የሥራ ውል የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች

0
70

የአሠሪ እና ሠራተኛ  ሕግ ታሪካዊ ዳራ ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ሥርዓት መምጣትን ተከትሎ በሠራተኛው ላይ ይደርስ የነበረውን የጉልበት ብዝበዛ እና አመቺ ያልሆነ የሥራ ቦታ ለማስተካከል የወጣ ሕግ ነው:: ሕጉ  ከሌሎች ሕጎች አንፃር የቅርብ ጊዜ ስለመሆኑ በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ   ዓቃቢ ሕግ ባለሙያ አቶ ስማቸው አያሌው ገልፀውልናል::

 

እንደ ዓቃቢ ሕግ ባለሙያው ማብራሪያ ቀደም ብሎ ሥራ ላይ የነበረው አዋጅ 377/1996 እንደገና በአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011  ተተክቶ ሥራ ላይ እንዲውል ሆኗል::

አዋጁ ሲወጣ ዓላማ አድርጎ የያዘው  ሠራተኛው ከሥርዓት ውጭ ወይም ያለአግባብ እንዳይባረር፣ የሥራ ዋስትና እንዲኖረው፣ ሠራተኛው ግዴታውን እንዲያውቅ፣ የሥራ ሰዓት፣ የእረፍት ሁኔታ፣ የስንብት ክፍያ … በጠቅላላው የአሠሪ እና ሠራተኛ ግንኙነትን በመቆጣጠር የኢንዱስትሪ ሰላም በማስፈን ምርት እና ምርታማነትን መጨመር ነው::

ሕጉ በዋናነት በአሠሪ እና ሠራተኛው መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን አስቀድሞ ባወቀው  እና በተግባባበት ሕግ እንዲመራ የሚያደርግ ነው:: አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ከአንቀጽ 23 እስከ 33 ድረስ  ያሉት ድንጋጌዎች ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች ተጠቅሰዋል:: በዚህ ጽሑፍም በአንቀጽ 27 ስር የተመለከቱትን ዝርዝር ሁኔታዎች  ባለሙያው አብራርተዋል::

 

የሥራ ሰዓት አለማክበር

የማንኛውም ሠራተኛ መደበኛ የሥራ ሰዓት በቀን ስምንት ወይም በሳምንት ከአርባ ስምት ሰዓት አይበልጥም:: ስለዚህ አንድ ሠራተኛ መደበኛ የሥራ ሰዓቱን   አክብሮ መገኘት የግድ ይለዋል:: ነገር ግን አንድ ሰው ሰዓቱን ሳያከብር የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በስድስት ወር ውስጥ በጠቅላላው ለስምንት ጊዜ የሥራ ሰዓት ያላከበረ ሠራተኛ የሥራ ውሉ ያለማስጠንቀቂያ እንደ ሚቋረጥ በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (1) (ሀ) ላይ ተመልክቷል::

 

ከሥራ ገበታ መቅረት

በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (1) (ለ) እንደተመላከተው “የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በስድስት ወር ውስጥ ለአምስት ቀናት ከሥራ መቅረት የሥራ ውልን ያለ ማስጠንቀቂያ ያቋርጣል:: በዚሁ አንቀፅ ስር እንደተመላከተው ያለበቂ ምክንያት ከሥራ መቅረት የሥራ ውል ለማቋረጥ የሚያስችል ሲሆን በይዘቱ ሲታይ ደግሞ የቀድሞው አዋጅ ዝርዝር ጊዜውን ከፋፍሎ አስቀምጧል::  በ2011 ዓ.ም የወጣው አዋጅ የጊዜ አቀማመጥ ላይ መጠነኛ ልዩነት ያለው ቢሆንም በስድስት ወር ውስጥ አምስት ቀን ከሥራ መቅረት ለስንብት የሚያበቃ ጥፋት በመሆኑ አሠሪው  በየጊዜው ማስጠንቀቂያ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት  ያሳያል::

ሠራተኛው በተለያዩ ቀናት በመደዳው ሳይሆን አልፎ አልፎ በድምሩ ከአምስት ቀናት በላይ ከሥራ መቅረቱ ቢረጋገጥም በዚህ ምክንያት የሥራ ውሉን ለማቋረጥ የሚቻለው አሠሪው በተደጋጋሚ በጽሑፋ ማስጠንቀቂያ የሰጠው መሆኑ ሲረጋገጥ ስለመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (1) (ለ) ድንጋጌ ይዘት ያስገነዝባል::

 

በሥራው ላይ የማታለል ተግባር መፈጸም

በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (1) (ሐ) መሰረት በህብረት ስምምት በሌላ አኳኋን ካልተወሰነ በስተቀረ የሥራ ውልን ያለ ማስጠንቀቂያ ማቋረጥ ከሚቻልባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ሠራተኛው በሥራው ላይ የማታለል ተግባር ሲፈጽም ነው:: ለራሱም ሆነ ለሌላ ሰው ብልፅግና በመሻት የአሠሪውን ገንዘብ /ንብረት ያለ አግባብ መጠቀም የማባረሪያ ምክንያት ነው ተብሎ ተቀምጧል:: በዚህም ቀጣሪ ተቋሙ በሥራ ቦታ አምባጓሮ /ጠብ/ ያጫረ ከሆነ፣ ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት በድርጅቱ ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ያለ ማስጠንቀቂያ ውል ሊያቋርጥ ይችላል::

 

የሠራተኛው መታሰር

በአዋጁ አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (1) (በ) ላይ እንደተጠቀሰው በአንድ ሠራተኛ ላይ ከ30 ቀናት ለሚበልጥ ጊዜ የእስራት ፍርድ ተወስኖበት ከሥራ ከቀረ የሥራ ውሉ ያለ ማስጠንቀቂያ የሚቋረጥ ይሆናል:: የሥራ ውል ለማገድ ከሚያስችሉ ሌሎች ምክንያቶች አንዱ ሠራተኛው ከሰላሳ ቀናት ላልበለጠ ጊዜ መታሰር ነው::

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ አንዳንዴ  ከሥራው ባህሪ አንፃር ለሥራው ብቁ ሆኖ  አለመገኘት ያጋጥማል:: ለምሳሌ ገንዘብ ያዥ ወይም ንብረት ክፍል ሠራተኛ በእምነት ማጉደል ወንጀል ጥፋተኛ ቢባል  ወደ ነበረበት ቦታ ሲመለስ ሥራውን በአግባቡ ይሠራል ተብሎ  አይታመንም:: በመሆኑም ባለሙያው  በወንጀል የሚጠየቀው ጥፋተኛ ሆኖ በእምነት ማጉደል ብቻ ሳይሆን  ለያዘው ሥራ ብቁ አለመሆን አብሮ ሊታይ የሚችል ነው::

 

ከአቅም በታች ሥራ መሥራት

በአዋጁ አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (1) (ሠ) ላይ በተጠቀሰው መሰረት ሠራተኛው ሥራውን ለማከናወን ችሎታ እያለው የሥራ ውጤቱን ባለማቋረጥ ወይም በሥራ ደንቡ ወይም በሁለቱ ወገኖች መግባባት ከተወሰነው የምርት ጥራት እና መጠን በታች ሲሆን የሥራ ውሉ ያለ ማስጠንቀቂያ ሊቋረጥ ይችላል::

 

የማሰናበቻ ምክንያቶች በጽሑፍ ለሠራተኛው መገለጽ ያለባቸው ስለመሆኑ

አሠሪው ከዚህ በላይ የተጠቀሱትና ሌሎች በዚህ ጽሁፍ ባልተሸፈኑ በአዋጁ አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (1) ስር በተዘረዘሩ ምክንያቶች የሠራተኛውን የሥራ ውል ያለ ማስጠንቀቂያ የሚያቋርጥ ከሆነ በአንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (2) መሰረት የሥራ ውሉን በሚያቋርጥበት ጊዜ የሥራ ውሉ የሚቋረጥበትን ምክንያት እና ቀን በመጥቀስ ለሠራተኛው በጽሑፍ መግለጽ አለበት::

 

የሥራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ የ30 ቀነ ገደብ ያለው ስለመሆኑ

በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (1) መሰረት አሠሪው የሥራ ውልን ያለ ማስጠንቀቂያ የሚያቋርጡ ምክንያቶች በሚያጋጥሙት ጊዜ በአዋጁ አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (3) መሰረት የሥራ ውሉን ሊያቋርጥ የሚችለው ውሉ የሚቋረጥበት ምክንያት መኖሩን ባወቀ በ30 የሥራ ቀናት ውስጥ ነው:: ጉዳዩን ካወቀ 30 የሥራ ቀናት ያለፉ እንደሆነ ሠራተኛውን የማሰናባት መብቱ በይርጋ ቀሪ ይሆናል::

በዚህ ይርጋ መሰረት አሠሪው በሕጉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ የሠራተኛውን ውል የማቋረጥ ርምጃ ሳይወስድ ቆይቶ ጊዜው ካለፈ በኋላ ውል ያቋረጠ እንደሆነ ሠራተኛው የጊዜ ገደቡ ባለፈበት ድርጊት ተጠያቂ እንዳይሆን መብት ስለሚሰጠው  ስንብቱ ሕገ-ወጥ ነው በማለት ክርክር ሊያቀርብ ይችላል::

 

የሥራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ከመቋረጡ በፊት ሠራተኛውን ለ30 ቀናት አግዶ ማቆየት ስለሚቻልበት ሁኔታ

በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (4) እንደተጠቀሰው በአንቀጽ 27 ንኡስ አንቀፅ (1) መሰረት የሥራ ውሉን ያለ ማስጠንቀቂያ የሚያቋርጡ ክስተቶች ሲፈጠሩ የሠራተኛው የሥራ ውል እንዲቋረጥ ከመደረጉ በፊት ሠራተኛውን ከሥራ አግዶ ማቆየት ሰለሚቻልበት ሁኔታ አሠሪው በህብረት ስምምት ሊወሰን ይችላል:: ሆኖም የእገዳው ጊዜ ከ30 የሥራ ቀናት መብለጥ የለበትም:: በመጨረሻ ግን ሠራተኛው በነዚህ ምክንያቶች ከሥራ ሲሰናበት የስንብት ክፍያ አያገኝም::

 

የህግ አንቀጽ

ነፍሰጡር የሆነች ሴትን አሠሪው የማሰናበት ሥልጣን እንደሌለው የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 87 ንኡስ ቁጥር (6) ይደነግጋል፡፡

  • የሥራ ስንብት ክፍያን በተመለከተ የተሻረው አዋጅና ማሻሻያ ድንጋጌዎቹ ላይ የሰፈሩት ምክንያቶች ሲሟሉ በአዲሱ አዋጅ አንቀፅ 39 ንኡስ ቁጥር (1) (መ) ስር ተካቷል፡፡
  • አንድ ሠራተኛ የተለያዩ ፈቃዶችን የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ ለመጀመሪው የአንድ ዓመት አገልግሎት የሚሰጠው የፈቃድ መጠን አሥራ ስድስት (16) የሥራ ቀናት ነው፡፡
  • አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 85 መሠረት የሕመም ፈቃድ ሠራተኛ በሥራ ላይ በሚደርስ ጉዳት ሳይሆን በሌላ ሕመም ምክንያት ሥራ ለመሥራት ካልቻለ ያገኛል፡፡ ይህም ፍቃድ በአንድ ዓመት ውስጥ በማንኛውም ሁኔታ ከስድስት ወር አይበልጥም፡፡

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የነሐሴ 5  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here