“የሞተው ወንድምሽ የገደለዉ ባልሽ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ”

0
173

ክሊመንቲያና እህቷ ክሌር በሩዋንዳው የርስ በርስ ጦርነት ብዙ ዋጋ ከፍለው በህይወት ከተረፉት እድለኞች መካከል ናቸው:: በ6 ዓመቷ ያንን አስከፊ ክስተት ያየችዉ ክሊመንቲያ ክስተቱን በጠራራ ፀሀይ ከሚጥል መብረቅ ጋር ታነጻጽረዋልች:: ከተዘጋ ቤት እየተንኳኳ የተገኘው ሁሉ ሲገደል የልጅነት የዓይን እማኞች ናቸው:: ከዚህ የሞት ድግስ በተዓምር ተርፈው ዛሬ ያንን ጊዜ የሚተርኩት እህትማማቾች የሆነውን ህልም ነበር ብለው ማሰብ ይሻሉ::

በአፍታ ቅጽበት ከሞቀ ቤት፤ ከቤተሰብ አቅፍ ወጥቶ ህልምም ተረትም እውነትም የሆነውን የህይወት ዘመን ትዝታ ለመተረክ የወሰደው ቅጽበት ነው:: የነበረው እንዳልነበረ ለመሆን ዓይንን ከድኖ የመግለጥ ያህል ቆይታ ብቻ ነው የጠየቀው::

በዚያ እድሜ ከሞት አምልጠው ወደየትና ወደማን መሄድ አሊያም ምን ማድረግ እንዳልባቸው አያውቁም:: መፍትሔው እግር ወዳደረሰው መሮጥ  ብቻ ነበር:: በዚያ ለጋ እድሜ መራብና መጠማትን፣ መጠጊያና ተስፋ ማጣትን፣ የድርጊቱን መንስኤና መፍትሔ  ማሰላሰልና በማይችል ዓዕምሮ ግራ መጋባትንና መድረሻ ቢስነትን አስተናግደዋል:: በየሀገሩ ከስድስት በላይ የስደተኞች የመጠለያ ጣቢያዎች ተዘዋውረዋል:: የ6 ዓመቷ ክሊመንቲያ እንደምትለው ቤተሰቦቻቸው በህይወት ይኑሩ ወይም ይሙቱ አያውቁም:: ከሞት ለማምለጥ እግሬ አውጭኝ ብለው ከቤት ሲወጡ ቤተሰቦቻቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንኳ ምንም መረጃው አልነበራቸውም:: በዓለማቀፉ የቀይ መስቀል ማህበርና በሌሎችም አፋላጊ ድርጅቶች ሙከራ ከ12 ዓመታት ፍለጋ በኋላ ሙሉ ቤተሰቧን አገኘች::

ያንን በጠራራ ፀሀይ እንደሚጥል መብረቅ ነው ያለችውን ጭፍጨፋ አልፋ ቤተሰቧን አገኘች:: አይገርምም ዓለም ግን ዛሬም ከዛ ለባሰ የርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ጦሩን ሲሰብቅ ያድራል::

የእኛም እጣ ፈንታ ይሄው ነው:: ከሰሜኑ ጦርነት ሳናገግም ይኼው ዳግም በርስ በርስ ግጭት ውስጥ እንገኛለን:: ብዙዎችን በሞት ከጎናችን አጥተናል:: ብዙዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው ለረሃብና ለእንግልት ተዳርገዋል:: ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል:: ዓእንደ ሩዋንዳ ዓይነት ሀገራት እኔን ኘየየ ይቀጣ እያሉ ዓለምን ለሰላም እየሰበኩና ወደልማት ገብተው-እንደኛ ዓይነት ሀገር ያውም ሀገር በቀል የእርቅ፤ የሽምግልናና ችግርን የምፍቻ መንገድ ያለው ጥንታዊና ታሪካዊ ሀገር የራስን ጸብ በራስ ለማርገብ በእልፍ ዛሬም የበርካታ ህይወት በሚገበርበት ግጭት ውስጥ ዋጋ እንከፍላለን::

ሩዋንዳውያን ችግራቸውን ዳግም እንዳይመለስ በእርቅና በይቅር ባይነት ዘግተዋል:: ነገር ግን ጥሎት ያለፈው ጠባሳ ዛሬም ድረስ አልሻረም:: ለሩሪክ የሚቀመጥ ጠባሳን ከማሳረፉ በፊት እኛም ችግራችንን በንግግርና በውይይት ፈተን ወደልማትና ወደሰላም መመለስ ይሻለናል:: “ካለበለዚያ የሞተው  ወንድምሽ የገደለው ባልሽ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” የርስ በርስ ግጭት ውጤቱ ሁላችንንም ነው ሚበላን::

 

በኲር ጥቅምት 11  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here