የማይከሰሱት አጥፊዎች

0
77

በአሜሪካ ማሳቹሴት ከተማ ከ25 የሚበልጡ የተሽከርካሪዎች መስታዉት በቀጣናው በሚገኙ ባለጉትዬ ግንደቆርቁር ወፎች ምንቃር መሰባበሩን ዩፒ አይ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል::

የቀጣናው ኗሪ ጃኔል ፋቫሎሮ ስለሁነቱ በተሽከርካሪው ውስጥ እንደተቀመጠች በፊት ለፊት የመስታዉት ማፅዳጃ ላይ ግንደ ቆርቁር ወፉ አርፎ (ተቀምጦ) አንፀባራቂ መስትወቱን ሲሰባብር  ስለ መመልከቷ እማኝነቷን ሰጥታለች::

ጃኔል ፋቫሎሮ ግንደ ቆርቁሮቹ  ከስምንት እስከ 24 ኢንች ቁመት፣ በጥቁር እና ነጭ ላባ የተዋቡ፣ በአናታቸው ላይ ጉትዬ ወይም ቁንጮዋቸው ከፍ ብሎ መቆፈሪያ ወይም መሰባበሪያ ምንቃር ያላቸው ስለመሆኑም በማህበራዊ ሚዲያ በፅሁፍ አጋርታለች::

የቀጣናው ከፊሎቹ ኗሪዎች ተሽከርካሪያቸውን ሲያቆሙ መስታዉቱን አንፀባራቂ፣ መከለያ ካርቶን ወይም በመጠቅለያ ወረቀት በመሸፈን ከግንደ ቆርቁሮቹ ለመከላከል መሞከራቸው ነው የተገለፀው – በድረ ገጹ::

 

ማይክ ሮስተር የተሰኘው የቀጣናው ኗሪ በበኩሉ በፒክአኘ መኪናው ውስጥ እንደተቀመጠ ከአሽከርካሪው በተቃራኒ ባለው የፊት መስታዉት መጥረጊያ ላይ አርፎ ከውጪ ወደ ውስጥ ግንደ ቆርቁሩ እየመታ ሲሰባብር  መደናገጡን አብራርቷል::

ስለ ግንደ ቆርቁሮቹ እና አውዳሚ ድርጊታቸው መነሻ ምክንያት እና ውጤት በብራውን ዩኒቪርሲቲ የስነ ምህዳር እና የስነ ህይወት ዝግመት ለውጥ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ስራመሪው ማቲው ፋክስጃገር ሁነቱ ከዓእዋፉ የመራቢያ ወቅት ጋር እንደሚገናኝ ነው ያሰመሩበት::

ተባባሪ ስራ መሪው ግንደ ቆርቁሮቹ መራቢያ ወይም አጣማጅ መፈለጊያ ወቅታቸው በመሆኑ በአንፀባራቂ መስታዉቱ የሚያዩትን የራሳቸውን ምስል እንደ ተቀናቃኛቸው በመውሰድ ጥቃት እንደሚፈፅሙ ነው ያብራሩት::

በመጨረሻም ተሽከርካሪዎች ሲቆሙ መስታዉቱን በካርቶን፣ በስስ ወረቀት ወይም መጋረጃ ጨርቅ ማልበስ ተገቢ መሆኑን በመግለጽ ነው ያደማደሙት ተባባሪ ዳይሬክተሩ::::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here