“የሥራ ሰው በመሆኔ ቶሎ ወደ እርጅና አልገባሁም”

0
178

በክፍል አንድ ትጉህ የሥራ ሰው እንዲሁም የሀገር ሽማግሌ ከሆኑት አሥር አለቃ ሁናቸው አያሌው ጋር ያደረግነውን ቆይታ አካፍለናችኋል፤ የመጨረሻውን ክፍል እነሆ::

 

ስለ ባሕር ዳር ከተማ ታሪክ ቢነግሩን?

የፋሽስት ጣሊያን ጦር ሀገራችንን በ1928 ዓ.ም ጥቅምት ወር ነበር የወረረው:: በወቅቱ ትንሽየዋ መንደር ባሕር ዳርም በሚያዝያ ወር በጠላት ጦር እጅ ወደቀች:: በዚህ ጊዜ የጣሊያን ጠላት ጦር ሙሉ ጎጃምን ተቆጣጠረ ተብሎ መወራቱ ይነገራል::

ፋሽስት ጣሊያን አብዛኛውን ትኩረቱን በመጀመሪያ በገዳማት የተያዙ የአስተዳደር አካባቢዎች ላይ ቢያደርግም እየቆየ የቅኝ ግዛት ዓላማውን ለማስፋት እና በህዝቡ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያስችለውን የፕሮፖጋንዳ ከመንዛቱም ባሻገር የአስተዳደር ቢሮዎችን ከፈተ:: ከዚህ ጋር ተያይዞም የጦር መንደሮችንም አቋቁሟል:: በወቅቱ የነበረውን ባላባታዊ የካህናት ርስት በማስለቀቅ የአውሮፓዊያንን የመሬት አስተዳደር ይዞታ ፖሊሲን ለማስፈጸም፣ ለማለማመድ እና ለመተካት ጥረት አድርጓል:: በዚህም ጣሊያን የመሬት ይዞታውን ከለወጠ በኋላ ነባር እና አዳዲስ መንደሮችን በማስተካከል መንገዶችን በመጥረግ በመጠኑም ቢሆን የከተማነት መልክ እንዳላበሳት ይነገራል:: በጊዜው ይከሰት የነበረውን ጎርፍ እና የውሃ ማቆር ለመከላከል ከድባንቄ ተራራ ጀምሮ ወደ ዓባይ እና ጣና የሚቀላቀሉ ተፋሰሶችን ቆፍሮ ሰርቷል::

ከዚህ ባለፈ ለባሕር ዳር የከተማነት ገጽታ ያላበሳት እና ለእድገቷ እንደዋነኛ ምክንያት የሚነሳው ጣሊያኖች በጣና ሀይቅ ላይ ስድስት ትላልቅ የሞተር ጀልባዎችን በማሰማራት ከዘጌ፣ ጎርጎራ እና ደልጊ አካባቢዎች ጋር ግንኙነት መፍጠራቸው ነው:: ይህም በንግድ፣ በማህበራዊ እና ሌሎች መስኮች ለከተማዋ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነበር:: ከገጽታ አንጻርም ቀልብ መሳብ ችላለች:: እንዲሁም ያላት ውበት ጎልቶ መውጣት ችሏል::

ጣሊያን የተለያዩ የመሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት ለከተማዋ እድገት አስተዋጽኦ ቢያበረክትም ሌሎች ቅኝ ገዥ ሀገራት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ እንደሚያደርጉት የፈጸመው እንጅ ለከተማዋም ሆነ ለሀገራችን አስቦ ያደረገው አለሆኑን መገንዘብ አያዳግትም:: ከዚህ ባለፈም የፋሽስት ጣሊያን ጦር የቅኝ ግዛት ቀንበሬን ካልተቀበላችሁኝ በሚል ህዝቡን መግረፍ፣ በማሰር፣ በመረሸን እና በመስቀል መቅጣቱን አላቋረጠም ነበር:: ህዝቡም ለጠላት በቀላሉ እጅ የሚሰጥ አልነበረም:: በዚህ የተነሳም በሸፈቱ የጦር አርበኞች እና አዝማቾች እየተመራ ጣሊያንን መግቢያ እና መውጫ ያሳጣው ነበር::

ከ1932 እስከ 1933 ድረስ የእንግሊዝ ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖች በባሕር ዳር ጣሊያኖች የሰሯቸውን ቤቶች እና ህንጻዎች መደብደባቸውን እና በጠላት ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን መረጃዎች ያሳያሉ:: በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ያሉ አርበኞች ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሱበት ፋሽስት ጣሊያን ሽንፈት ደርሶበት የነበረውን ሀብት እና ንብረት ጣና ሀይቅ ውስጥ በማስመጥ ወደ ደብረ ታቦር ሸሽቷል:: በጣሊያን እንዲሰጥሙ ከተደረጉ ንብረቶች መካከል ከሰጠሙበት እንዲወጡ ተደርገው አሁንም ድረስ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ መርከቦች አሉ::

በጣሊያን የፋሽስት ወረራ ወቅት አርበኞችን በመምራት ባሕር ዳርን ከጠላት ነፃ እንዳወጧት የሚነገርላቸው ስመ ጥር አርበኛው ቢተወደድ መንገሻ ጀምበሬ ናቸው::

በአጠቃላይ የባሕር ዳር አመሰራረት ስንመለከት ከጣሊያን ወረራ ጋር ተያይዞ የመንደርነት ቅርጽ እያየዘች ትምጣ እንጅ አሁን መስቀል አደባባይ ካለበት እስከ ሰርጸ ድንግል ትምህርት ቤት ያለው ቦታ ጣልያን ይጠቀምበት የነበረው አውሮፕላን ማረፊያ እና በ1936 በዘጌ የተገነባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መኖሩ እና ዘመናዊ ትምህርት በዚያው ከመጀመሩ ውጭ በዋናነት የሚጠቀሱ መሠረተ ልማቶች አልነበሩም::

 

በከንቲባ መመራት ከጀመረች በኋላስ የነበራት ገጽታስ?

በ1935 ዓ.ም ማዕከላዊ መንግሥቱ የአስተዳደር መዋቅር ለውጥ በማድረግ ባሕር ዳር የወረዳ ዋና ከተማ እንድትሆን አስችሏታል:: በዚህ ጊዜ የተሾሙት እና የመጀመሪያው የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ የነበሩት ደጃዝማች ጊላ ወልደ ጊዮርጊስ ይባላሉ::

በ1948 ዓ.ም የጎጃም አውራጃዎች እንደገና ሲዋቀሩ ባሕር ዳር የአውራጃ ዋና ከተማ የመሆን አድልም አግኝታለች:: ነገር ግን ልዩ ልዩ መሰረተ ልማቶች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት ከ1950ዎቹ ወዲህ ነበር::

በ1940ዎቹ መጨረሻ ከአብዛኞቹ የሀገራችን ከተሞች በአንጻራዊነት ባሕር ዳርን የበለጠ ዘመናዊነትን ሊያላብሳት የቻለ የከተማ ፕላን ተሰርቶላታል:: ይሁንና ፕላኑ ዝርዝር እና ደረጃውን የጠበቀ የከተማ ፕላን መስፈርቶችን የያዘ ብሎም ያሟላ አልነበረም:: ፕላኑ የያዘው የገበያ ቦታን እና ጠበብ እንዲሁም አነስተኛ መንገዶችን ነበር:: ከእነዚህ መንደሮች ውስጥ በተለምዶ ቀበሌ አምስት እና ስድስት እንዲሁም አራት በከፊል ይገኙበታል::

ከዚህ በመቀጠልም በወቅቱ የነበረው የኃይለ ሥላሴ መንግሥት በከተማዋ ውበት እና የተፈጥሮ ሀብት እየተገለጠለት በመምጣቱ ከተማዋን የበለጠ ለማዘመን ከውጭ መንግሥታት ጋር በመነጋገር የመጀመሪያው የአየር ላይ ፎቶ ግራፍ ተነስቷል:: ከዚህ ጋር ተያይዞ የከተማዋ ፕላን በተሻለ መልኩ ተሰርቷል:: የባሕር ዳር ድንበሮችም የጣና ሐይቅን እና በከተማዋ ዙሪያ ያሉ ተራሮችን ታከው የተሰመረ ነበሩ::

ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ባሕር ዳር መስፋት እና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች መገንባት የጀመሩበት ዋነኛ ጊዜ ነው:: ለአብነትም በ1951 በነዳጅ የሚሰራ መብራት ለስድስት ሰዓታት ማግኘት ጀመረች:: ከአምስት ዓመታት በኋላም ከጢስ አባይ ፏፏቴ ከሚመነጨው ኃይል በመሳብ የ24 ሰዓት ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆናለች:: በ1953 ደግሞ ንጹህ የመጠጥ ውኃ በቦኖ ለህዝቡ ማዳረስ ተጀመረ::

በዚህ ጊዜ ለከተማዋ እድገትን ያጎናጸፉ እና ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ መሰረተ ልማቶች መገንባት ቀጥለዋል:: ባሕር ዳርን ውብ ገጽታ ያላበሷት እና የከተማዋ ገጽታ መለያ መሆን የቻሉት ዘንባባዎች በዚህ ወቅት ነው የተተከሉት:: ከ1960ዎቹ ጀምሮ ባሕር ዳር ከተማ በመሰረተ ልማትም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች በሚደነቅ ፍጥነት ማደግ ጀመረች፤ ወደ ከተማዋ የሚፈልሰው ቁጥርም በእጥፍ እየጨመረ ዛሬ ካለበት ላይ ደርሷል:: የአማራ ክልል ርዕሰ መዲና የሆነችውም በ1985 ዓ.ም ነበር::

 

የአሥር አለቅነት ማዕረጉን እንዴት አገኙት?

አሥር አለቅነት ማዕረጉ የመጣው ሳልፈልገው ነው:: የእኔ ዋነኛው ሥራ ከብት ማርባት፣ እርሻ ማረስ ነበር:: በዚህ ሥራ ላይ እያለሁ ሽፍቶች ማስቸገር ጀመሩ:: ሰው ጫካ ማገዶ ለቅሞ የእለት ጉርሱን ለማግኘት፣ አርሶ ለመብላት አልችል አለ፤ ክምር ሳር ሁሉ ሚያቃጥል ወንጀለኛ ነበር:: በመሆኑም መንግሥት እነኚህን ሽፍቶች ልክ እንዳስገባ የአሥር አለቅነት ማዕረግ ሰጥቶ የጸጥታ ሹም አደረገኝ:: ብዙም የማልፈልገው ነገር የነበረ ቢሆንም ብዙ ወንጀለኞችን ይዣለሁ፣ እርምጃ የተወሰደባቸውም አሉ:: እሱ ካልመጣ እነ እገሌ አይያዙም እየተባለ ይወራ ነበር:: ከእነ ፊታውራሪ እያሱ ዘለቀ እና ሌሎች ሹመኞች ጋር ሠርቻለሁ::

 

ለረጅም እድሜዎ እና ለጥንካሬዎ ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?

መጨነቅ እና አብዝቶ ማሰብ አልወድም፤ ማስበው ነገር የለኝም፤ በደስታ ነው የምኖረው:: ሌላው ደግሞ የሥራ ሰው በመሆኔ ቶሎ ወደ እርጅና አልገባሁም::

 

እንግዳችን ስለነበሩ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

 

(ዮናስ ታደሰ )

በኲር ሰኔ 3 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here