የሠራተኞች ቀን አከባበር የሚጀምረው የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ተከትሎ በርካታ የእድገት ለውጦች በታዩበት ወቅት ነው። በወቅቱ በአሜሪካ ይካሄድ የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እ.አ.አ በ1865 ከመጠናቀቁ አስቀድሞ በተለይ በሰሜን ምሥራቅ የሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች ከእርሻ መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ተሸጋግረው ነበር። አዳዲስ የፈጠራ ግኝቶችም የጉልበት ሥራ በማሽኖች እንዲተኩ ያስቻሉ ነበሩ፡፡ ይህም በፍጥነት እየተስፋፉ የሄዱት የባቡር ሀዲድ ግንባታ ቁሳቁሶች ወደ ተለያዩ ፋብሪካዎች እና ገበያዎች በቀላሉ እንዲሰራጩ አግዘዋል።
እ.አ.አ በ1880ዎቹ የአሜሪካ ሠራተኞች በቀን ለ12 ሰዓታት፣ በሳምንት ደግሞ ለስድስት ቀናት በትንሽ ደመወዝ ይሠሩ ነበር። የአምስት ዓመት ሕጻናት ሳይቀሩ አስከፊ ይዘት ባላቸው ፋብሪካዎች ለመሥራት ይገደዱ ነበር። በወቅቱ ጥቅም ማግኘት የሚባል ነገር ተሰምቶ የማያውቀው ጤና ጥበቃም ለሠራተኞቹ ልፋት ዕውቅና እንዲሰጥ ግፊት ይደረግ እንደነበር ታውቋል።
ዕለቱ እንዲከበር የተወሰነውም በ1886 በቺካጎ በተነሳው የሠራተኞች የስምንት ሰዓት ሥራ እንዲከበር የተቀጣጠለው አድማ በፖሊሶች በተተኮሰ ጥይት አራት ሰዎች ለህልፈት በመዳረጋቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡
በወቅቱ በሠራተኛው በኩል ሰላማዊ ሰልፍ መደረግ የጀመረው ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ነበር። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኢንዱስትሪው አብዮት ያለማቋረጥ የሚሠሩ አዳዲስ ማሽኖችን በማስገኘቱ የፋብሪካ ባለቤቶች ሠራተኞቻቸው ከዕሁድ በስተቀር በየቀኑ 16 ሰዓት እንዲሠሩ ያስገድዷቸው ስለነበር ነው፡፡
እነዚህ ለውጦች ሠራተኞች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲፈልሱ ያደረገ ሲሆን በተለያዩ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሥራ ፈላጊ አሜሪካውያን የኢንዱስትሪ ከተማ ወደ ነበሩት ኒው ዮርክ፣ ቺካጎ እና ፒትስበርግ የመሳሰሉ ከተሞች መምጣት ጀመሩ። ጎን ለጎንም አዲስ ሥራ ለማግኘትና ኑሯቸውን ለማሻሻል የሚፈልጉ በርካታ ስደተኞች በተለይ ከአውሮፓ በከፍተኛ ሁኔታ ይፈልሱ ነበር።
የአሜሪካ ኢኮኖሚ እያደገ ሲሄድ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየፋብሪካው ውስጥ በቀን አስራ ሁለት ሰዓት፣ በሳምንት ሰባት ቀን… እጅግ አስቸጋሪና አደገኛ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ዝቅተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው መሥራታቸውን ቀጠሉ። ከዛም ባለፈ እድሜያቸው እስከ አምስት ዓመት የሚደርሱ ሕፃናትን እና አዋቂዎችን በሰዓት ከሚከፈላቸው 20 ሳንቲም እጅግ ባነሰ ክፍያ ማሠራት እየተለመደ መጣ።
ቀስ በቀስ ግን አሠሪዎች ለሠራተኞች የተሻለ ክፍያ እንዲከፍሉና የሥራ ቦታዎችን እንዲያሻሽሉ መደራደር እንዲቻል የሠራተኛ ማህበራት መደራጀት እና የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀመሩ። በተለያዩ ጊዜያት የሚያዘጋጇቸው ስብሰባዎች እና የሥራ ማቆም አድማዎችም አድማውን በሚያካሂዱት ሠራተኞች እና አድማ በታኞች መካከል በሚደርስ ግጭት ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ወደ ሁከት ይቀየራሉ።
እ.አ.አ በመስከረም 5/1882 በተካሄደ ተቃውሞ በኒውዮርክ ከተማ የሚኖሩ 10 ሺህ ሠራተኞች ያለክፍያ ፈቃድ በመውሰድ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ተነስቶ መዳረሻውን በመናፈሻ ቦታ ያደረገ ጉዞ አካሄዱ። ይህ ቀን የመጀመሪያው የሠራተኞች የረፍት ቀን ተብሎ ተቆጠረ።
ከዛን ቀን ወዲህ የሠራተኞች የረፍት ቀን በይፋ እንዲካሄድ በቀረበው ጥያቄ ላይ የመንገድ ላይ ሰልፍ እንዲሁም ለሠራተኞች እና ለቤተሰቦቻቸው የመዝናኛ ቀን እንዲያካተቱበት ሐሳብ ቀረበ።
ይህን ተከትሎ የዩናይትድስቴትስ እና የካናዳ የንግድና የሠራተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የሠራተኞችን ኑሮ ለማሻሻል ከግንቦት 1 ቀን 1886 ጀምሮ ሠራተኞች በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ እንዲሠሩ ጥያቄ አቀረበ። ብዙ ቦታ የሚገኙ አሠሪዎች በጥያቄው ባለመስማማታቸው ግንቦት አንድ ቀን ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ፡፡ ይህ ንቅናቄ እያደገ ሄዶ በአሜሪካ የተጀመረው በሌሎችም ሀገራት ድጋፍ ማግኘት ቻለ፡፡ የሀገሪቱ ክፍለ ግዛቶች ለሠራተኞቹ ክብር የሚሰጥበት ቀን ለመመደብ አንድ በአንድ ሕግ ማውጣት ጀመሩ።
በየዓመቱ ሚያዝያ 23/ሜይ 1/ የሚከበረው የሠራተኞች ቀን የበጋው ወቅት የሚያበቃበት ይፋዊ ቀን እንዲሆን ተወሰነ። ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከበር በታቀደው መሰረት እስካሁን በዓሉ በሰልፍ እና ቤተሰብ አንድ ላይ ተሰባስበው ሽርሽና የተለያዩ ድግሶችን በማዘጋጀት ይከበራል።
ከበርካታ ውጣ ውረድ በኋላ የሠራተኞች ቀን ብሄራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር እ.አ.አ በ1894 የቀረበውን ረቂቅ ሕግ በፊርማቸው ያጸደቁት ፕሬዝዳንት ግሮቨር ክሊቭላንድ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤”እውነተኛ የአሜሪካዊነት ስሜት ለሠራተኞች የሚሰጠው ክብር በከፍተኛ ልፋት ለመገኘቱ እውቅና ይሰጣል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የሠራተኞች ቀን ታሪክ በአሜሪካ የዓለም የሠራተኞች ንቅናቄ ከተጀመረ ከመቶ ሰላሳ ዓመት በኋላ ብዙ ሀገራት ምናልባትም ከ80 በላይ የሚሆኑት ዕለቱን ብሔራዊ በዓል አድርገው ያከብሩታል፡፡
በኢትዮጵያም በየዓመቱ ቀኑ ታስቦ ከመከበሩ ባለፈ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት እና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ሠራተኞች እና አሠሪዎች በማህበር የመደራጀት እንዲሁም ማህበራቸውን የማቋቋም መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡ ይህ መብት አሠሪዎችም የአሠሪ ማህበር፣ ሠራተኞች የሠራተኛ ማህበር ለማቋቋም እና ለመደራጀት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡
የሠራተኛ ማህበር የሠራተኞችን መብት እና ጥቅም የሚያስከብር የሠራተኞች ድርጅትን በህብረት ስምምነት እና በሥራ ግጭት ላይ ሠራተኞችን ይወክላል፡፡ የሠራተኛ ማህበሩ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እና ትእዛዞች በአባላቱ መታወቃቸውን፣ መከበራቸውን እና መፈጸማቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የሠራተኛ ማህበር አባላት ሕጎች እና መመሪያዎች በሚወጡበት እና በሚሻሻሉበት ጊዜ ንቁ ተሳታፊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
የሠራተኞች ማኅበር መሪዎች የሥራ ክርክር ለማቅረብ፣ የኅብረት ስምምነት ለመደራደር፣ በማኅበር ስብሰባ ለመገኘት፣ በሴሚናሮች እና በሥልጠና ለመካፈል እንዲችሉ ከክፍያ ጋር ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ ፈቃዱም የሚሰጥበት ሁኔታ በኅብረት ስምምነት ሊወሰን ይችላል፡፡
በ1995 የወጣው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 603 እና 42 ንኡስ አንቀፅ አንድ (ሀ) እና የወንጀለኛ መቅጫ አዋጅ ቁጥር 414/2004፣ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2019 አንቀጽ 12 ንኡስ አንቀፅ አራት 82 እና 113 ተደንግጎ ይገኛል፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም