የምርት ብክነት – ትኩረት የሚሻዉ ወቅታዊ ጉዳይ

0
41

በአራተኛው ድህረ አፍሪካ ምርት ጉባኤ እና አውደ ርዕይ (2017 ዓ.ም መገባደጃ መካሄዱን ልብ ይሏል) የተነሳው መረጃ እንደሚያመላክተው በድህረ ምርት ወቅት 800 ሚሊዮን ዜጎችን መመገብ የሚያስችል ምርት ይባክናል፤ ይህም 10 በመቶ ያህሉን የዓለም ሕዝብ መመገብ የሚችል ነው:: በአፍሪካም ከሚመረተው ሰብል 30 ከመቶ በላይ የምርት ብክነት እንደሚከሰት ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች 305 ሚሊዮን (እ.አ.አ እስከ 2025 መጨረሻ) እንደሚደርስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ቅድመ ትንበያ ያሳያል:: ለዚህ ደግሞ የምርት ብክነትን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ፈተናዎች ከፍተኛ ድርሻ እንደሚይዙ ነው መረጃው የሚያመላክተው::

የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) በ2023 እ.ኤ.አ ባወጣው ሪፖርት ዓለም ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ባጋጠማት የተለያዩ ችግሮች ምክንያት በየዓመቱ 69 ሚሊዮን ቶን የግብርና ምርት ይታጣል::

ያደጉ ሀገራት ዘመናዊ የማረሻ፣ የመዝሪያ እና የመሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎችን ቢጠቀሙም ከእነዚህ ውጪ በሆኑ ምክንያቶች ግን አሁንም ለምርት ብክነት ፈተና እንደሆኑባቸው መረጃዎች ያሳያሉ:: በአፍሪካ ያለው የምርት ብክነት መንስኤ ግን ከሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች  በተጨማሪ የአመራረት ዘዴ ካለመዘመኑም ጋር የተገናኘ ነው::

በኢትዮጵያም የበጋ መስኖን ጨምሮ  አዳዲስ መሬቶችን ወደ ምርት በማስገባት፣ ዘመናዊ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችንም በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ ቢሆንም የምርት ብክነት እና የጥራት ጉድለት ግን የዘርፉ ፈተናዎች ናቸው::

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ በከብት እና በሰው ኃይል መውቃት፣ ለብክነት የተጋለጠ የመውቂያ ቦታ፣ በባሕላዊ መንገድ ምርትን ማከማቸት እና ተያያዠዥ ነገሮች ደግሞ የምርት ብክነት ዋና መንስኤዎች ሆነው ይነሳሉ::

የአማራ ክልል በ2017/18 የምርት ዘመን ያቀደውን 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፤ ዕቅዱን ለማሳካት ደግሞ የሰብል ስብሰባው ከብክነት ነጻ ሆኖ እንዲከናወን በትኩረት እየሠራ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል::

ዘግይቶ መሰብሰብ፣ ሰብልንም በዘመናዊ መንገድ አለመውቃት እና የአያያዝ ጉድለት  ደግሞ ዋና ዋና ምክንያች ስለመሆናቸው ነው ቢሮው ያመላከተው:: በመሆኑም የምርት ብክነትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሠራ ነው::

ነጋ ባንተይሁን በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሠማሩ አርሶ አደር ናቸው:: በተያዘው የምርት ዘመን ሰሊጥ፣ ጥጥ እና ማሽላ በማምረት ላይ ይገኛሉ:: በአሁኑ ወቅትም የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል:: ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና በሌሎችም ምክንያቶች የምርት ብክነት እንዳያጋጥማቸው በወቅቱ እየሰበሰቡ መሆኑን ነው የተናገሩት::

አርሶ አደሩ እንደተናገሩት እስካሁን በሰሊጥ ከሸፈኑት 700 ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ሺህ ኩንታል የሰሊጥ ምርት አግኝተዋል፤ ምርቱን ወደ ገበያ እስከሚያቀርቡ ደግሞ ደረጃውን በጠበቀ መጋዝን ውስጥ አከማችተዋል::

ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች (ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ፣ ጥጥ፣ ማሽላ) ተሸፍኗል:: የመምሪያዉ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ ኑርሁሴን አብድልቃድር እንደተናገሩት እስከ ኅዳር 08 ቀን 2018 ዓ.ም 50 በመቶ ያህሉ ሰብል ተሰብስቧል:: ቀሪውንም በወቅቱ ለመሰብሰብ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል::

ሰብሉ ተወቅቶ ወደ ማከማቻ በሚገባበትም ወቅት የምርት ብክነት እንዳያጋጥም አርሶ አደሮች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ የግብርና ባለሙያዎችም እገዛቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነው ያሳሰቡት::

በተመሳሳይ የምዕራብ ጎንደር ዞን 525 ሺህ 336 ሄክታር መሬትን በሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሽላ፣ ጥጥ እና በሌሎች የምግብ ሰብሎች መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፤ ከዚህም 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ  የመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ ሞገስ ጋሹ ተናግረዋል:: ይህም 22 ነጥብ ስምንት ኩንታል በሄክታር እንደማለት ነው::

ብክነትን በመቀነስ የታቀደውን ምርት ለማሳካት በዞን እና በወረዳ ደረጃ የባለሙያ ቡድን ተቋቁሞ ቀበሌ ድረስ ወርዶ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል:: የደረሱ ሰብሎች በወቅቱ እየተሰበሰቡ መሆኑን ገልጸው ውቂያውም በዘመናዊ አሠራሮች ታግዞ እንዲከናወን እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል::

ባለሙያው እንዳሉት እስከ ኅዳር 09 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በ345 ሺህ 965 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ ሰብል ተሰብስቧል::

ሰብልን ከማሳ ላይ መሰብሰብ እንደተጠናቀቀ የምርት ብክነትን በሚያስቀር እና ጥራትን በሚያረጋግጥ አግባብ የመውቃት ሥራ እንደሚከናወን አቶ ሞገስ አስታውቀዋል:: በቂ ባይሆንም ምርትን ከማሳው ላይ ቀጥታ መሰብሰብ የሚያስችሉ 179 ሁለገብ መሰብሰቢያዎች (ኮምባይነር) ወደ ሥራ ይገባሉ ብለዋል::

በቀጣይም ትራክተር እና ሁለገብ መውቂያዎችን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል:: ከልማት ባንክ እና ከሌሎችም ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል::

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በክልሉ የግብርና ሜካናዜሽን እንዲስፋፋ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል:: ቢሮው በግብአት አቅርቦት፣ ስርጭትና ቁጥጥር መመሪያ ላይ ውይይት ባካሄደበት ወቅት ክልሉ ለሜካናይዜሽን የተመቸ መሆኑን አስታውቀዋል::

የእርሻ ሜካናይዜሽንን ማስፋፋትም ለዘመናት በበሬ ትከሻ በማረስ፣ በሰው ጉልበት ምርት በመሰብሰብ እና በእንስሳት ጉልበት ምርትን ከገለባ በመለየት ይባክን የነበረውን የአርሶ አደሩን ጉልበት እና ጊዜ ከመቆጠብ ባለፈ የምርት ብክነትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ነው የገለጹት::

ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን በስፋት መተግበር አርሶ አደሮች ያላቸውን የተበጣጠሰ መሬት አቀናጅተው በዘመናዊ መንገድ  እንዲያመርቱ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ታምኖበት በትኩረት እየተሠራበት ነውም ብለዋል:: ይህ ደግሞ የምርት ብክነትን በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል፤ በአርሶ አደሩ በኩል የሜካናይዜሽን ፍላጎት እንዲፈጠር ማስቻል፣ አስፈላጊውን ገንዘብም እንዲቆጥቡ ማድረግ ላይ በስፋት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል::

ዘመናዊ የአመራረት ዘዴ በክልሉ እንዲሰፋ የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል:: ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የብድር ሥርዓትን ለማመቻቸትም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል::

በአየር ፀባይ ሁኔታ፣ በሰብሎች አሰባሰብ፣ በውቂያ እና በክምችት ወቅት ከ15 እስከ 22 በመቶ የምርት ብክነት እንደሚኖር የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። በወቅቱ አለመሰብሰብ፣ ዝናብ /እርጥበት/ በማያስገባ መልኩ አለመከመር፣ የተሰበሰበውን ሰብል ጥራት እና መጠን ጠብቆ አለመውቃት፣ የጎተራ ተባዮችን የሚቀንሱ የተሻሻሉ የሰብል ማከማቻ ዘዴዎችን /ቴክኖሎጂዎችን አለመጠቀም፣ የከረመ እና አዲስ ሰብልን ቀላቅሎ ማስቀመጥ፣ የሰብል ማከማቻዎችን በአግባቡ አለማፅዳት እና ፀረ-ተባይ መድኃኒቶችን በአግባቡ አለመጠቀም የምርት ብክነት ዋና መንስኤዎች መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል::

ምርትን በወቅቱ መሰብሰብ፣ ዝናብ /እርጥበት/ በማያስገባ መልኩ መከመር እና መውቃት፣ ከውቂያም በኋላ በጥንቃቄ ወደ ጎተራ ማስገባት፣ የተሻሻሉ የእህል ማከማቻ ዘዴዎችን /ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንዲሁም ጎተራን በአግባቡ ማፅዳት የምርት ብክነትን በከፍተኛ መጠን ይቀንሳሉ ብሏል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሕዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here