔኘ ጋርዲዮላን ቀልብ ሳበ:: በ2008 እ.አ.አ ከሬሲንግ ሳንታንዴር ጋር በተደረገ ጨዋታ የ90 ደቂቃ የጨዋታ እድል ተሰጥቶት ሲጫወት ብዙዎች በፔኘ ደፋር ውሳኔ ተገርመው ነበር::

አሰልጣኙን ጨምሮ የክለቡ አመራሮች የጣሉበት እምነት ግን ወደ ዋናው ቡድን ባደገበት ዓመት 80 ሚሊዮን ዩሮ የውል ማፍረሻ ዋጋ ያለው የውል ማራዘሚያ እንዲፈራረም አስችሎትም ነበር::  ይህ ዋጋ በወቅቱ ዓለምን ያነጋገረም ነበር:: “ገና በለጋ እድሜ ያለ ተጫዋች እንዴት ይህን ያህል ዋጋ ይቀመጥለታል” በሚል! ሆኖም ግን የተሰጠውን እድል በአግባቡ በመጠቀም እንደሰይዱ ኬይታና ያያ ቱሬን የመሳሰሉ አማካዮችን በልጦ የካታሎኑ  ክለብ የልብ ትርታ ሆነ::

በአጫዋወት መንገዱ ኳስ መንጠቅ፤ የተቃራኒ ቡድን ሽግግርን ማቋረጥና ለቡድኑ ወደ ማጥቃት ሽግግር በመቀየር የለየለት ተጫዋች ነበር:: በብሔራዊ ቡድን ያሰለጠኑት ሺሴንቴ ዴልቦስኬ “እኔ አሁን ተጫዋች የመሆን እድሉ ቢኖረኝ ቡስኬትስን መሆን ነው የምመኘው” ሲሉም መስከረውለት ነበር::

በባርሴሎና 32 ዋንጫዎች ያሳካው ሰርጅዮ ቡስኬትስ ከሁሉም ድሎቹ መካከል ማንቸስተር ዩናይትድን በመርታት ያሸነፉበት የ2009ኙ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ድል እርካታ ያገኘበት መሆኑን ገልፆ ነበር::

ምክንያቱ ደግሞ የአባቱን ድል የተጋራበት መሆኑ ነው:: በአውሮፓ የክለቦች ውድድር ታሪክ አባትና ልጅ ሆነው በተመሳሳይ ክለብ በመጫወት ዋንጫ ያሳኩ ሦስት ብቻ ናቸውና ነው:: የዛሬ ባለታሪካችን ሰርጅዮ ቡስኬትስና አባቱ ቻርለስ በባርሴሎና፣ ሴዛርና ፓውሎ ማልዲኒ በኤሲ ሚላን እንዲሁም ማኑኤል ሳንቸስና ማኖሎ ሳንቸስ በሪያል ማድሪድ::

“የማይታየው ፈረስ” የሚል መጠሪያ በብዙዎች የሚሰጠው ቡስኬትስ በጨዋታ መንገዱ ዓይነግቡ ባይሆንም እርሱ የሌለ ቀን “ባርሳ፤ ባርሳ አይመስልም”ም ይባላል:: ምክንያቱም የተከላካይና የአጥቂ ስፍራን ሚዛን በመጠበቅ ወሳኝ በመሆኑ ነበር:: 700 ጨዋታዎችን ካደረገበት ባርሴሎና ጋር በ2023 የተለያየው አማካዩ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በአሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር ተፎካካሪው ኢንተር ሚያሚ እየተጫወተ ይገኛል::

በዚያም የባርሴሎና የቀድሞ ተጫዋቾች ሊዮኔል ሜሲ፣ ሊዩስ ሱዋሬዝና ጀርዲ አልባ የሚገኙ ሲሆን አሰልጣኙ ደግሞ ለተወሰኑ ዓመታት በባርሴሎና አጣማሪው የነበረው ሀቪየር ማሻራኖ ነው:: የሰርጅዮ ቡስኬትስን ውሳኔ ከሰማ በኋላም  “እርሱ  ያላሳካው ነገር የለም:: ከእግር ኳስ ተጫዋችነት ራሱን ቢያገልም፤ በእርግጠኝነት አሰልጣኝ ሆኖ ይመለሳል:: ምክንያቱም እውቀቱም ይሁን አቅሙ አለውና!” ሲል መስክሮለታል::

የብዙዎች ምርጫ፤ ሜዳ ውስጥ ከኳስ ጋር ከመነጋገር ውጪ ምንም አያውቅ፤ አመለ ሸጋ ነው የሚባልለት ቡስኬትስ “የማይታየው ፈረስ” ከወርኃ ታህሳስ በኋላ በሜዳ ላይ በተጫዋችነት የማንመለከተው ይሆናል::

 

(እንየው ዘላለም)

በኲር የመስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here