“የሥራ ባሕላችን አልተለወጠም”

0
181
“ሥራ የሰው ልጆች ሁሉ የመኖር ዋስትና ነው:: ጠንክሮ የሠራ ከራስ አልፎ የቤተሰብን እና የአካባቢን ኑሮ ለመለወጥ ወደሚያበቃ ታላቅ ደረጃ ያሸጋግራል የሚል ዕምነት አለኝ” የሚል ጠንካራ አቋም ያላት ትውልድ እና ዕድገትዋ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዚገም ወረዳ የሆነችው የምሥራች በቀለ ናት:: የምሥራች በባሕር ዳር ከተማ ሆምላንድ ሆቴል አካባቢ ጫማ ከሚያሳምሩ ወጣቶች መካከል አንዷ ናት::
የምሥራች በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በቴክስታይል የትምህርት ዘርፍ በ2014 ዓ.ም ተመርቃለች:: ለሰባት ወራት በብሄረሰብ አስተዳድሩ በሥራ ፍለጋ አሳልፋለች:: ከዚህ በላይ መቆየትን ግን አልፈለገችም:: ምክንያቷ ደግሞ ከዓመት በፊት ለሥራ ፍለጋ ከጓደኞቿ ጋር ወደ ባሕር ዳር በመጣችበት ወቅት በሰለጠነችበት የትምህርት ዘርፍ በርካታ የሥራ ማስታወቂያዎችን ማየቷ ነበር::
ወጣቷ ሀሳቧን እውን ለማድረግ ወደ ባሕር ዳር አቀናች:: ከመጣች በኋላ ሳትሰለች በየዕለቱ ጊዮርጊስ አካባቢ ካለው የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ መከታተል ጀመረች:: አንድ ቀን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሰላም ካምፓስ በቴክስታይል የትምህርት ዘርፍ ለሰለጠኑ የኮንትራት ሥራ ቅጥር ማውጣቱን ተመለከተች:: በተባለው ቀን እና ቦታ ተገኝታ ተመዘገበች:: በውድድሩም አሸንፋ ቅጥር እንድትፈጽም ዩኒቨርሲቲው ጥሪ አደረገላት::
ቅጥር ለመፈጸም ግን የምስራች እንደምትናገረው ቀላል አልነበረም:: በተለይ የሥራ ዋስ በማጣቷ አባቷ ከአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰው ፈልገው እና የመጓጓዣ ከፍለው እንዳመጡላት ታስታውሳለች:: ወጣቷ የተጠየቀችውን መስፈርት ካሟላች በኋላ በ3ሺህ 500 ብር የወር ደሞዝ ተቀጥራ መሥራት ጀመረች::
በሰላም ካምፓስ ለአንድ ዓመት ከሠራች በኋላ የሥራ ኮንትራቱ ሲያልቅ ደግሞ ደግማ ወደ ቤተሰብ በመሄድ መቀመጥን ስላልፈለገች የተገኘውን ሥራ ለመሥራት መፈለግ ጀመረች:: የምስራች እንደምትለው እያንዳንዱ የሥራ ዓይነት ትንሽ ወይም ትልቅ ሳይባል በትኩረት ከተሠራ ጥሩ የገቢ ምንጭ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አላት:: ምክንያቷ ደግሞ ዛሬ ላይ በዝቅተኛ ሥራ በመሰማራታቸው ሲናቁ የነበሩ ሰዎች ከፍ ብለው ማየቷ ነበር::
ማንኛውም ሥራ ገቢ ያስገኛል፤ ዕድገትም ያስከትላል የሚል ጠንካራ እምነት ያላት የምስራች፤ የቀን ሥራን ጨምሮ እርሷ ልትሰማራባቸው የምትችላቸውን ዘርፎች ከማሰላሰል ባለፈ እየተዟዟረች ትመለከት ነበር::
የኋላ ኋላ ጥቂት የመነሻ ወረት የሚጠይቀውን ጫማ የማሳመር/የሊስትሮ/ ሥራን ለመሥራት አሰበች:: የሊስትሮ ሥራን ለመጀመር ሌሎች ሲሠሩ ቁጭ ብሎ ከመመልከት ባሻገር በመጠየቅም የተወሰኑ ቀናትን ይህን አሳለፈች:: ከዚህ በኋላም በ700 ብር አስፈላጊ የሚባሉ የሊስትሮ ዕቃዎችን ገዝታ ወደ ሥራ ገባች::
ወጣቷ በሥራዋ በፊት በኮንትራት ተቀጥራ ታገኘው ከነበረው ገቢ ያልተናነሰ ገንዘብ ታገኛለች:: አሁን ላይ በቀን ከ80 እስከ መቶ ብር ታገኛለች:: ክረምት ደግሞ የዕለት ገቢዋ ከዚህ እንደሚበልጥ ታምናለች::
የምሥራች ወደፊት ዘርፉ የተሻለ ገቢ የምታገኝበት፣ ወደ ሌላ ሥራ የምትሸጋገርበት፣ የሥራ ባህልን የምታዳብርበት… እንደሆነ ነግራናለች:: የ22 ዓመቷ ወጣት እንደምትለው የአብዛኛው ሥራ ፈላጊም ሆነ ወላጅ የሥራ ባህል ሊለወጥ ይገባል:: ዝቅ ብሎ ከመሥራት ያለ ሥራ መቀመጥን የተሻለ አድርገው የሚገምቱ አሉ:: ብዙ ጊዜ ወላጆች ልጆች ከተማሩ በተማሩበት ትምህርት ዘርፍ አሊያም ደግሞ ሀብት ካላቸው ያለምንም የገበያ ጥናት ሰዎች አተረፉበት፣ አደጉበት በተባለ ንግድ እንዲሰማሩ ይፈልጋሉ:: ይህ ኪሳራ እንጅ ትርፍ አያመጣም::
ወጣቷ የተሰማራችበት ሥራ ትልቅ ባይሆንም ዝቅ ብላ በመሥራቷ አንዳንድ ጓደኞቿ እንደሚያበረታቷት ትናገራለች:: አሁን ላይ ከምታገኘው ገቢ ለቤት ኪራይ በወር አንድ ሽህ አምስት መቶ ብር ትከፍላለች:: የምስራች ከራሷ አልፋ ቤተሰቦቿን የማገዝ ዓላማ ሰንቃለች::
ደንበኞቿ በወጣቷ አገልግሎት አሰጣጥ ደስተኛ እንደሆኑ እኛም በሥራ ቦታዋ ተገኝተን አረጋግጠናል:: የሥራን ክቡርነት ተገንዝበው በተራ ያለምንም የፆታ ልዩነት የደንበኞቻቸውን ጫማ ከሚያሳምሩት መካከል አንዷ የሆነችው የምስራች እርሷም ቢሆን ደንበኛቿን ለማሳደሰት ትፈልጋለች::
በመጨረሻም ወጣቷ በተለይ ወላጆች ሁሉንም ሥራ እኩል አድርጎ ያለመመልከት ግንዛቤያቸውን በመለወጥ ዝቅ ብሎ የሚሠራን ማበረታታት እና ሊኮሩበትም እንደሚገባ መክራለች::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here