“የምዘግበው ለሀገሬ በታማኝነት ነው”

0
177

‹‹ያልጠየቀችው ምሁር እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ አለ›› ለማለት ይከብዳል:: የምታነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ጥንካሬና አስፈላጊነት፣ እንግዶቿን ጥያቄ ስትጠይቅ የምታሳየው ጨዋነት እና እርጋታ፣ ለጥያቄዎቹ የምታደርገው ዝግጅት፣ ለሙያው ያላት ክብር፣ … እጅግ አስደናቂና አስደሳች ነው!

ክርስቲያን አማንፑር በጋዜጠኝነት ስራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ የስም ልዕልና ካላቸው ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ናት:: ከእንግሊዛዊ እናት እና ከኢራናዊ አባት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር መስከረም 12 ቀን 1958 ተወለደች:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን አንደጨረሰች፤ ወደ እንግሊዝ ለትምህርት ተላከች:: አባቷ እንደ አውሮፓዊያን ዘመን ቀመር በ1979 በኢራን የተካሄደውን አብዮት ተከትሎ ከሥራቸው ተፈናቅለዋል፤ ይህን ተከትሎ ቤተሰቡ የተወሰነ መቸገሩ ይነገራል:: ሆኖም ኢራንን ለቀው ወደ እንግሊዝ አምርተዋል::

አማንፑር በ1983 የመጀመመሪያ ዲግሪዋን በጆርናሊዝም የትምህርት መስክ አግኝታለች:: ከሁለት ዓመታት በኋላም በሲኤንኤን ኮርስፖንዳንት ሆና ተቀጠረች:: በ1985 እ.አ.አ ኢራቅ ኢራን ጦርነት ላይ የሰራችው ዘገባ ዓለም ለዚህች ታዳጊ ወጣት ጋዜጠኛ ዓይን እና ጆሮውን እንዲሰጣት ከማስቻሉም በላይ የዲፖንት-ሽልማት አሸናፊ እንድትሆን አድርጓታል::

ለሲኤንኤን መሥራት የጀመረችው በዜና ክፍል ረዳትነት ሲሆን አሁን ላይ የጣቢያው ፈርጥ ጋዜጠኛ ከመሆኗ አስቀድሞ በጥቁር ፀጉሯ እና የንግግር ዘይቤዋ ለረጅም ዓመታት አየር ላይ እንዳትወጣ ተከልክላ እንደነበር ትናገራለች::

ዛሬ ላይ የጣቢያው ዓለም አቀፍ የዜና ተንታኝ በመሆን ዘገባዎችን  በመስራት እና የተለያዩ ሀገራት መሪዎችን ቃለ መጠይቅ እያደረገች ዓለማችንን የተሻለች የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ እየሰራች ትገኛለች::

አንጋፋዋ የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ክርስቲያን አማንፑር፤ ከኢራኑ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ ጋር በኒው ዮርክ ልታደርግ የነበረውን ቃለመጠይቅ ፀጉሯን እንድትሸፍን በመጠየቋ ሰርዛለች።

አማንፑር ከዚህ ቀደም የነበሩ የኢራን መሪዎችን ከኢራን ውጪ ቃለ መጠይቅ በምታደርግበት ወቅት፣ ፀጉሯን እንድትሸፍን ጥያቄ ቀርቦላት እንደማያውቅ ተናግራለች።

የፕሬዚዳንቱ ረዳት፣ ይህ ጥያቄ የቀረበላት “አሁን በኢራን ባለው ሁኔታ” ምክንያት መሆኑን እንዳሳወቋትም ጠቁማለች። አማንፑር ከፕሬዚዳንቱ ረዳቶች በአንዱ ፀጉሯን እንድትሸፍን ጥያቄ እስከሚቀርብላት ድረስ ቃለ መጠይቁን ለማድረግ ዝግጁ እንደነበረች ተናግራለች።

በትዊተር ገጿ ላይ “የጭንቅላት መሸፈኛን በተመለከተ ሕግ ወይም ባህል በሌለበት ኒው ዮርክ ውስጥ ነው ጥያቄው የቀረበው” ስትል ተናግራለች።

የፕሬዝዳንቱ ረዳት ፀጉሯን የማትሸፍን ከሆነ ቃለ መጠይቁ እንደማይደረግ ግልጽ እንዳደረጉላት እና ይህም “የአክብሮት ጉዳይ ነው” በሚል እንደተገለጸላት ተናግራለች።

አማንፑር እና የፕሮግራሟ አዘጋጆች “ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ እና ያልተጠበቀ ሁኔታ” በማለት የጠራችውን ሁኔታ በመቃወም ቃለ ምልልሱን ሰርዘው ጥለው ወጥተዋል።

አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ፀጉሯን ሳትሸፍን ፕሬዝዳንቱ ሊቀመጡበት ተዘጋጅቶ የነበረ ባዶ ወንበር ፊት ለፊት ተቀምጣ የሚያሳይ ፎቶ ለጥፋለች።

የሲኤንኤን ጋዜጠኛዋ ክርስቲያን አማንፑር ታይም መጽሔት የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ኮርስፖንዳንት ሲል እንደመረጣት ይታወሳል። በ1980 የተካሄደውን የቦሲኒያ ጦርነት በቦታው ተገኝታ ዘግባለች። ስለ ጦርነት አዘጋገብ ያላትን አተያይ ስታጋራ ብሔራዊ ጥቅምን ታሳቢ ማድረግን ትመክራለች።

“በጦርነት ዘገባ ላይ በሚዛናዊነት እሳቤ ገለልተኛ መሆን የጠላትና የአጥፊዎች ተባባሪ እንደመሆን ነው። ሚዛናዊነት ሁሉንም (ሀገርን እና ሀገርን እየወጋ ያለ ኃይል) በእኩል ማስተናገድ አይደለም። ሁለቱ በሞራል እኩል ሊሳሉ አይችሉም። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለሁም። ምክንያቱም የምዘግበው (ለሀገሬ) በታማኝነት ነው” ትላለች።

ክርስቲያን አማንፖር የትራምፕን አስተዳደር ከሚቃወሙ ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ነበረች:: የትራምፕን አስተዳደር ከናዚ ጀመርመን መንግሥት ጋር እያወዳደረች አውግዛለች:: አስተዳደሩ ለነጭ የበላይነትን ለሚያቀነቅኑ ቡድኖች ድጋፍ ይሰጣልም ስትል ተችታለች::

ጥቅምት 23 ቀን 2007 እ.አ.አ ለጋዜጠኝነት ሥራዋ የብሪቲሽ ኢምፓየር ትዕዛዝ ኮማንደር ባጅ (ቁጥር 3) ተቀብላለች። ክርስቲያን አማንፖር በጋዜጠኝነት ላበረከተችው አስተዋጽኦ ከ45 በላይ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን እና ክብሮችን ተጎናጽፋለች::

ከዚህ ባሻገር አይረን ማን ሁለት፣ ፒንክ ፓኝተር ሁለት፣ ዘ ኢሞርታልስ እና ሌሎች የሆሊውድ ትላልቅ ፊልሞች ላይ ራሷን ገጸ ባሕሪ በመወከል ተውናለች::

አማንፑር ጊልሞር ገርልስ በተሰኘ የቴሌቭዥን ተከታታይ ፊልም እንደ እራሷ ሆና ሠርታለች:: በተከታታይ ፊልሙ ውስጥ፣ አማንፑር ከዋና ገፀ-ባህሪያት ለአንዱ ለጋዜጠኛ ሮሪ ጊልሞር የሥራ መንፈስ መነሳሳት እንደምክኒያት ሆና ቀርባለች።

አማንፖር ብቸኛ ልጇን ጆን ዳሪዩስ ሩቢንን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2000 ነበር የወለደችው:: በወቅቱ ክርሰቲያን አማንፖር 41 ዓመቷ ነበር::

በሀገራችን እንደ አማንፖር የምትነሳው ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ናት፤ አድናቂዎች ለመዓዛ ብዙ ስም ሰጥተዋታል:: ‹‹ብረቷ እመቤት››፣ ‹‹ጀግና ሴት››፣ ‹‹አንደኛ››፣ ‹‹ተዓምረኛ እንስት››፣ … እነጋዜጠኛ ብሩክ ታየ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያዊቷ ክርስቲያን አማንፑር›› ይሏታል::

በሀገራችን በመገናኛ ብዙኃንና በጋዜጠኝነት ዘርፍ ያለው የሴቶች ተሳትፎና ተፅዕኖ ፈጣነሪነት አነስተኛና ማደግ/መሻሻል ያለበት ነው:: (በተለይ) በሙያው ላይ ያሉም ሆኑ ወደፊት ወደዚህ ሙያ የሚገቡ ሴት ኢትዮጵያውያን ከጋዜጠኛ ክርስቲያን አማንፖር እና መዓዛ ብሩ ትልቅ ልምድ ሊቀስሙ ይገባል!

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here