የምንጊዜም ምርጡ ተከላካይ

0
92

ግሎብ ሶከር አዋርድ የተሰኘው ተቋም ይህንን እግር ኳሰኛ ከሦስት ዓመት በፊት “የምንጊዜም ምርጡ ተከላካይ” ሲል መርጦታል:: ዛሬ ላይ እድሜው 39 ደርሶ እና ጉዳቶች ተጠናክረውበት የእግር ኳስ ግርማ ሞገሱ የተገፈፈ ቢመስልም ሰውዬው ግን የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪዎች በሙሉ በአንድነት ያጨበጨቡለት ምርጥ የመሀል ተከላካይ ነው፡፡

ተወልዶ ያደገው በስፔኗ ሲቪያ ከተማ ውስጥ ነው:: እግር ኳስን መጫወት የጀመረውም ለስፔኑ ሲቪያ ክለብ ነው:: ምንም እንኳን እግር ኳስን በተወለደባት ከተማ ሲቪያ ይጀምር እንጂ በዓለም እግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ ጐልቶ የታወቀው ግን በስፔኑ ኃያል ክለብ በሪያል ማድሪድ መለያ ነው፡፡

ለስፔን ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ከመጫወቱ በተጨማሪ ለስፔን ዋናው ብሔራዊ ቡድን 180 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል:: ከስፔን ብሔራዊ ቡድን ጋር የዓለም ዋንጫን እና የአውሮፓ ዋንጫን ማሳካት የቻለው ይሄው ስፔናዊ የኋላ ደጀን፣ ከሪያል ማድሪድ ክለብ ጋር ደግሞ አራት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ፣ አምስት የስፔን ላሊጋ ዋንጫ እና ሁለት የኮፓ ዴላሬ ዋንጫዎችን ስሟል፡፡

የሪያል ማድሪድ ጠንካራ የመከላከል ብቃት ሲታወስ ስሙ ቀድሞ የሚጠራውም ይሄው ተጨዋች ነው::በተለይ በ2018 (እ.አ.አ) ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ ጋር ሲጫወቱ ግብፃዊው የሊቨርፑል አጥቂ ላይ ባደረሰበት  ጉዳት  ብዙ  ሰዎች  ያስታውሱታል፡፡

በጀርገን ክሎፕ የሚመሩት ሊቨርፑሎች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ገናና ስም ካለው የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ጋር የሚያደርጉት የፍፃሜ ጨዋታ የብዙ እግር ኳስ አፍቃሪዎችን ትኩረት የሳበ ነበር፤ በተለይ የሊቨርፑልን የአጥቂ መስመር የሚመራው ሙሐመድ ሳላህ ከሪያል ማድሪዱ የኋላ ደጀን ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያም በጉጉት የተጠበቀ ነበር፤ ጨዋታው በተጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግን ስፔናዊው ተከላካይ በሙሐመድ ሳላህ ላይ ባደረሰበት ከፍተኛ የትከሻ ጉዳት ሳላህ ከሜዳ  ሲወጣ ተከላካዩ የቢጫ ካርድ ተመልክቶ ጨዋታው ቀጥሏል:: በመጨረሻም ያለ ሙሐመድ ሳላህ የተጫወቱት ሊቨርፑሎች በሪያል ማድሪድ የ3 ለ 1 ሽንፈትን አስተናግደዋል፡፡

አሁን ስለየትኛው የስፔን እና የሪያል ማድሪድ ተከላካይ እያወራን እንደሆነ ለአንባቢዎች ግልፅ ይመስለኛል:: ሙሉ ስሙ ሰርጂዮ ራሞስ ጋርሲያ ይባላል::ዓለማችን ካፈራቻቸው ጠንካራ የመሀል ተከላካዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ሰርጂዮ ራሞስ አሁን ላይ በሜክሲኮው ሞንቴሬይ ክለብ በመጫወት ላይ  ይገኛል፤ እድሜው ደግሞ 39 ደርሷል፡፡

ራሱን በጡረታ  ማግለል ወይም ጫማውን መስቀል የማይፈልገው ስፔናዊው ጠንካራ የመሀል ተከላካይ ከስፔን ብሔራዊ ቡድን የተሰናበተበትን ሁኔታም ይቃወማል::በወቅቱ ከስፔን ብሔራዊ ቡድን በአዲሱ አሰልጣኝ ዲላ ፎውንቴ ሲሰናበት “ብዙ ካገለገልኩበት እና ገና ብዙም አገለግላለሁ ካልኩበት የስፔን ብሔራዊ ቡድን መሰናበቴን ስገልጽ በጥልቅ ሐዘን ነው” በማለት መረጃውን በማኀበራዊ የትሥሥር ገጹ አጋርቷል፡፡

ራሞስ ከብሔራዊ ቡድን መሰናበቱን በተመለከተ የተሰማውን መጥፎ ስሜት ለተከታዮቹ እና ደጋፊዎቹ  ባጋራው መልዕክቱ “አቋሜ ሳይወርድ እና ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በፈቃዴ ራሴን ሳላገል እኔን ማሰናበት ተገቢ አልነበረም” የሚል ሃሳቡንም አጋርቷል::እዚህ ላይ ለስፔን ብሔራዊ ቡድን 180 ጊዜ ተሰልፎ መጫወቱን ልብ ይሏል፡፡

ጠንካራው ስፔናዊ የሪያል ማድሪድ ተከላካይ ከሎስ ብላንኮዎቹ ጋር በነበረው የ16 ዓመታት ቆይታ 22 ዋንጫዎችን አሳክቷል::በ671 ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ የመሀል ተከላካይ ሆኖ 101 ግቦችን በማስቆጠርም የሚስተካከለው ተጨዋች የለም::እነዚህን ሁሉ የተጨዋቹን ስኬቶች ግምት ውስጥ በማስገባት ግሎባል ሶከር አዋርድ የተባለው ተቋም ሰርጂዮ ራሞስን “የምንጊዜም መርጡ ተከላካይ” ማለቱ ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችን አበራክቷል ሲል የዘገበው ኢኤስፒኤን ነው፡፡

የሪያል ማድሪድን አምበልነት ከቀድሞው የሪያል ማድሪድ ግብ ጠባቂ ኢከር ካሲያስ ከተረከበ በኋላ በሪያል ማድሪድ ቤት ተፅእኖው የጐላው ራሞስ፣ የእሱ ተፅእኖ ፈጣሪነት በክለቡ ኘሬዚዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ እንደልተወደደለት እና ከክለቡ ለመሰናበቱም ምክንያቱ ይሄው እንደሆነ መረጃዎች በስፋት ወጥተዋል፡፡

ለሪያል ማድሪድ የ16 ዓመታት ግልጋሎት ያበረከተው እና ራሱንም ሆነ ክለቡን ለብዙ ክብሮች ያበቃው ሰርጂዮ ራሞስ ከሪያል ማድሪድ ሲሰናበት የፈረንሳዩን ፒኤስጂ ክለብ ተቀላቅሏል::በፒኤስጂ ከቀድሞው  የባርሴሎና ተቀናቃኙ ሊዮኔል ሜሲ ጋር በጋራ የመጫወት እድልንም አግኝቷል::ፒኤስጂን በጉዳት ምክንያት ብዙም ማገልገል ያልቻለው ራሞስ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ሲቪያ ተመልሶ መጫወት የቻለ ቢሆንም በሲቪያም በጉዳት እና በአቋም መውረድ ምክንያት  በተጠበቀው ልክ መጫወት ሳይችል ቀርቷል፡፡

አሁን በሜክሲኮው ሞንቴሬይ ክለብ 93 ቁጥር መለያ ለብሶ የእግር ኳስ ጨዋታን የቀጠለው ሲርጂዮ ራሞስ ከስፔን ብሔራዊ ቡድን እና በተለይ ደግሞ ከሪያል ማድሪድ ክለብ ጋር ባሳለፋቸው ድንቅ  ዓመታት የዓለም ኮከብ ተጨዋች እና የአውሮፓ ኮከብ ተጨዋችነትን ክብር አለማግኘቱ ብዙዎችን የሚያስቆጭ ሆኗል፡፡

በእግር ኳስ የዓለም ኮከብ እየተባሉ የሚመረጡት ተጨዋቾች ግብ የሚያስቆጥሩት ብቻ እንደሆነ ማሳያው ሰርጂዮ ራሞስ እና በርካታ ግብ ጠባቂዎች እንደሆኑ አብነት እየጠቀሱ የሚከራከሩ ብዙ የእግር ኳስ ተንታኞች እየተፈጠሩ ነው::ከጣሊያናዊው የተከላካይ መስመር ተጨዋቹ ፋቢዮ ካናቫሮ እና ከጀርመናዊው ግብ ጠባቂ ኦሊቨር ካህን ውጪም ለትልቅ ክብር የበቁ የኋላ መስመር ተጨዋቾች  እንደሌሉም  አብነቶች ይጠቀሳሉ፡፡

ሰርጂዮ ራሞስን ያጡት ሪያል ማድሪዶች የኋላ መስመራቸው በብዙ እየተፈተነ ስለመሆኑ የዘንድሮ የተለያዩ ጨዋታዎቻቸው እማኝነት ይሰጣሉ::በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በአርሴናል በደርሶ መልስ 5 ለ 1 የመሸነፋቸው ሚስጥርም ይሄው የኋላ መስመራቸው ድክመት እንደሆነ አይታበልም::በላሊጋውም ቢሆን በባርሴሎና እየተመሩ በመሆናቸው ዘንድሮ ያለምንም ዋንጫ ዓመቱን የሚያጠናቅቁ ከሆነ የቀድሞ የኋላ ደጀናቸውን አብዝተው የሚናፍቁት ይሆናሉ፡፡

ግሎብ ሶከር አዋርድ የምንጊዜም ምርጡ ተከላካይ ያለው ሰርጂዮ ራሞስ በእናንተ አተያይስ የዓለም እና የአውሮፓ ኮከብ ተጨዋችነት ክብር አይገባውም ነበር ትላለችሁ?፡፡

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የሚያዝያ 20  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here