ኢትዮጵያ ክብሯን ከወራሪ ሲጠብቁ በየጦር አውዱ የተሰዉላት ቆራጥ የጀግና ዘሮች እንዳሏት ሁሉ የሀይለኞችን መንደር የሚያሸብር፣ የአምባገነኖችን መሰረት የሚያናውጥ፣ የክፉዎችን የክፋት ጫካ መንጣሪ፣ የጭቁኖችን እምባ አባሽ ሃያል ብእር ያላቸው ጉምቱ የብእር አርበኞችንም አፍርታለች።
የተለየ ሀሳብን በይፋ መናገር ይቅርና ለሚያምነው ወዳጁ እንኳ በሹክሹክታ መንገር እጅግ በሚያስፈራበት በዚያ ወቅት ዉስጡ የሚሰማውን የሚናገር ካለ እንኳ ያ ሰው በርግጥም በህይወቱ የቆረጠ የታላቅ መርህ ሰው መሆን አለበት። አልፎ አልፎ በእንዲህ አይነት ፅኑ የህይወት መርሆ ላይ ቆሞ ወለም ዘለም ሳይል ወደ ግቡ የሚገሰግስ አንዳንድ ሰው ሊገኝ ይችላል። በጣት የሚቆጠሩ እንደዚህ ያሉ፣ ጥቂት ግን የሚሊዮኖች ግምት፣ ከራስ ይልቅ ለሌሎች ኖሮ ለማለፍ የቆረጡ ምናልባትም በመቶ ዓመታት አንዴ የሚከሰቱ አንዳንድ ሰዎች ይኖራሉ። እነርሱም ዓለምን ቀይረዋል፤ ፍትህ ለተጓደለባቸው እንደ ዋስ ጠበቃ፣ ለግፈኞች እንደ ፍም እሳት የሚፋጁ፣ የሌሎች ስቃይ ግድ የሚላቸው፣ የማህበረሰቡን ሸክም የተሸከሙ የየሀገራቱ ጀግኖች አሉ። እኛም አሉን፤ ብዙ አርበኞች። ለሞት እንኳ ያልተበገሩ መርሆን ተከትለው ፀንተው ያለፉ የሀገር ኩራቶች አሉን።
ባልተጠበቀ እና ወሳኝ የሽግግር ወቅት የኢትዮጵያ ፀሐፊዎች ከባህላዊው የሥነ ፅሑፍ ሚናቸው ያለፈ ሀላፊነት ተሸክመዋል። የእነርሱ ስራ ክስተቶችን መሰነድ ወይም አፈ ታሪኮችን መከሸን ብቻ አይደለም:: ነገር ግን የባህል መስተጋብር ጠባቂ፣ የእውነታ ደጋፊዎች እና የጋራ ድምፅ አስተጋቢዎችም ናቸው።
ታሪክ ከብእር በስተቀር ሌላ ያልታጠቁ እና ለእውነት ፍንክች የማይል ጥብቅና፣ ለጭቆና እና ለሀሰት በጠላትነት በሚቆም የፀሀፊያን አብነቶች የተሞላ ነው። እነዚህ አብነቶች በማህበረሰብ ውስጥ የፀሀፊን ሚና እና አቅም የሚያስታውሱ ናቸው። ከእነዚህ መሀል አንዱ በኢትዮጵያ ሥነ ፅሑፍ ውስጥ ትልቅ ክብር የተጎናፀፈው በአሉ ግርማ ተቀዳሚ አብነት ይሆናል። በማይበገር መንፈሱ እና በማይዋዥቅ እምነቱ የሚታወቀው በአሉ ግርማ ስራዎቹን የእርሱን ዘመን አስከፊ እውነታዎች ለማሳየት ተጠቅሞባቸዋል። በፖለቲካ ማእበል ወይም ነውጥ መሀል እንኳ የእርሱ ስራዎች ያለምንም ፍርሃት የኢትዮጵያውያንን የእለት ተእለት ትግል ያንፀባርቁ ነበር። የእውነት ደጋፊ መሆኑ በአሉን ዋጋ አስከፍሎታል:: ማለትም ለእውነት ዋጋ ከፍሎላታል፤ የታገላቸው ኃይሎች ሕይወቱን ነጥቀውታል።
ሌላው ጀግና አቤ ጉበኛ ነው፤ ለመፃፍ የተወለደ፣ ለመፃፍ የኖረ፣ በመፃፍም ዋጋ የከፈለ፣ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጉምቱ ደራሲያን አንዱ ነው። ስሙን ከመቃብር በላይ የሚያስጠሩ ብዙ ሥራዎችን ሠርቶ ያለፈ፣ ምንጊዜም ኢትዮጵያ የማትረሳው ጀግናዋ ነው። አቤ የተከበረ የአገሪቱ ጋዜጠኛና ደራሲ ነበር።
አቤ የሥነ ፅሑፍ ስራውን የጀመረው በ1942 በጤና ሚኒስቴር እየሰራ ባለበት ተውኔቶችን በመፃፍ ነበር። በማከታተልም አቤ ካበረከታቸው ስራዎቹ፦ ከመቅሰፍት ስራዊት ይጠንቀቅ ሰውነት፣ የሮም አወዳደቅ (1953)፣ የፓትሪክ ሉሙምባ አሳዛኝ አሟሟት (1954)፣ የአመፅ ኑዛዜ፣ አልወለድም፣ the savage girl፣ የፍጡራን ኑሮ፣ የራኄል እምባ (1956)፣ የደካሞች ወጥመድ (1965)፣ ፖለቲካና ፖለቲከኞች (1969)፣ ቂመኛው ባህታዊ፣ መልክአም ሰይፈ ነበልባል፣ defiance.፣ የረገፉ አበቦች፣ ጎብላንድ፣ አጭበርባሪው ጦጣ፣ አንድ ለእናቱ፣ እድል ነው በደል እና ሌሎቹም ተጠቃሽ ናቸው። ቂመኛው ባህታዊ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴያትር ለሕዝብ ያሳየው የመጀመሪያ ተውኔቱ ሲሆን አልታተመም። ነገር ግን ለህትመት ከበቁት ተውኔቶቹ ውስጥ፣ የደካሞች ወጥመድ እንዲሁም ፖለቲካና ፖለቲከኞች የተሰኙት ሁለቱ ብቻ ናቸው መድረክ ላይ የታዩት። የራኄል እምባ የተሰኘው ሶስተኛ ተውኔቱ በመፅሐፍ ቅዱሳዊ ጭብጥ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ለመድረክ እይታ እንዳይበቃ ተደርጓል:: ዋነኛ ምክኒያቱም አሰቃቂው የራሄል የባርነት ታሪክ ለባለስልጣናቱ ሊዋጥላቸው ባለመቻሉ ነው። ለዚህም ይመስላል በመግቢያው ላይ እንዲህ የፃፈው፣ ይህ ቲያትር ከተፃፈ ጥቂት ዓመታት አልፈዋል። በመድረክ ለመታየትም ተመድቦ ነበር:: ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ለተንቀሳቃሽ የሆሊውድ ፊልም ወይም ለዚያ ቦታ አግባብ ላለው ካልሆነ በቀር ለእኔ ቲያትር ጊዜ ባለመገኘቱ ሳይታይ ቀርቷል፤ ግድ የለኝም፣ ካሳተምኩት ይበቃኛል።
አቤ ጉበኛ በበርካታ ሀያሲያን ዘንድ ከፍሬያማዎቹ ዘንድ ይፈረጃል። ለአብነት መንግስቱ ለማ ስለ አቤ ሲገልጹ፣ “በዘመናዊ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ የሽያጭ ደረጃ የያዙ ስራዎቹን በመፃፍ ወደር ያልተገኘለት ታታሪ ሰው ነው” ብለዋል።
አልወለድምና መልከአ ሰይፈነበልባል በተሰኙ ሁለት የልብ ወለድ ስራዎቹ አቤ በሀገሪቱ ያለውን ማህበራዊ ኢፍትሃዊነት በቆራጥነት በመተቸትና የኢኮኖሚ ለውጥን በማቀንቀን ድፍረቱን አስመስክሯል። የጊዜውን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በቻለው መጠን በሀቀኝነት በማጋለጥ ከጊዜው የቀደመ ይሉለታልም። የዘመኑን ያረጀ አገዛዝ ያለምንም ርህራሄ ክፉኛ ይነቅፍ ነበር። ስራዎቹ በጥቅሉ ወጣቱን አካባቢውን እና ራሱን ዞር ብሎ በደስታ እንዲመለከት እና ራሱን እንዲመረምር ያስቻሉ ናቸው።
አቤ ወደ መጨረሻዎቹ ጊዜያት ያረጀውን የዘውድ አገዛዝ የተካውን ማርክሲስታዊ ርእዮት በሚያቀነቅነው የደርግ አገዛዝ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋ እየቆረጠ መጣ። በመሆኑም የደርግን መንግስት በመቃወም በግልጽ ይናገር እንደነበር ታሪኩን የፃፉ ምሁራን ይናገራሉ። በ1972 ዓ.ም ጥር ወር ውስጥ ስራዎቹን ለማሳተም ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ በሄደበት ወቅት አንድ ሆቴል ውስጥ ተገድሎ ተገኘ። አሟሟቱ እጅግ በረቀቀ መንገድ የተፈፀመ በመሆኑ ልክ እንደ በዓሉ ግርማ የገዳዩ ማንነት እስካሁን ምስጢር እንደሆነ ቀርቷል።
ዳኛቸው ወርቁ ብእርን ለማህበረሰብ ባህል እድገት ፍሬን ከእብቅ እንደሚለያይ መንሽ መጠቀም የቻለ ግን በዘመኑ ካለው ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ግንዛቤ የመረዳት አቅም በላይ ሆኖ እርሱን የሚረዳው ትውልድ ወይም ዘመን እስኪነሳ ለመጠበቅ የተገደደ ስራ “አደፍርስ”ን ያበረከተ ነው።
በ1970 ዓ.ም አካባቢ የታተመው አደፍርስ የኢትዮጵያን ማህበረሰብ ከአብዮቱ በፊት ከሩቅ አሻግሮ ማየት የቻለ ታላቅ ስራ ነው።
የዳኛቸው ወርቁ የመጀመሪያው በአማርኛ ቋንቋ የፃፈው ድርሰቱ አደፍርስ ወዲያው ያገኘው አቀባበል ጥሩ አልነበረም። የቋንቋ እና የጭብጥ ድክመት እንዳለበት በፀሀፊያን እና በምሁራን ዘንድ ነቀፋ ስለገጠመው የሚረዳኝ ትውልድ እስኪነሳ በሚል መፃህፎቹን ከገበያ እየገዛ እስከመሰብሰብ ደርሶ ነበር። ሆኖም ስራው በአሁኑ ወቅት እንደ ትልቅ አብነት የሚጠቀስ ታላቅ ስራ ተደርጎ ክብር ተጎናፅፏል።
ምንጭ – DEFIANCE, A POSTCOLONIAL NOVEL BY THE ETHIOPIAN ABBIE GUBEGNA: THE RIGHTS OF A FREE PEOPLE UNDER ITALIAN FASCISM
-The Reporter, website
-በግሎባል ሳይንቲፊክ ጆርናል ላይ በ2012 ዓ.ም ላይ ባሳተሙት ጥናታዊ ፅሑፍ: ዶ/ር ደመቀ ጣሰው
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ሰኔ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም