የማዳበሪያ ንግድ እና  አዋጅ

0
87

እ.ኤ.አ በ1908 “the father of chemical warfare” እየተባለ የሚጠራው ጀርመናዊ ሳይንቲስት ፍሪትዝ ሀርበር ለመጀመሪያ ጊዜ የአፈር ማዳበሪያ ቀምሞ  በፋብሪካ ማምረት ጀመረ፡፡ ማዳበሪያ የዓለም እጅግ ወሳኝ ሰትራቴጅካዊ ሸቀጥ ነበር፡፡  የአፈር ማዳበሪያው ምርታማነትን በመጨመሩ ሳይንቲስቱ እ.አ.አ 1918 የሰላም የኖቬል ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ ማዳበሪያ በምርት ውጤት ላይ ያስገኘውን እድገት ተከትሎም  የዓለማችን እጅግ ውድ እና ጠቃሚ   ሸቀጥ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን ይህን ውድ የዓለማችን የአፈር ማዳበሪያ ቅኝ ገዥዎች ለእርሻ ስለሚፈልጉት ለማግኘት ይማስኑ እንደ ነበር መረጃዎችን ዋቢ አድርገው በአማራ ክልል የፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አቃቢ ሕግ አቶ ዓለምነህ እሸቴ ገለጻ ያስረዳል፡፡ እንደ ባለሙያው ማስረጃ በ1950 ዎቹ አጋማሽ አንድ ኩንታል ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ እንደ ሀገራቱ መገበያያ ገንዘብ አንድ ፓውንድ፣   76 ዶላር… ይሸጥ ነበር፡፡

የሀገሪቱ 80 ከመቶ ሕዝብ በግብርና ዘርፍ የተሰማራባት ኢትዮጵያም  እ.አ.አ በ1960 ማዳበሪያ መጠቀም ጀምራለች፡፡ የአፈር ማዳበሪያ  2ኛውን ወይም ከ45 ከመቶ በላይ የሆነውን የሀገር ውስጥ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ (GDP)  85 ከመቶ እና  የሀገሪቱን የውጭ ንግድ  80 ከመቶ እንደሚያሳድግ እንዲሁም  የሥራ እድል  እንደሚፈጥር የወርልድ ባንክ 2012 (World Bank 2012) መረጃ አመላክቷል፡፡

የኢኮኖሚ ጉዳዮች አቃቢ ሕግ አቶ ዓለምነህ እሸቴ የማዳበሪያ ጉዳይ ከሀገራት አልፎ ዓለምን የሚንጥ ከባድ የፖለቲካ አጀንዳ ጭምር መያዙን ያመላክታሉ፡፡ በዚህም  ከማዳበሪያ አምራች ሀገራት ጀምሮ ሌሎችም የዓለምን የማዳበሪያ አቅርቦት እና ግብይት እስከመወሰን ድረስ ባለው ሂደት ይፋለማሉ፡፡  በሀገራችንም ሆነ በክልል ደረጃ የአፈር ማዳበሪያ ለፖለቲካ መጠቀሚያነት ሲውል እንደሚስተዋል ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

አትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለግብርናው ዘርፍ በሰጠችው ልዩ ትኩረት  እያደገ የመጣውን የአርሶአደሩን የማዳበሪያ ፍላጎት ለማሟላት በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረት ቢያደረግም እስከ ዛሬ ማሳካት አልተቻለም፡፡ ይሁን እንጅ በየዓመቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ  በመመደብ ከዓለም ገበያ ከምታስገባቸው ሸቀጦች አንዱ ማዳበሪያ ነው፡፡

የኢኮኖሚ ጉዳዮች አቃቢ ሕግ አቶ ዓለምነህ እሸቴ እንዳሉት መንግሥት በዚህ ዓመት ብቻ ለማዳበሪያ መግዣ 84 ቢሊዮን ብር ገደማ ድጎማ አድርጓል፡፡  19 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያም ግዥ ተፈጽሟል፡፡ የክልሉ መንግሥት በበኩሉ  ለምርት ዘመኑ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ሰው ሠራሽ  የአፈር ማዳበሪያ  ለማቅረብ አቅዶ  በማስገባት ላይ ይገኛል፡፡  ለዚህም ከ79 ቢሊዮን ብር በላይ ዋስትና ገብቷል፡፡ ይህ ክልሉ ከሚሰበስበው ዓመታዊ መደበኛ በጀት 71 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር ተቀራራቢ ነው፡፡

የአፈር ማዳበሪያ የአቅርቦት እጥረት ፣ መዘግየት፣ ዋጋው በዓለም ገበያ ላይ መጨመር፣  ሕገ ወጥ ግብይት እና ስርጭት ለመንግሥት እና ለአርሶ አደሩ  ፈተናዎች ናቸው፡፡  አርሶ አደሩ ማዳበሪያን በወቅቱ፣ በሚፈልገው ጥራት፣ መጠን እና በተወዳዳሪ ዋጋ ገዝቶ ምርታማነቱን ለማሳደግ እንዲችል የአቅርቦት ሥርዓቱን የሚያቀላጥፍና ወጭን የሚቆጥብ አሠራር መቀየስና ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የአቃቢ ሕግ ባለሙያው አቶ ዓለምነህ እሸቴ  ተናግረዋል፡፡

ታዲያ ግብይቱ እና ስርጭቱ ለግብርናው ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት በሚችልበት ትክክለኛ አቅጣጫ ለመምራት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ሕጎች ተቀርጸው ሥራ ላይ መዋላቸውንም ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ ማዳበሪያ የማምረትና የንግድ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 137/91 አንዱ ነው፡፡

እንደ አቶ ዓለምነህ ማብራሪያ አዋጁ ዘመናዊ የሆነ የግብይት ሥርዓትን የዘረጋ ሲሆን እሱን ተከትለው የወጡ መመሪያዎችም ይህን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል ድንጋጌዎችን ይዘው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

 

አዋጁ ማዳበሪያ የማምረት፣ የማስመጣት፣ የመላክ፣ የማጓጓዝ ፣የማከማቸት ፣የመግዛት እና የመሸጥ ሂደትን በሙሉ የሚያጠቃልል ነው፡፡ ስለሆነም አዋጁ በዚህ የግብይት ሂደት ውስጥ ተፈፃሚነት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ አዋጁ የማዳበሪያ ግብይት በነጻ ገበያ የሚመራበትን ሥርዓት ቢዘረጋም መንግሥት በከፍተኛ ድጎማ የሚያመጣው መሆኑን ተከትሎ የአቅርቦት እና የስርጭት አሠራሩ አዋጁን ተከትለው በወጡ መመሪያዎች ተፈጻሚ እየተደረገ ነው፡፡ የማዳበሪያ አዋጁን ለማውጣት ያስፈለገበትን  ምክንያት ዐቃቢ ሕግ ባለሙያው ሲዘረዝሩ፦

       የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት መሰረት የሆነውን ግብርናን በዘመናዊ የእርሻ ሳይንስና በምርት ግብዓቶች ለማጎልበት፤

       ወቅታዊ አቅርቦቱን፣ ጥራቱን፣ ግብይቱን፣ በተፈለው ቦታና መጠን መሰራጨቱንና መሸጡን ለመከታተልና ሥርዓት ለማስያዝ፤

       ማዳበሪያ ልዩ ጥንቃቄ የሚሻ ኬሚካላዊ ቁስ በመሆኑ በአመራረት፣ በማስመጣት፣ በአያያዝና በማከማቸት ደረጃውን የጠበቀ ለመሆኑ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ፤

       ማዳበሪያ የሚያመርቱ ፣ የሚያስመጡ ፣ የሚሸጡና የሚያሰራጩ ግለሰቦችን /ድርጅቶችን/ የሚያግዙ ፣ የሚያማክሩ፣ የሚቆጣጠሩ መንግሥታዊ አካላትን መሰየም፣ የገበያ ሥርዓቱን በሚፈለገው አቅጣጫ ለመምራት ተገቢውን ድጋፍ እንዲሰጡ፣  የቁጥጥር ሥራ እንዲሠሩ እና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ ግብርና ቢሮ  የግብርና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥር ኳራንታይን ባለሥልጣን ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡

በማዳበሪያ ግብይትና ሥርጭት ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉት አምራቾች፣ አቅራቢዎች፣ ላኪዎች አስመጭዋች፣ አጓጓዦች፣ አከማቾች፣ ጅምላ አከፋፋዮች፣ ቸርቻሪዋች እና አሰራጮች በወንጀል የሚያስጠይቁ ግዴታዋች በአዋጁና አዋጁን ለማስፈፀም በወጡ መመሪያዎች ስር በዝርዝር ሰፍረዋል፡፡

 

በማዳበሪያ ማምረትና ንግድ አዋጅ ቁጥር 137/91 አንቀጽ 26 በወንጀል የሚያስጠይቁ ግዴታዋች ተብለው የሰፈሩት እያወቀ የተበከለ ወይም ያልተመዘገበ ማዳበሪያ መሸጥ ወይም ለሽያጭ ማቅረብ፣  ደረጃውን ያላሟላ ማዳበሪያ መሸጠ ወይም ለሽያጭ እያወቀ ማቅረብ፣  የቀረጢት ሥራው ደረጃውን ያልጠበቀ መሆኑን እያወቀ ማዳበሪያ መሸጥ ወይም ለሽያጭ ማቅረብ፣  በቀረጢቱ ላይ ያለው ምልክት እና የቀረጢቱ አስተሻሸግ ደረጃውን ያልጠበቀ ማቅረብ፣ በቀረጢቱ ውስጥ ያለው ማዳበሪያ ከተፈለገበት ዋጋ ያነሰ ማዳበሪያ መሸጥ ወይም ለሽያጭ ማቅረብ፣ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ተቆጣጣሪዋች አለመተባበር፣ መሰናክል መፍጠር እና የተሳሳተ መረጃ መስጠት እንዲሁም  የታሸገ መገንጠል ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በማዳበሪያ ግብይት የተሰማራ ሰው በአዋጁ አንቀጽ 29፣ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 እና በንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ 813/2006 የተመላከቱትን ድንጋጌዎች ከተላለፈ   በወንጀል ይጠየቃል፡፡

 

ይሁንና በሀገራችን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የአፈር ማዳበሪያን ወደ ሀገር ውስጥ በብቸኝነት የማስገባት እና የማሰራጨት ሥራው የሚከናወነው በገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት እና በዩኒየኖች አማካኝነት በመሆኑ በአዋጁ የተመለከቱ የማዳበሪያ ግብይት አዋጅ ተግባራዊ አይሆንም፡፡  በክልላችን የአፈር  ማዳበሪያ ሥርጭት የሚፈጸመው ጥር 2008 ዓ.ም በጸደቀው የአብክመ ኩፐን ሥርዓት የግብርና ግብዓት ሽያጭ በተሻሻለው የአፈጻጸም መመሪያ ነው፡፡

በዚህም የአፈር ማዳበሪያ ስርጭቱ የአርሶ አደሩን ፍላጎት በባለሙያ በማረጋገጥ በግብርና ቢሮ በየደረጃው በሚገኝ መዋቅር በሚሰጥ ፈቃድ ከማህበራት ወይም ዩኒየን ግዥ ይፈጸማል፡፡ በክልላችን የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭትና ግብይት እንቅስቃሴ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ተጠያቂነት በማረጋገጥ ረገድም የተለያዩ መ/ቤቶች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ፍርድ ቤት ፣ ድጋፍ ሰጭ እና ተቆጣጣሪ ተቋማት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ እነዚህ ተቋማት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በተናጠል እና በጋራ በቅንጅት ጥረት ቢያደረጉም የአፈር ማዳበሪያ ስርጭትን በሚፈለገው ልክ ሥርዓት ማስያዝ አልተቻለም፡፡ የክልሉ ግብርና ቢሮ በ2015 ዓ.ም በአማራ ክልል ከ4ሽህ 648 ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር መያዙን አሳውቋል፡፡ አጥፊዋችንም ተጠያቂ በማድረግ እና በሕገ ወጥ መንገድ የተያዘውን የአፈር ማዳበሪያ በመውረስ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል፡፡  ይህን በግብአት ስርጭት ላይ የሚከሰት ሕገወጥ ዝውውር ለማስቆምም ሕዝብ ከመንግሥት ጎን ቆሞ ጥቆማ እንዲያደርስ የዘርፉ ባለሙያ ጠይቀዋል፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here