በክፍል አንድ በባሕር ዳሩ ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ የሆኑት መምህር ቃለ ጽድቅ አየነው የዐብይ ጾምን በተመለከተ ለአሚኮ በርከት ያሉ መረጃዎችን መስጠታቸው የሚታወስ ነው። ሁለተኛ እና የመጨረሻ ክፍሉን ደግሞ በዚህ መልኩ አሰናድተነዋል። መልካም ንባብ!
ቀሪዎቹን የዐብይ ጾም ሳምንታት ያብራሩልን?
ሦስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹ምኵራብ› ይባላል:: ምኵራብ አምልኮተ እግዚአብሔር ሲፈጸምበት፣ ሕገ ኦሪት ሲነበብበት የነበረ፣ በአይሁድ የሚሠራ መካነ ጸሎት ነው:: ዘወትር ቅዳሜ ብዙ ሕዝብ ይሰበሰብበት ስለ ነበር ጌታችን ለማስተማር ብዙ ጊዜ በምኵራብ ተገኝቷል:: ስያሜው የተወሰደው በዮሐንስ ወንጌል “በመቅደስም በሬዎችን፣ ላሞችን፣ በጎችን እና ርግቦችን የሚሸጡትን አገኘ …” ተብሎ ከተገለጸው ላይ ሲሆን “ምኵራብ” የሚለው ቃልም በአማርኛ “መቅደስ” ተብሎ ተተርጉሟል:: ምኵራብ የሚባለው ሳምንት ጌታችን ወደ ምኵራብ ገብቶ ማስተማሩ የሚነገርበት “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፤ እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት” ብሎ በምኵራብ ይሸጡ፣ ይለውጡ የነበሩትን የገሠፀበት፣ ቤተ መቅደስን የከብት መንጃ፣ የወርቅ እና የብር መነገጃ ያደረጉ ሰዎችን ከነሸቀጣቸው ከቤተ መቅደስ ያስወጣበት፣ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ የስሙ መጠሪያ እና የጸሎት ሥፍራ መሆኗን ያስረዳበት እና ያወጀበት፣ በቤተ መቅደስ የንግድ ሥራ ማከናወን እንደማይገባ ያረጋገጠበት ዕለት ነው::
አራተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት “መጻጒዕ” ይባላል:: ስያሜው በዮሐንስ ወንጌል ላይ ከሚገኘው ኃይለ ቃል የተወሰደ ነው:: በዚህ የወንጌል ክፍል ጌታችን በቤተ ሳይዳ ሕሙማንን እንደ ፈወሰ ተነግሮአል:: ብዙ ሕሙማን ፈውስ ሽተው አንዲት የመጠመቂያ ሥፍራን ከበው ይኖሩ ነበር:: በዚያች ሥፍራ ቀድሞ የወረደ እና የተጠመቀ አንድ በሽተኛ ብቻ ይፈወስ ነበር:: ጌታችን በዚህ ሥፍራ ተገኝቶ በሽተኞችን ጐብኝቷል:: በዚያም ልዩ ልዩ ደዌ ያለባቸው አምስት ዓይነት ሕሙማን እንደ ነበሩ ተገልጧል፤ እነዚህም፡- ሰውነታቸው የደረቀ፣ የሰለለ እና ያበጠ፤ እንደዚሁም ዕውራን እና አንካሳን ነበሩ:: ከዚህ አምስት የተለያየ ዓይነት በሽታ ከተያዙ ሰዎች መካከል ደዌው የጸናበት፣ ለ38 ዓመታት በደዌ ዳኛ፣ ባልጋ ቍራኛ ተይዞ የኖረው፣ ከደዌው ጽናት የተነሣ “መጻጒዕ” ተብሎ የተጠራው በሽተኛ አንዱ ነበር:: መጻጒዕ ስም አይደለም፤ ደዌ የጸናበት በሽተኛ ሕመምተኛ ማለት ነው እንጂ:: ሰውየው ከበሽታው ጽናት የተነሣ ስሙ ጠፍቶ በበሽታው ሲጠራ የነበረ ነው:: አምላካችን ይህን ሰው “አልጋህን ተሸክመህ ሒድ” ብሎ 38 ዘመን የተኛበትን አልጋ ተሸክሞ ወደ ቤቱ እንዲገባ ማድረጉ የሚነገርበት ወቅት በመኾኑ ሳምንቱ “መጻጒዕ” ተብሎ በተፈወሰው በሽተኛ ስም ተሰይሟል:: ዛሬም ቢኾን በሰዎች ላይ ልዩ ልዩ ደዌያት አሉ፤ የሥጋን ደዌ ሐኪሞች ያውቁታል፤ ከዚህ የከፉት የነፍስ ደዌያት ግን እጅግ ብዙዎች ናቸው:: በኃጢአት ብዛት ልባቸው የደረቀ እና ያበጠ፣ ሰውነታቸው የሰለለ፣ ዓይነ ሕሊናቸው የታወረ፣ እግረ ልቡናቸው የተሰበረ ብዙዎች ሕሙማን አሁንም አሉ:: ፈውስን ይሻሉ፣ ድኅነትን ይፈልጋሉ:: እንደ መጻጕዕ ቦታቸውን ሳይለቁ እግዚአብሔርን በተስፋ ቢጠብቁት አንድ ቀን ይፈወሳሉ::
አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት “ደብረ ዘይት” ይባላል:: ስያሜው የተወሰደውም በማቴዎስ ወንጌል ካለው ትምህርት ነው:: ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኝ በወይራ ዛፎች የተሸፈነ ትልቅ ተራራ ነው:: ጌታችን ምሥጢራትን በተለያየ ቦታ ገልጧል:: ምሥጢረ ጸሎትን በጌቴሰማኒ፣ ምሥጢረ መንግሥቱን በደብረ ታቦር፣ ምሥጢረ ቊርባንን በቤተ አልዓዛር፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን በቤተ ኢያኢሮስ እና ምሥጢረ ምጽአቱን በደብረ ዘይት ገልጧል:: ደብረ ዘይት ጌታችን ዳግም ለፍርድ መምጣቱን እና ምሥጢረ ምጽአቱን ለደቀ መዛሙርቱ በሚገባ የገለጠበት ዕለት ነው:: ደብረ ዘይትን ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ለማደሪያነት ተጠቅሞበታል:: ቀን ቀን በምኲራብ ያስተምራል፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በደብረ ዘይት ያድራል:: ይህንም ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይመሰክራል “ዕለት ዕለት በመቅደስ ያስተምር ነበር:: ሌሊት ግን ደብረ ዘይት ወደምትባል ተራራ ወጥቶ ያድር ነበር:: ሕዝቡ ሁሉ ይሰሙት ዘንድ ማልደው በመቅደስ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር”:: በዚህ ለማደሪያነት ባገለገለው ተራራ ምሥጢረ ምጽአቱን ስለ ገለጠበት አምስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ደብረ ዘይት የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል::
ደብረ ዘይት ጾሙ እኩል የሚሆንበት፣ አምላካችን በግርማ መንግሥቱ ለፍርድ በመጣ ጊዜ መልካም ለሠሩ ክብርን፣ ክፉ ለሠሩ ቅጣቱን የሚያስተላልፍ መሆኑ የሚነገርበት፣ ስለ ዓለም መጨረሻ እና ስለሚመጣው ሕይወት የምንማርበት የክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ዕለት ነው::
ስድስተኛው ሳምንት “ገብር ኄር” የሚል ስያሜ አለው:: “ገብር ኄር” ማለት “በጎ እና ታማኝ አገልጋይ” ማለት ነው:: ስያሜው ከማቴዎስ ወንጌል የተወሰደ ሲሆን ታሪኩም እግዚአብሔር በሰጠው ጸጋ በታማኝነት ማገልገል የሚያስገኘውን ዋጋ ያስረዳል:: በተሰጠው መክሊት ያተረፈ ሰው ዋጋ አለው:: በፈጣሪው ዘንድ መልካም፣ በጎ እና ታማኝ ባሪያ ተብሎ ይሸለማል:: ባያተርፍ ደግሞ ሐኬተኛ ባሪያ (አገልጋይ) ይባላል፤ ቅጣቱንም ይቀበላል:: እንግዲህ እኛም ታማኝ አገልጋይ መሆን ይጠበቅብናል:: ሳምንቱ ይህ መልእክት የሚተላለፍበት ወቅት ነው:: በዚህ ዘመን በመክሊታቸው የሚያተርፉ እንዳሉ ሁሉ መክሊታቸውን (ጸጋቸውን) ዝገት እስከሚያጠፋው ድረስ የሚቀብሩ ብዙዎች ናቸው:: መክሊትን (ጸጋን) መቅበር ዋጋ የማያሰጥ መሆኑን ተገንዝበን በቻልነው መጠን ለማትረፍ መትጋት እና ታማኝ አገልጋይ መሆን እንደሚገባን ከገብር ኄር ታሪክ እንማራለን::
ሰባተኛው ሳምንት ‹ኒቆዲሞስ› የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን፣ የስያሜው መነሻም በዮሐንስ ወንጌል የተመዘገበው ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ አለቃ ታሪክ ነው:: ኒቆዲሞስ በሦስት መንገድ የአይሁድ አለቃ ነበር፤ በሥልጣን፣ በዕውቀት እና በሀብት:: ሰው ሥልጣን ቢኖረው ሀብት እና ዕውቀት ላይኖረው ይችላል:: ዕውቀት ቢኖረው ደግሞ ሀብት እና ሥልጣን ላይኖረው ይችላል:: ሀብት ቢኖረውም ዕውቀት እና ሥልጣን ላይኖረው ይችላል:: ኒቆዲሞስ ግን ሦስቱንም አንድ ላይ አስተባብሮ የያዘ የአይሁድ አለቃ ነበር:: ኒቆዲሞስ ወንጌልን ለመማር ከአይሁድ ሁሉ ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችን ይሔድ ነበር:: ኒቆዲሞስ ፈሪሳውያን ማመን ባልቻሉበት በዚያን ዘመን ጆሮውን ለቃለ እግዚአብሔር፣ ልቡን ለእምነት የከፈተ ሰው ነው:: ብዙ ሰዎችን እናውቃለን ማለት ከመልካም ነገር ሲከለክላቸው ኒቆዲሞስ ግን አዋቂ ሳለ ራሱን ዝቅ አድርጎ፣ እምነት በማጣት የነጠፈችውን የፈሪሳውያንን ኅብረት ጥሎ፣ ሐዋርያትን መስሎ ጌታውን አግኝቶታል:: ጌታችን ዓለምን ለማዳን ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በለየባት በዚያች አስጨናቂ ሰዓት፣ ሐዋርያት በተበተኑባት አይሁድ በሠለጠኑባት በዕለተ ዓርብ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን በድርብ በፍታ (ገመድ) ገንዞ የቀበረ፣ እሱን ያገኘ ያገኘኛል ሳይል በድፍረት ከእግረ መስቀሉ የተገኘ ሰው ነው–ኒቆዲሞስ:: ስለ ምስጢረ ጥምቀት ኒቆዶሞስ የተማረበትም ነው:: ስለዚህም ሰባተኛው ሳምንት በእርሱ ስም ተሰይሟል::
“ሆሣዕና” ስምንተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ሲሆን የሰሙነ ሕማማት መጀመሪያ ነው:: ሆሣዕና ስያሜው በማቴዎስ ወንጌል ከሚገኘው ትምህርት የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም “መድኀኒት” ወይም “አሁን አድን” ማለት ነው:: ክብር ይግባው እና አምላካችን በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ “ሆሣዕና በአርያም” የሚሉ የአዕሩግ፣ የሕፃናት ምስጋና እየቀረበለት ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ጉዞ ያደረገበት፣ ትሕትናውን የገለጠበት፣ ይህን ዓለም ከማዕሠረ ኃጢአት መፍታቱን በምሳሌ ያስረዳበት ዕለት ነው:: “ተጽዕኖ” ተብሎ ከሚጠራው የዐቢይ ጾም መጨረሻ (ዕለተ ዓርብ) እና ከሰሙነ ሕማማት መግቢያ ጀምሮ ያለው ሳምንት ሆሣዕና ይባላል:: የክርስቶስን ነገረ ሕማሙን፣ ስቅለቱን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን ሆሣዕና ተብሎ ዓለምን ማዳኑን የሚናገሩ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚነበቡበት ነው:: አምላካችን ለሰው ልጅ መዳን መከራ መቀበሉ እና የማዳን ሥራው በሰፊው የሚታወጅት፣ በሰሙነ ሕማማት ለሚያርፉ ምእመናን ጸሎተ ፍትሐት የሚደረግበት፣ ወንጌል በአራቱ ማዕዘን የሚሰበክበት ሳምንት ነው–ሆሣዕና:: ከዚያው አያይዞም ሰሙነ ሕማማት ይቀጥላል፤ ወቅቱም የክርስቶስን ነገረ ሕማሙን እና ዓለምን ያዳነበት ጥበቡን የምንሰማበት ሳምንት ነው::
ምዕመኑ እንዴት መጾም አለባቸው?
ምዕመኑ ቅበላ በማለት በየስጋ ቤቱ በሚተራመስበት አባቶች ጾም ይጀምራሉ፤ ይህም ራሳቸውን ስጋቸውን ለማለማመድ ነው መዘጋጀት ያስፈልጋል፤ እነሱ የሚያሳዩን ይሄን ነው፤ ዐብይ ጾምን የሚቀበል ሰው ራሱን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፤ ዐብይ ጾም ሙሽራ ነው፤ ሰክሮ ከልክ በላይ በልቶ ጠጥቶ መጠበቅ ልክ አይደለም፤ አንዳንድ ሰዎች ባለመዘጋጀታቸው መሐል ላይ ጾም ያቋርጣሉ፤ ጾም ቢቋረጥ ሁለት ቀንም እንኳ ቢቀር ማቋረጥ አያስፈልግም፤ እጅህን እሳት ቢፈጀው ከእንግዲህ አይጠቅምም ብለህ ለእሳት ትሰጠዋለህን? ይላሉ፤ አባቶች፤ ባል እና ሚስት በምንጣፍ በአንድ አይሆኑም፤ ከሩካቤ ይቆጠቡ በጣም ከተቸገሩ ቢያንስ 40 ጾም እና ህማማቱን በግድ ይጹሙ፤ ቀስ በቀስ ሁሉንም ይጹሙ፤
ሌላው በቂም በበቀል በተንኮል ውስጥ ሆኖ መጾም ውጤት የለውም፤ አንድ ሰው በሁዳዴ ጾም ሰው ለመግደል ከቤቱ ሊወጣ ሲል “ሚስቱ ቁርስ በልተህ ሂድ” ትለዋለች፤ “እኔ እኮ አማኝ ነኝ” ሲል ይመልሳል:: “ይህ ግለሰብ ሰው ሊገል ተሰናድቶ የሚጾመው ጾም በመርዝ የተበከለ ምግብ ነው” ይለዋል:: ስንጾም መልካም ምግባር፣ ጸሎት እና ምጽዋት ማድረግ ያስፈልጋል፤ ጾመኞች የተቸገሩትን የሚረዱ መሆን አለባቸው:: መርፌ እየሰኩ ጠላቴን እንዲህ ውጋው የሚሉ የውርንጭላ ድካም ነው የሚሆንባቸው::
መድኅኒት የሚወስዱ ሰዎች እግዚአብሔር አስጨንቆ የሚገዛ አምላክ አይደለም እና ለጾም አይገደዱም:: መድሃኒት ያቋርጡ የሚል ትምህርት የለም፤ ወደ ጤንነታቸው እስኪመለሱ አይገደዱም::
የሀገርን ሰላም ከማስጠበቅ አንጻር ከአማኙ ምን ይጠበቃል?
እንቅልፍ “ታበዢ ከነብር ትፋዘዢ” ይባላል፤ ይህ ማለት ነብር ዜማ ይወዳል፤ እረኛው ዋሽንት ሲነፋ እየተሳበ ከእረኛው ይደርሳል፤ ቁጭ ብሎ ያደምጣል፤ ባለዋሽንቱ አቅቶት ትንፋሽ ሲያጥረው፣ ነብሩ በጥፍሩ ጫር ያደርገዋል፤ እንደገና ይነፋል፤ አቅቶት ሲያቆም አሁንም ነብሩ ይጭረዋል፤ ዋሽንት እንዳይነፋ ደክሞታል፤ እንዳይተወው የነብር ጥፍር አለ፤ ይቸገራል፤ ልክ እንደዚህ እኛም ሀገራዊ ችግርን መገንዘብ አለብን፤ ችግሩ ከመወሳሰቡ በፊት ወድመን መንቃት ያስፈልገናል፤ የማንወጣው ጣጣ ውስጥ ልንገባ እንችላለን፤
ሁሉም ቆም ብሎ ማሰብ አለበት፤ ራሱን መገምገም ይጠበቅበታል:: ለሰላም ሁሉም ድርሻ አለው፤ ይህም ልጆችን አንጾ ከማሳደግ ይጀምራል:: መንፈሳዊ የሆነ ዜጋ መፍጠር ይገባል፤ ይህ ከሆነ ሰው ለመግደል፣ ሌላውን ለመጉዳት እና ጥፋት ለማድረስ የሚሻ ሰው አይኖርም:: ክርስትና የሚያስተምረው የክርስቶስን ሥርዓት ነው፤ ይህን የማይከተል ሰው በዚህ ዓለምም ሆነ በዘላለማዊ ሕይወቱ ቅጣት ይጠብቀዋል:: በጎ ስነ ምግባር ያለው ትውልድ በመፍጠር ሀገርን ማጽናት ይቻላል::
እንግዳችን ስለነበሩ እናመሰግናለን!
እኔም አመሰግናለሁ!
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም