የሥርዓተ ምግብ ዋስትና – መስኖ

0
13

የአማራ ክልል የ25 ዓመት አሻጋሪ እና ዘላቂ ልማት ዕቅድ የክልሉ ምጣኔ ሃብት 50 ከመቶ የሚመነጨው ከግብርና እንደሆነ ነው የሚያመለክተው።

በልማድ በቆየው ዝናብን ጠብቆ በማልማት  ብቻ ግን የሚፈለገውን ያህል በምግብ ራስን መቻል (የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ) አይቻልም፤ መስኖን በመጠቀም በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ ማምረት ደግሞ የችግሩ መሻገሪያ ነው:: ይህም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ ገቢን ያስገኛል::

አሁን ያለንበት ወቅት (የክረምቱን ማለፍ እና የበጋውን መምጣት ተከትሎ) በመደበኛው የግብርና ሥራ የለሙ ሰብሎች የሚሰበሰቡበት እና ለበጋ መስኖ ደግሞ ዝግጅት የሚደረግበት ነው:: ይህን ተከትሎ ታዲያ የአማራ ክልልም ለዚሁ ተግባር ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

ክልሉ ከፍተኛ የከርሰ ምድር እና ገጸ ምድር  ውኃ ባለቤት ነው፤ ይህን ጸጋ በመጠቀም የተሻለ ምርት ለማምረት የመስኖ ማስጀመሪያ ንቅናቄ ከክልል ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ካሉ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር እየተደረገ ነው። ለአብነትም የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ከሚመለከታቸው ጋር በባሕር ዳር ከተማ ምክክር አካሂዷል።

ከመምሪያው የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በ2018 የመጀመሪያ ዙር መስኖ ከ33 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ይለማል ተብሎ ይጠበቃል።

በሰሜን ጎጃም ዞን የሰሜን አቸፈር ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሥ አለነ እንደሚሉት ወረዳው ከፍተኛ የመሥኖ አቅም ካላቸው አካባቢዎች አንዱ ነው:: በመጀመሪያው ዙር  የመስኖ ልማትም 2457 ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ ተግብቷል:: በዚህም 350 ሺህ ኩንታል ያህል ስንዴ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ስድስት ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ተደራሽ ይደረጋል፤ የማሳ ልየታም ተካሂዷል::

አቶ ንጉሥ እንዳሉት በሄክታር እስከ 36 ኩንታል ምርት ለማግኘት ታስቧል:: ለዚህም አስፈላጊ ግብዓቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ ነው:: በመስኖ ልማቱ (በአትክልት እና በጋ ስንዴ) 12 ሺህ 800 ህል አርሶ አደሮች ተሳታፊ ይሆናሉም ብለዋል።

ከበጋ ስንዴ በተጨማሪ ድንች፣ ቀይ እና ነጭ ሽንኩርት እንዲሁም ቲማቲም በመስኖ ሥራው በስፋት የሚለሙ ናቸው።

የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እያደገ መምጣቱን የገለፁት ኃላፊው የወረዳው ማሳ በብዛት የዓባይ እና ጣና ክላስተር (ኩታ ገጠም) በመሆኑ አርሶ አደሩ የውኃ መሳቢያ ሞተር (ፓምፕ) በመጠቀም ያለማል ነው ያሉት።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ባለፈው ዓመት ስንዴን ከሕብረት ሥራ ማሕበራት ጋር የሚበላሹ ምርቶች እንዳይባክኑ ደግሞ ከንግድ ተቋማት ጋር በማቀናጀት ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የይልማና ዴንሳ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌትነት አሰፋ እንዳሉት ደግሞ በ2018 የመሥኖ ልማት ከሦስት ሺህ 118 ሄክታር መሬት በላይ በመጀመሪያው ዙር ይለማል፤ ከዚህ ውስጥ አንድ ሺህ 200 ሄክታር ያህሉ በስንዴ የሚለማ ነው።

ለሥራውም ሦስት ሺህ 500 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ተሠራጭቷል፤ 987  የውኃ መሳቢያ ሞተሮችም በሥራ ላይ ናቸው:: 11 ካናሎች (የመስኖ ውኃ ማፋሰሻ ቦይ) ደግሞ ተጠርገው ዝግጁ ናቸው:: በአካባቢው ያሉት ምንጮችም የውኃ አማራጭ ሆነው ጥቅም ላይ ይውላሉ::

አካባቢው የቆላ የደጋ ፍራፍሬ፣ ድንች፣ ነጭ እና ቀይ ሽንክርት በብዛት ይመረታል።

ሌላው ሐሳባቸውን የሰጡን የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ደሳለኝ አድማሴ ናቸው፤ ወረዳው የመሥኖ ልማት ልምድ ያለው መሆኑን ያነሱት ኃላፊው በዚህ ዓመትም 11 ሺህ 134 ሄክታር መሬት በመስኖ ይለማል ነው ያሉት፤ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶም ነው ወደ ሥራ የተገባው:: አስፈላጊ የአፈር ማዳበሪያም በቅርቡ እንደሚሰራጭ ተናግረዋል፤ ስንዴ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ በአካባቢው በስፋት ይመረታሉ።

አቶ ደሳለኝ እንደነገሩን ከአራት ሺህ 600 በላይ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች በሥራ ላይ ናቸው፤ በዚህ ዓመትም 80 አዲስ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን ለማቅረብ ታቅዷል። በፀሐይ ብርሃን የሚሠሩ አራት ሞተሮችን ለማቅረብም ታስቧል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ በለጠ ጥጋቡ እንደገለፁት የክልሉን የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት እና የአምስት ዓመቱን ዕቅዶች ለማሳካት በተለይ መስኖ እና ተፈጥሮ ሃብት በትኩረት ይሠራል።

በዞኑ በ2018 በጀት ዓመት ከ33 ሺህ 543 ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ይለማል፤ ከዚህ ውስጥ 21 ሺህ ሄክታሩ (62 ከመቶ ያህሉ) በመጀመሪያው ዙር መስኖ በበጋ ስንዴ ይሸፈናል።

ዘጠኝ ሺህ ያህል የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ዝግጁ መሆናቸው እና 56 ዘመናዊ ካናሎች መኖራቸው ለሥራው ውጤታማነት ትልቅ አቅም ናቸው፤ ቆጋን ጨምሮ በርካታ ወንዞች መኖራቸውም ዕቅዱን ለማሳካት እንደሚያስችሉ ነው ያነሱት።

መምሪያ ኃላፊው እንደተናገሩት በበጋ መስኖ ስንዴ ከሚለማው 21 ሺህ ሄክታር መሬት 882 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል፤ ከ21 ሺህ ሄክታር ውጭ ያለው መሬት ደግሞ በቅመማ ቅመም እና በቋሚ አትክልቶች እየለማ ነው። ለአብነትም 560 ሄክታር መሬት በአቮካዶ እየለማ ይገኛል።

ለሥራውም 63 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ (ዳፕ እና ዩሪያ) ያስፈልጋል፤ ይህ ደግሞ በመጋዘን ስላለ ችግር እንደማይኖር አረጋግጠዋል።

የሕብረት ሥራ ማሕበራት ገበያ በማፈላለግ አቀናጅተው እንደሚመሩት የገለፁት አቶ በለጠ ሌሎች የተደራጁ ማሕበራትም ስለሚገዙ የገበያ ችግር አይገጥምም ብለዋል፤ ስንዴ ከተሰበሰበ በኃላ ደግሞ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ይቀጥላል፤ በትንንሽ ማሳዎች ደግሞ ከመጀመሪያው ዙር ጀምሮ አትክልትና ፍራፍሬ ይለማል። የስንዴ ለማት በብዛታ በኩታ ገጠም (በክላስተር) የሚለማ መሆኑንም ተናግረዋል::

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሺፈራው የክልሉን ያለፈ ዓመት የመስኖ ልማት አፈፃፀምና የዘንድሮውን ዕቅድ ከሰሞኑ በነበረ የባለድርሻ አካላት ምክክር አቅርበዋል።

ግብርናን ከዘመናት የዝናብ ጥገኝነት የማውጣትና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ሰፊ በመስኖ የሚለማ መሬት መኖርና ያንንም አቅም ለመጠቀም እና የምግብና የሥርዓተ ምግብ ችግሮች መፍቻ ምንጭ መስኖ ልማት መሆኑንም አንስተዋል።

የአማራ ክልልን እምቅ የመስኖ አቅም በስፋት ለመጠቀም አዲስ መስኖ ልማት ላይ ርብርብ መደረግ አለበት ያሉት አቶ ቃልኪዳን በዚህ ዓመት 51 ሺህ 781 ሄክታር መሬት በአዲስ በመስኖ ለማልማት መታቀዱን ተናግረዋል።

አቶ ቃልኪዳን ሺፈራው አክለውም በክልሉ በ2018 ዓ/ም በበጋ መስኖ ስንዴ 260 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 10 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ስለመታቀዱም አስረድተዋል። በክልሉ የፍራፍሬ ልማትን ለማሳደግም በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴን በማምረት ለተቀመጠው ሀገራዊ ግብ አስተዋፅኦ በማድረግ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘትና የሀገር ውስጥ አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት ማሟላት እና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው በመስኖ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የህብረተሰቡን ስርአት ምግብ ዋስትና ማሻሻል እና ከፍተኛ የሥራ እድል መፍጠሪያ ማድረግም ያስፈልጋል ብለዋል።

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here