የሠላሳ ቀኑ ስምምነት

0
116

ሦስት ዓመታትን የተሻገረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት  በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ነጥቋል። በሚሊዮኖች ሲፈናቀሉ የዩክሬን ከተሞች እና መሠረተ ልማቶች እንዲሁም የሩሲያ ግዛቶችም እየፈራረሱ ይገኛሉ፡፡

ጦርነቱን ለማስቆም የተደረጉ ጥረቶችም ከዚህ ግባ የሚባል ውጤት አላስገኙም፤ በድጋሚ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት የገቡት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ትራምፕ ግን ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ከሰሞኑ የአሜሪካ እና የዩክሬን ልዑካን በሳዑዲ አረቢያ ያደረጉት ከፍተኛ ውይይትም የዚህ ማሳያ ነው፤ ይህን ተከትሎም ሁለት ቁልፍ ጉዳዮች ታይተዋል። በመጀመሪያ ዩክሬን ይሁንታ የሰጠችውን የ30ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ሩሲያ እንድትቀበለው የሚጠይቀው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ዋሺንግተን ለኪየቭ ወታደራዊ ዕርዳታ እና የስለላ ድጋፍ እንደገና መጀመሩን ማስታወቋ ነው። ይሁንና  የመጨረሻው ዙር ድርድር በሩሲያ ፖለቲከኞች፣ ባለሙያዎች እና ጋዜጠኞች መካከል ሰፊ ክርክር አስነስቷል።

ሩሲያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ሰርጌይ ማርኮቭ አሜሪካ ያቀረበችውን የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ሀገራቸው ላትቀበል የምትችልባቸውን ምክንያቶች አስቀምጠዋል፡፡ ከምክንያቶቹ ውስጥም  የተኩስ አቁም ስምምነቱ የሩሲያ ጦር ግስጋሴን ለማስቆም እና ተነሳሽነቱን ለመግፈፍ ያለመ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ በተቃራኒው የተኩስ አቁሙ ለዩክሬን  ተጨማሪ የጦር መሣሪያ ለማቅረብ ለማመቻቸት ነው ሲሉም ነው ያብራሩት፡፡ እንዲሁም ሰፊ ወታደራዊ ቅስቀሳን ለመቀጠል እና የዩክሬን የፖለቲካ አገዛዝ አፋኝነት እና ፀረ ሩሲያ ተፈጥሮን ለማጠናከር በምዕራቡ ዓለም እና በዩክሬን በኩል ጥቅም ላይ ስለሚውል ሩሲያ የተኩስ  አቁሙን መቀበል የለባትም ሲሉ ለታስ የዜና ወኪል ተናግረዋል፡፡

ይህ ይባል እንጂ የዩክሬን እና የአሜሪካ ልዑካን የመጨረሻ መግለጫ እንደሚያሳየው በሳዑዲ አረቢያ የተደረገው ስብሰባ በአሜሪካ ዕቅድ መሠረት መካሄዱን ነው። አሜሪካ ዩክሬንን በፍጥነት ጦርነቱን እንድታቆም  ማስማማት እንደሚያስፈልግ እንድትገነዘብ ግፊት ማድረግ ነበር ዓላማዋ፤ ግፊቷም ተሳክቷል። በምላሹ ዋሺንግተን ከዚህ ቀደም አግዳ የነበረውን የዩክሬን ወታደራዊ ዕርዳታን ለመቀጠል ቃል ገብታለች፡፡

አሜሪካ ለዩክሬን ያቀረበችውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ጥያቄ ለሩሲያም እንደምታቀርብ አስታውቃለች። የአሜሪካ እና የዩክሬን ከፍተኛ ባለስልጣናት በሳዑዲ አረቢያ ጂዳህ ከተማ በተኩስ አቁም ዙሪያ በተወያዩበት ጊዜ  የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የተኩስ አቁም ሀሳቡን ለሩሲያ አቅርበው አዎንታዊ ምላሽ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ ልዑክም ወደ ሞስኮ በማቅናት ከሩሲያ ባለስልጣናት ጋር ምክክር በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ “ዩክሬን የተኩስ አቁም እና ውይይት ለማድረግ ዝግጁ ነች። ሩሲያ ይህንን ሃሳብ ውድቅ ካደረገች፣ በሚያሳዝን ሁኔታ ለሰላም እንቅፋት የሆነው ማን እንደሆነ እናውቃለን” ብለዋል ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮ።

ኪየቭ እና ዋሺንግተን ከስምምነት ላይ የደረሱት ዩክሬን በሞስኮ ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ፈጽማ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ከታወቀ በኋላ ነው።

ከአውሮፕላኑ ጥቃት በኋላ ሩሲያ በሰጠችው መግለጫ “ዩክሬን አሁንም ጦርነቱን ለማቆም ዲፕሎማሲያዊ ዘዴ ለመጠቀም ዝግጁ አለመሆኗን አመላካች ነው” ስትል የዩክሬንን ድርጊት አውግዛለች። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ “ከአሁን በኋላ ሩሲያ ይህን ጥሩ ሀሳብ እንድትቀበል ማሳመን የአሜሪካ ተግባር ነው” ብለዋል።

ሁለቱም ልዑካን (የአሜሪካ እና ዩክሬን) ጦርነቱን ለማቆም በሚደረገው ድርድር ላይ ለመሳተፍ እና ድርድሩን በአስቸኳይ ለመጀመር ልዑካኖቻቸውን ለመሰየም ተስማምተዋል። ይህ በእንዲህ እያለ አሜሪካ በሩሲያ ላይ “መጠነ ሰፊ” ማዕቀብና ታሪፍ ልትጥል እንደምትችል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሞኑ አስታውቀው ነበር፡፡

“የአሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነት ለዩክሬን ጊዜያዊ እረፍት ብቻ ይሰጣል” ሲሉ የተናገሩት  የክሬምሊን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከፍተኛ አማካሪ ዩሪ ኡሻኮቭ  ናቸው፡፡  ዩሪ ኡሻኮቭ በአሜሪካ ሀሳብ ላይ ለሩሲያ የዜና ወኪሎች ሪያ እና ታስ በሰጡት መግለጫ ሩሲያ ፍላጎቶቿን እና ጉዳዮቿን ከግምት ውስጥ በማስገባት የረጅም ጊዜ እልባት እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡ የታቀደው የተኩስ አቁም ለዩክሬን ኃይሎች ጊዜያዊ እረፍት ከማድረግ ያለፈ ነገር እንደማይፈይድ ነው የጠቆሙት፡፡

ሩሲያ አሜሪካ ጥያቄዎቿን ከግምት ውስጥ ታስገባለች  የሚል ተስፋ እንዳላት እና የሩሲያ ስጋትን ለአሜሪካ ተደራዳሪዎችም ማስተላለፉን አማካሪው ተናግረዋል። አሜሪካ በሩሲያ ላይ መጠነ ሰፊ ማዕቀብና ታሪፍ ልትጥል እንደምትችል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መናገራቸው ታዲያ የተኩስ አቁም ስምምነት ምክክሩን ተስፋ ቢስ ያደርገዋል እየተባለ ይገኛል፤ ሬውተርስ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ግንኙነቷን ለማደስ የተወሰኑ ማዕቀቦችን ለማንሳት እየተዘጋጀች መሆኑን ባለፈው ቢዘግብም ትራምፕ ከሰሞኑ በተረጋገጠ የማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው በሞስኮ የባንክ ሥርዓት ላይ ማዕቀብ ሊጣል እንደሚችል አመላክተዋል።

ትራምፕ እንዳሉት ሩሲያ ዩክሬንን እያወደመች በመሆኑ የተኩስ አቁም አልያም ዘላቂ የሰላም ስምምነት እስኪፈረም ድረስ በሩሲያ ባንኮች ላይ መጠነ ሰፊ ማዕቀብ ለመጣል ማሰባቸውን አሳውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሰሞኑ ኩርስክን ጎብኝተዋል፤ የጦር አዛዦችንም አግኝተው አነጋግረዋል፡፡ የሩሲያ ወታደሮች 86 በመቶ አካባቢውን መልሰው መቆጣጠራቸውን እና የዩክሬን ኃይሎችን ለማስወጣት የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ፑቲን አረጋግጠዋል።

ዩክሬን ባለፉት ሦስት ቀናት ወደ ሩሲያ ኩርስክ ክልል ያስገባቻቸው ወታደሮች በሩሲያ ከባድ የመልሶ ማጥቃት እየተፈጸመባቸው በከበባ ውስጥ እንደሚገኙ ሬውተርስ ዘግቦ ነበር፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው ደግሞ ክሬምሊን የተኩስ አቁም ስምምነቱን እያጠና መሆኑን አስታውቋል፡፡ ቀደም ሲል ትራምፕ የተኩስ ማቆም ዕድልን በተመለከተ አዎንታዊ መልዕክቶች እንደደረሳቸው ተናግረው ነበር። ይን እንጂ “መልዕክት ብቻ ዋጋ የለውም”  ነው ያሉት። ተግባራዊ ካልተደረጉም ሩሲያን ለመጫን “በገንዘብ (በማዕቀብ) ነገሮችን ማድረግ እችላለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህ በእንዲህ እያለ ዩክሬን ከሰሞኑ በሩሲያ ላይ በፈጸመችው መጠነ ሰፊ የድሮን ጥቃት ቢያንስ ሦስት ሰዎች ሲሞቱ 18 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል። ዩክሬን  በ337 ድሮኖች ነበር ሩሲያ ላይ ጥቃት የሰነዘረችው፡፡ 91 ድሮኖችም ሞስኮን ዒላማ ያደረጉ እንደነበሩ የሩሲያዉ የዜና ኤጀንሲ ታስ ባወጣው መረጃ አመላክቷል። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የድሮን ጥቃቶቹን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ ሌሊት ላይ ሞስኮን ዒላማ ያደረጉ 91 ድሮኖችን ጨምሮ 337 የድሮን ጥቃቶችን አየር ላይ ማምከኑን አስታውቋል።

ሌሊት 10 ሰዓት ላይ በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ህንጻዎች መጎዳታቸው ታውቋል፡፡ በሞስኮ የሚገኙ ኤርፖርቶች መዘጋታቸው እና የባሕር ትራንስፖርትም ነው የተገለጸው።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here