የምርት ብክነት ማለት በምርት ዘመኑ ሊገኝ ከሚገባው ምርት ውስጥ በአያያዝ እና በአሰባሰብ ሂደት በሚፈጠር ችግር ምክንያት መጠኑ ሲቀንስ ማለት ነው፡፡
በምርት ዘመኑ ሊገኝ የሚገባው የምርት መጠን ቀነሰ ማለት የምርት እጥረት ተከሰተ ማለት ነው፡፡ ይህ የምርት መቀነስ ደግሞ የዋጋ ግሽበትን ያመጣል፡፡
የዋጋ ግሽበት የሚባለው በተወሰነ የጊዜ መጠን ውስጥ የምርት እና አገልግሎቶች ዋጋ መጨመር ማለት ነው፡፡ ይህም በሚፈለገው ልክ ለገበያ ምርትን ማቅረብ ባለመቻል ይከሰታል፡፡ የእነዚህ ሁኔታዎች መከሰትም የኑሮ ውድነት ይባላል፡፡
እንደ ዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ የድህረ -ምርት ኪሳራ የሚለካው በመጠን እና ጥራት ላይ ያለው ብክነት ከምርት ጊዜ አንስቶ እስከ መጨረሻው የፍጆታ ደረጃ ድረስ ተለክቶ ነው። እነዚህ ኪሳራዎች የሚከሰቱት በሁሉም የድህረ -ምርት ሰንሰለት ደረጃዎች ማለትም ገና ከማሳ፣ ቀጥሎ ምርቱ ሲሰበሰብ እና የአያያዝ (የማከማቸት) ሂደትን፣ መጓጓዝን እና ግብይትን ያካትታል።
የድርጅቱ መረጃ እንደሚያመላክተው ደካማ አያያዝ እና የማከማቸት ልምዶች፣ የመሠረተ ልማት እጥረት፣ የሰብል በሽታ ዋናዎቹ የብክነት ምክንያች ሲሆኑ ከመነሻው ጀምሮ ጥራት የሌላቸው ዘሮች፣ በቂ ያልሆነ የግብርና አሠራር ወይም በመስክ ላይ ያሉ የነፍሳት ጥቃቶች ምርቱን ከመሰብሰባቸው በፊት መጥፋት ወይም ደግሞ ብክነትን በማስከተል ይጠቀሳሉ። ድርጅቱ የኪሳራ ምክንያቶችንም እንደሚከተለው በዘርፍ አስቀምጧቸዋል፡፡
የድህረ – ምርት ኪሳራ መንስኤዎች
አካላዊ ምክንያቶች፡- ተገቢ ባልሆነ አያያዝ ምክንያት የሚከሰት ጉዳት ነው፡፡
ስነ ሕይወታዊ ሁኔታዎች፡- የሚባሉት ደግሞ ተባዮች፣ ሻጋታ እና በማከማቻ ወቅት ሰብሎችን ሊጎዱ በሚችሉ በሽታዎች ምክንያት ምርቱ ላይ የሚከሰት ጉዳት ነው።
የአካባቢ ሁኔታዎች፡- ሰብሉ ከተሰበሰበ በኋላ ለዝናብ፣ ለፀሐይ እና ለእርጥበት መጋለጥ የምርት መበላሸትን እና ብክነትን ያስከትላል።
በማጓጓዝ ወቅት (ደካማ አያያዝ)፡- ምርቱ ከተሰበሰበበት ወደ ተጠቃሚ እስከሚደርስበት ሂደት በሚኖር ደካማ የማጓጓዝ ሥርዓት ከፍተኛ የምርት ብክነትን ያስከትላል። ለማድረቅ እና ለማቀነባበር የተስማሚ መሣሪያዎች እጥረትም ተጠቃሽ ናቸው።
የገበያ እና የአቅርቦት ሰንሰለት ችግሮች፡- የገበያ ተደራሽነት እጦት፣ የምርትና ስርጭት ቅንጅት ደካማ መሆን እና የዘመናዊ ማስቀመጫ ቦታ መሟላት አለመቻል በዚህ ውስጥ ይካተታሉ።
ብክነቱ የሚያስከትላቸው ጉዳች
ከላይ የተጠቀሱት የምርት ብክነት ምክንያች በርካታ መዘዞችን እንደሚያስከትል የዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ ያስገነዝባል፤ ዋናዋናዎቹም የሚከተሉት ናቸው፡፡
የምግብ አቅርቦት መቀነስ፡- ለምግብ ፍጆታ የሚሆን አነስተኛ መጠን ያለው ምግብ እንዲኖር ያደርጋል።
ዝቅተኛ ገቢ፡- ይህም በዋናነት አምራቹን በእጅጉ ይጎዳል፤ አርሶ አደሮች ሊያገኙት የሚችሉት ሰብል ይበላሻል ወይም ለገበያ በማቅረብ የሚያገኙትን ገቢ ያጣሉ።
የምግብ ዋጋ መጨመር፡- የምርት ብክነት ካ ገበያ ላይ የምርት አቅርቦት እጥረትን ያስከትላል፤ ይህም የምግብ ዋጋን ከፍ ሊያደርግ ስለሚችል ዋጋው ተመጣጣኝ እንዳይሆን ያደርጋል።
የምግብ ዋስትና ማጣት፡- ከፍተኛ ኪሳራ (ብክነት) የምግብ ዋስትና እጦትን እና የአመጋገብ ጉዳዮችን ያባብሳል።
የአካባቢ ተፅዕኖ፡- ምርትን ማባከን አላስፈላጊ የሃብት አጠቃቀምን እና አካባቢያዊ ጫናን ያስከትላል።
በአፍሪካ የምርት ብክነት (የአየር ንብረት ለውጥ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማነስና ሌሎች ጉዳዮች) በአህጉሪቱ ሕዝብ የምግብ ደህንነት ላይ እንቅፋት ሆኗል ተብሏል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በድህረ ምርት ወቅት 800 ሚሊየን ዜጎችን መመገብ የሚያስችል ምርት እንደሚባክን በ2017 ዓ.ም መገባደጃ ላይ ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደው ድህረ አፍሪካ ምርት ጉባኤ እና አውደ ርዕይ ወቅት ተነስቷል፡፡ በአፍሪካም ከሚመረተው ሰብል 30 ከመቶ በላይ እንደሚባክን ተጠቁሟል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ800 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም በአፍሪካ 278 ሚሊዮን ሕዝብ የረሃብ አደጋ በዚሁ በድህረ ምርት ብክነት ምክንያት ያጋጥማልም ነው የተባለው፡፡
ኪሳራውን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስልቶች
የተሻሻለ የአያያዝ ጉዳቱን ለመቀነስ ገበሬዎችን በአግባቡ ለመሰብሰብ፣ ለመደርደር እና ለማስቀመጥ ትክክለኛ መንገዶችን ከግብርና ባለሙያ እና ዓለም አቀፍ ልምዶችን በመጠቀም ማስተማር የሚለው በቀዳሚነት የተቀመጠ የድርጅቱ ምክረ ሐሳብ ነው።
በተገቢ ሁኔታ ምርቱን ማድረቅ፡- እርጥበትን ለመቀነስ እና የሻጋታ ጉዳትን ለመከላከል ለትክክለኛው ማድረቂያ መንገድ ወይም ዘመናዊ መሣሪያዎችን መጠቀም ይገባል።
የተሻሻሉ መጓጓዣዎችን መጠቀም ደግሞ ምርት ከማሳ ወደ ተጠቃሚ እስኪደርስ ባለው ሂደት የሚኖረውን ከፍተኛ ኪሳራ ያስቀራል፤ ለዚህ ደግሞ በተለይ መንግሥት በትኩረት መሥራት እንደሚገባው ነው የጠቆመው።
ማቀነባበር እና እሴት መጨመር፡- የቆይታ ጊዜን ለማራዘም እና ዕሴት የሚጨምሩ ምርቶችን ለመፍጠር እንደ ማድረቅ፣ ማቆር እና ማቀዝቀዝ ያሉ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ቴክኒኮችን በየአካባቢው መፍጠር ይገባል።
ወቅታዊ የገበያ መረጃ አርሶ አደሩ እንዲኖረው ማስቻል ሌላው ምክረ ሐሳብ ነው፤ የተሻለ የገበያ መረጃ እና ትንበያ አቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ ለመቀነስ የሚረዳ ነው፡፡ ይህም ብዙ ተመርቶ ፍላጎት በማጣት የሚባክነውንም ምርት ይቀንሳል፡፡
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት በኢትዮጵያ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነው የግብርና ምርት እንደሚባክን አሳውቋል። ምርቱ የሚባክነው በዋናነት ድህረ ምርት ስብሰባ ላይ መሆኑን ጠቅሷል፤ እነዚህ ኪሳራዎች በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳላቸውም ነው ያመላከተው።
በሀገራችን ወቅቱ የምርት ስብሰባ ነው፤ በመሆኑም ከላይ የተዘረዘሩትን የምርት ብክነት መከላከያ ምክረ ሐሳቦችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የድህረ – ምርት ጉዳይ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስቧል።
በተጨማሪም ጥናቱ የድህረ ምርት ብክነትን መቀነስ የሚያስችል በድህረ ምርት አያያዝ ተግባራት ላይ የአጭርና የረዥም ጊዜ ስልጠና በመስጠት፣ የድህረ – ምርት ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስተዋወቅ፣ ለተቋማዊ የድጋፍ ሥርዓቶች (የግብርና ኤክስቴንሽንና የገጠር ብድር አገልግሎቶችን) ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ ከምርት በኋላ የሚስተዋሉ የአያያዝ ሥራዎችን በማጠናከር፣ የአካባቢውን የገበያ ትስስርን በማጠናከር እና የመንገድ እንዲሁም የእርሻ መሠረተ ልማትን በማጠናከር የምርት ብክነትን መቀነስ እንደሚቻል ነው የያስቀጠው።
መረጃ
የምርት ብክነቱ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች
የምግብ አቅርቦት መቀነስ፣
ዝቅተኛ ገቢ፣
የምግብ ዋጋ መጨመር፣
የምግብ ዋስትና ማጣት፣
የአካባቢ ተፅዕኖ፣
የምርት ብክነትን ለማስቀረት የሚያስችሉ ምክረ ሐሳቦች፡-
በተገቢ ሁኔታ ምርቱን ማድረቅ፣
የተሻሻሉ መጓጓዣዎችን መጠቀም፣
ማቀነባበር እና እሴት መጨመር፣
ወቅታዊ የገበያ መረጃ አርሶ አደሩ እንዲኖረው ማስቻል!
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም