ጥናቶች እንደሚያሳዩት ምርት ከተመረተበት ቦታ ለተጠቃሚው እስከሚደርስበት ባለው ሂደት ከ35 በመቶ የሚደርስ የምርት ብክነት ይከሰታል፤ ይህ ደግሞ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ካለመጠቀም ባሻገር በተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት የሚከሰት ጭምር ነው፡፡
ወቅቱ የግብርና ምርቶች የሚሰበሰቡበት ነው፤ ይህም በግብርና ሥራው መጀመሪያ አካባቢ የተያዘው ዕቅድ (በአማራ ክልል) አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር በማረስ 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እና ለስኬታማነቱ ርብርብ የሚጠይቅበት ወቅት ነዉ፡፡
በሌላ በኩል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር የሳተላይት መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ የኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የምርት ብክነትን ሊያስከትል እንደሚችል ነው የተሰጋው፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ የገጠር ቀበሌዎች ከባድ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ በ500 ሄክታር ላይ የተዘራ የደረሰ ሰብልን ማውደሙ ተነግሯል፤ ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ የወደመባቸው አርሶ አደሮችም ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።
ኅዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ለ30 ደቂቃ የጣለው ከባድ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ነው በሦስት ቀበሌዎች ላይ የሰብል ውድመት ያስከተለው።
ጉዳቱ በተለያዩ የሰብል አይነቶች ላይ የደረሰ ሲሆን ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ እና ጥራጥሬ ሰብሎች ይገኙበታል።
ሰብላቸው የወደመባቸው አርሶ አደሮች እንደተናገሩት በአካባቢው ባሕል መሠረት ሰብላቸውን በደቦ ለመሰብሰብ እየተዘጋጁ በነበሩበት ወቅት ድንገት የጣለው በረዶ ሰብላቸውን ሙሉ በሙሉ አውድሞባቸዋል።
አቶ ራራ ደሴ የተባሉ የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ አርሶ አደር በደረሰው ጉዳት በማዘንና በመደናገጥ በርካታ አርሶ አደሮች ለከፋ የጤና ቀውስ መዳረጋቸውን አንስተዋል። ሌላው የጉዳቱ ሰለባ አርሶ አደር ማሬ ታረቀኝ “ጉዳቱ ያልተጠበቀ ነው፤ እንኳን እኛ እንስሳቱ የሚበሉት ድርቆሽ ሳር አልተረፈም” ብለዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ ጥላሁን ዓለም ለአሚኮ እንደገለጹት ከ600 በላይ አርሶ አደሮች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በፍጥነት መልሶ የማቋቋም ሥራ መሠራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።
የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ በዕውቀት አየነው የደረሰው ጉዳት ከባድ መሆኑን አንስተዋል፤ በመሆኑም አርሶ አደሮችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በመሥራት በበጋ መስኖ ሰብል ልማት ምርቱን እንዲያካክሱ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ኃላፊው በሌሎችም ቀበሌዎች ተመሳሳይ ጉዳት ሊያጋጥም ስለሚችል አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ ሊሰበስቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብሰብ እንደሚገባ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስትትዩትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት አሳስበዋል፤ ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ታዲያ የደረሱ ሰብሎቻቸውን እየሰበሰቡ መሆኑን ነግረውናል፤ ሰብላቸውን በደቦ (በጋራ) መሰብሰብ ደግሞ የተሻለ አማራጭ አድርገው እየተጠቀሙ ነው፡፡
ሐሳባቸውን በስልክ ያካፈሉን በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ኃይለማርያም አያሌው እንዳሉት የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ እና ሌሎችንም የግብርና ሥራዎች በወበራ (በጋራ) ማከናወን የተለመደ ተግባር ነው፤ በአሁኑ ወቅትም የደረሱ ሰብሎቻቸውን እየሰበሰቡ ነው፡፡
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስጋት ውስጥ እንዳስገባቸው የተናገሩት አርሶ አደሩ ከስጋት ነጻ ለመሆን ሰብሉን ከማጨድ ባለፈ በአግባቡ መከመር፣ በጊዜ መውቃት እና ብክነት ሳይኖር ለጎተራ ማብቃት እንደሚገባ ጠቁመዋል፤ እርሳቸውም ይህንኑ ተግባር እያከናወኑ መሆኑን አክለዋል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ ሐሳባቸውን ለአሚኮ የሰጡ አርሶ አደር ዋለልኝ አስራደ እንደተናገሩት ሩዝ የኑሯቸው መሠረት ነው።
በ2016/17 የምርት ዘመን በቂ የአፈር ማዳበሪያ እንዳገኙም አክለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማሳቸውን በአግባቡ እንደሚንከባከቡ በማንሳት በዓመቱም ከ10 ኩንታል በላይ ሩዝ የማግኘት ተስፋን ሰንቀዋል።
ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች እንዳሉት ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እና ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ስጋት ለመውጣት የእርሻ ትራክተር እና የሰብል መሰብሰቢያ ማሽን (በሰብል ስብሰባ ወቅት በዋናነት የምርት መሰብሰቢያ ማሽን ወይም ኮምባይነር) በተመጣጣኝ ዋጋ ሊቀርብላቸው ይገባል።
በተመሳሳይ በ2016/17 የምርት ዘመን ከሦስት ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን መምሪያው ገልጾ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እንዲሰበስብ አሳስቧል።
እንደ ዞኑ ግብርና መምሪያ አርሶ አደሮች ሰብላቸውን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ እና ከምርት ብክነት ለመጠበቅ ከግብርና ባለሙያዎች ጋር ተቀራርበው እየሠሩ ነው።
በምርት ዘመኑ ከ153 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም ከሦስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
አርሶ አደሩ ከማሳ ጀምሮ ምርት ጎተራ እስኪገባ ድረስ በጥንቃቄ በመሰብሰብ እና በማጓጓዝ የምርት ብክነትን መቀነስ እንደሚገባ መምሪያው አሳስቧል።
በሌላ በኩል ከሰሞኑ በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የግብርና ሥራዎችን መመልከታቸው ይታወሳል፤ በጉብኝቱ የተገኙት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ደጀኔ እንደተናገሩት በዞኑ 19 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል አጠቃላይ የሰብል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።
ፎገራ ወረዳ በተለይም በሩዝ ምርት እንደ ሀገር ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን አብነት ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው በተያዘው የምርት ዘመን በፎገራ ወረዳ ብቻ 72 ሺህ ሄክታር መሬት በሩዝ ሰብል ተሸፍኗል ብለዋል። ከዚህም 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንደተናገሩት በክልሉ በምርት ዘመኑ አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር ተሸፍኗል፤ በዚህም 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። የቅድመ ምርት ሙያዊ ግምገማ ውጤትን ዋቢ በማድረግም “በክልሉ ያለው የሰብል ግምገማ ያቀድነውን ዕቅድ ማሳካት እንደምንችል የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
የድኅረ ምርት ብክነት እንዳይኖር ሜካናይዜሽንን መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ቢሮ ኃላፊው፣ አርሶ አደሮች ገንዘብ ቆጥበው የሰብል መሰብሰቢያ ማሽን (ኮምባይነር) እየጠየቁ መሆናቸውን በማንሳት የአርሶ አደሮችን ፍላጎት ለማሟላት እየተሠራ ነው ብለዋል። በተመሳሳይ አርሶ አደሮች የምርት ብክነትን ለመቀነስ የደረሰ ሰብላቸውን በፍጥነት በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ማስቀረት (መቀነስ) እንዳለባቸው አሳስበዋል።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም