በአራቱም የዓለም ማዕዘን ያለ የእግር ኳስ አፍቃሪ እና ደጋፊ ለቅጽበት እንኳን የሦስቱን ፈረሶች ግልቢያ ትኩረት አይነፍገውም። ፉክክሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጓጊ ሆኗል። አርሰናል፣ ሊቨርፑል እና ማንቸሰተር ሲቲ ሻምፒዮን ለመሆን ትንቅንቅ ውስጥ ገብተዋል። የፕሪሚየር ሊጉ አስጨናቂው ምዕራፍም እየተገለጠ ይገኛል። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልኩ ከተደራጀበት እ.አ.አ 1992 የውድድር ዘመን ጀምሮ በፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ለመሆን ሦስት ክለቦች ሲፎካከሩ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል እና ሊቨርፑል እኩል 71 ነጥቦች አሏቸው። ወጣት መድፈኞቹ በግብ ልዩነት የመርሲሳይዱን ክለብ በልጠው ከሊጉ አናት ላይ ተቀምጠዋል። ሊቨርፑል ሁለተኛ፣ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ በ70 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አርሰናል የፕሪሚርሊጉን ዋንጫ ካሳካ 20 ዓመታትን ደፍኗል። ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ለወራት ሊጉን ሲመራ ከርሞ በመጨረሻ በሠራው ስህተት ዋንጫውን በማንቸስተር ሲቲ መነጠቁ የሚታወስ ነው። የሚኬኤል አርቴታው ቡድን የአምናውን ስህተቱን ላለመድገም በጥንቃቄ እየተጓዘ ነው። በእርግጥም ዘንድሮ ከአምናው በእጅጉ መሻሻሉን ሜዳ ላይ አሳይቷል።
ክለቡ ከወትሮው በተለየ ለተጋጣሚው በቀላሉ የማይረታ ጠንካራ ቡድን ሆኗል። በተለይ ደግሞ አዲሱ የፈረንጆች ዓመት 2024 ከገባ ጀምሮ በፕሪሚር ሊጉ አንድም ሽንፈተ አልገጠመውም። በተጋጣሚዎቹ ላይም በርካታ ግቦችን እያዘነበ ይገኛል። ባልተሸነፈባቸው ባለፉት 11 ጨዋታዎች በተጋጣሚ ቡድን ላይ 38 ግቦችን አዝንቧል። አራት ብቻ ግቦች ደግሞ ተቆጥረውበታል። በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን ባለማስደፈርም ከሜዳ መውጣት ችሏል። አርሰናል እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ 31 ውድድሮችን አድርጓል። ከእነዚህ መካከል 22ቱን በድል ተወጥቷል። በአምስቱ ነጥብ ሲጋራ በቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፏል። ዌስትሀም፣ ፉልሀም፣ ኒውስካስትል እና አስቶንቪላ አርሰናልን በዚህ ዓመት ያሸነፉ ክለቦች ናቸው። ከተፎካካሪዎቹ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲ የበለጠ 75 ግቦችን አስቆጥሯል። ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች አነስተኛ የሆኑ 24 ግቦች ደግሞ ተቆጥረውበታል። የ42 ዓመቱ ስፔናዊ አሰልጣኝ በክረምቱ የዝውውር ወቅት ቡድኑን ለማጠናከር ያደረጓቸው ዝውውሮች ስኬታማ መሆናቸውን እያስመሰከሩ ነው። ዴክላን ራይስ፣ ካይ ሀቫርትዝ እና ጁሪየን ቲምበር ባሳለፍነው ክረምት ኤምሬስት የደረሱ ተጫዋቾች ናቸው።
በሰሜን ለንደኑ ክለብ አስደናቂ ብቃታቸውን እያሳዩ የሚገኙት በተለይ ራይስ እና ሀቫርትዝ ለቡድኑ ትልቅ አቅም ፈጥረዋል። ይህ ደግሞ ክለቡን ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋግሮታል። በመጀሪያው የሜዳ ክፍል ኳስን መስርቶ እና ተቆጣጥሮ በመጫወት ተጋጣሚን ፋታ ማሳጣት አርሰናሎች ላለፉት 31 ሳምንታት እየተገበሩት ያለ ታክቲክ ነው። አሰልጣኙ እንደየ ተጋጣሚው ተለዋዋጭ የታክቲክ አቀራረብ እንደሚከተል በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ለዚህ ማሳያ ደግሞ በቅርቡ በኢትሀድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነበረው የ30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በጥልቀት ተከላክሎ ጨዋታው ያለምንም ግብ መጠናቀቁ አይዘነጋም።
ቡድኑ ከዚህ በፊት እንደ ድክመት ይነሳበት የነበረው የኋላ ክፍል ችግር ዘንድሮ ተወግዷል። የኋላ ክፍሉ ችግር መፈታት ክለቡን በቀላሉ ግብ የማይቆጠርበት በማድረግ ተፎካካሪ አድርጎታል። የሰሜን ለንደኑ ክለብ እንደ ቡድን አሁን ላይ በሁሉም ረገድ በዓለማችን ጥራት ካላቸው ታላላቆቹ ቡድኖች ተርታ መሰለፍ ችሏል። ቡድኑ በአንድ ተጫዋች ጥገኛ አለመሆኑ ይታወቃል። በሁሉም የሜዳ ክፍል የሚገኙ ተጫዋቾች ግቦችን በማስቆጠር እና ወሳኝ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር አስደናቂ ጊዜ እያሳለፉ ነው። የመልበሻ ቤት ክፍሉ በጥሩ መንፈስ መሞላቱም ለቡድኑ ውጤት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ለዚህ ደግሞ የካይ ሀቫርትዝ በኤምሬት ያሳያው አስደናቂ ለውጥ ምስክር እንደሚሆን መረጃዎች አመልክተዋል። የአርቴታ ሂደቱን እመኑ ( trust the process) ትንቢትም አሁን ላይ የሥራ ይመስላል። አሰልጣኙ በኤምሬትስ የፈጠረው አብዮትም ዘንድሮ በክብረ ወሰኖች የታጀበ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። አርሰናል በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊጉም ከ14 ዓመታት በኋላ ሩብ ፍጻሜ መቀላቀል ችሏል።
አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከሊቨርፑል ጋር ይለያያል። በ2015 እ.አ.አ ብሬንዳን ሮጀርስን ተክቶ አንፊልድ ሮድ የደረሰው ጀርመናዊ አሰልጣኝ በዘጠኝ ዓመታት ቆይታው የፕሪሜየር ሊጉን፣ የሻምፒዮንስ ሊጉን እና ሌሎችንም ዋንጫዎችን አንስቷል። በ2019/20 የውድድር ዘመን ቀዮቹ ከ30 ዓመታት በኋላ ከዋንጫ ጋር እንዲገናኙ አድርጓል። በ2018/19 ደግሞ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ክብርን ተጎናጽፏል። ሊቨርፑልን ከወደቀበት አፈሩን አራግፎ ወደ ቀድሞ ኃያልነቱ መመለስ ችሏል- አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ። ታዲያ ይህን አሰልጣኝ በክብር ለመሸኝት ቀዮቹ በፕሪሚየር ሊጉ እልህ አስጨራሽ ትግል ከአርሰናል እና ሊቨርፑል ጋር እያደረጉ ነው።
የመርሲሳይዱ ክለብ በዚህ ዓመት የተሳካ የውድድር ጊዜ እያሳለፈም ይገኛል። ቸልሲን በማሸነፍ የካራባኦ ዋንጫን በማንሳት ዓመቱን በዋንጫ የጀመረው ሊቨርፑል በኢሮፓ ሊግም የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብሩን ከአትላንታ ጋር እያደረገ ነው። ቡድኑ ምንም እንኳን በጉዳት እየታመሰ ቢሆንም በፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን ሁለት ጨዋታዎች ብቻ መሸነፉ ለዋንጫ በሚያደርገው ጉዞ በትክክለኛ መንገድ እየተጓዘ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው። ክለቡ ከሜዳው ውጪ በቶተንሀም ሆትስፐርስ እና በአርሰናል ከሜዳው ውጪ መሸነፉ አይዘነጋም።
ምናልባት ጉዳት ላይ የሚገኙት አሌክሳንደር አርኖልድ፣ ዲያጎ ዦታ፣ ጆኤል ማቲፕ ፣ ቲያጎ አልካንትራ እና አሊሰን ቤከር ከጉዳታቸው አገግመው ቶሎ የሚመለሱ ከሆነ ዓመቱን በዋንጫ ለመደምደም ትልቅ አቅም እንደሚሆኑት የስካይ ስፖርት መረጃ ያመልክታል። ሊቨርፑል እስካሁን ካደረጋቸው 31 ጨዋታዎች በ21ዱ አሸንፏል፣ በስምንቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
በአውሮፓ አምስቱ ታላላቅ ሊጎች በሁሉም ውድድሮች ዘንድሮ በርካታ ግቦችን በተጋጣሚ መረብ ላይ ያሳረፈ ቀዳሚው ክለብም ነው- ሊቨርፑል። 125 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። በፕሪሚየር ሊጉ ብቻ ከአርሰናል በሦስት ግቦች ብቻ አንሶ 72 ግቦችን ከመረብ ጋር አገናኝቷል። 30 ግቦች ደግሞ ተቆጥረውበታል። የአሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ቡድን በዚህ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ክለቦች ጋር ባደረገው ጨዋታ አስቶንቪላን ብቻ መርታቱ ይታወሳል። በሌሎቹ ክለቦች ላይ ግን ጠንካራ ምቱን ማሳረፍ ተስኖት ነጥብ ጥሏል።
ማንቸስተር ሲቲ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ፉክክር ውስጥ የሚገኝ ሌላኛው ክለብ ነው። በፔፕ ጋርዲዮላ የሚመራው ክለብ ከአርሰናል እና ሊቨርፑል በአንድ ነጥብ አንሶ በ70 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኝው። የማንቸስተሩ ከተማ ክለብ ዘንድሮ በፕሪሜየር ሊጉ ትንሽ ተዳክሞ ቢስተዋልም እስካሁን ግን ከፉክክሩ አልወጣም። ዋንጫውን እንዴት ማሸነፍ እንዳለበት ሚስጥሩ የተገለጠለት ጋርዲዮላ በፕሪሜየር ሊጉ የአርቴታን እና የክሎፕን ጥላ እየተከተለ እያስደነገጣቸው ይገኛል።
ማንቸስተር ሲቲ ዘንድሮ እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ ነው የተሸነፈው። በሰባቱ አቻ ሲለያይ ልክ እንደ ሊቨርፑል 21ዱን ደግሞ ረቷል። 71 ግቦችን ከመረብ ሲያገናኝ 31 ግቦች ደግሞ ተቆጥረውበታል። ማንቸስተር ሲቲ ከአውሮፓ አምስቱ ታላላቅ ሊግ ክለቦች በርካታ ግቦችን ያስቆጠረ ክለብ ጭምር ነው። ከሊቨርፑል እና ባየርሊቨርኩሰን በመቀጠል 114 ግቦችን ከመረብ በማገናኝት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የዓለማችን ቁንጮ አሰልጣኝ በ2016 ኢትሀድ ከደረሰ በኋላ የፕሪሚየር ሊጉ የሃይል ሚዛን ወደ ኢትሀድ እንዲያጋድል አድርጎታል። የማንቸስተር ከተማ ክለብን ከቀይ ወደ ውሃ ሰማያዊ ቀለም እንዲቀየር አድርጓል። ዘንድሮም ይህን የአሸናፊነት መንገድ እንደማይስት በብዙዎቹ ዘንድ እየተነገረ ነው።
ማን ዋንጫውን ሊያነሳ ይችላል?
ወጣት መድፈኞቹ የአምናውን ስህተታቸውን እንደማይደግሙት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል። ምንም እንኳ ከሊቨርፑል እና ከማንቸስተር ሲቲም የበለጠ ከቋጥኝ የሚገዝፍ ፈተና ከፊታቸው ቢጋረጥም ዓመቱን በዋንጫ እንደሚደመድሙ እምነትን አሳድረዋል። አርሰናል በቀሪ መርሐ ግብሩ በሜዳው ቸልሲን ሲያስተናግድ ከሜዳው ውጪ ቶተንሀም ሆትስፐርስን እና ማንቸስተር ዩናይትድን ይገጥማል። ከወልቭስ፣ በርንማውዝ እና ኤቨርተን ጋርም የሚገናኝ ይሆናል።
ኦፕታ አናሊስትም እነዚህን ተጋጣሚዎቹን ከግምት በማስገባት፣ የተጫዋቾችን ወቅታዊ አቋም እና ጤንነት እንዲሁም የክለቡን ያለፈውን ታሪክ መነሻ በማድረግ የዘንድሮውን ዋንጫ ማን ሊያነሳ እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል። እንደ ኦፕታ መረጃ ከሆነ አርሰናል 29 በመቶ ብቻ ዋንጫውን የማንሳት ዕድል እንዳለው ግምቱን አስቀምጧል።
የሙሀመድ ሳላህ እና የዳሪዊን ኑኔዝ ጥምረት ሜዳ ላይ በተግባር ያልተገለጠለት ሊቨርፑል በቀጣይ መርሐ ግብሩ በአንፊልድ ሮድ ቶተንሀም ሆትስፐርስን እና በቪላ ፓርክ ከአስቶንቪላ ብርቱ ፈተና ይጠብቀዋል። ከፉልሀም፣ ኤቨርተን ፣ ዌስትሀም እና ወልቭስ ጋርም የሚጫወት ይሆናል። በአርጀንቲናዊው አማካኝ ማክ አሊስተር አስደናቂ ብቃት እየታገዘ ያለው ሊቨርፑል 31 ነጥብ 3 በመቶ ዋንጫውን ያነሳል የሚል ግምት ተሰጥቶታል።
ምንም እንኳ ጆስኮ ግቫርዲዮል፣ ናታን አኬ እና ኬይል ዎከር ጉዳት ላይ ቢሆኑም የዲብረይነ ፣ ሀላንድ እና ሮድሪ መልካም ጤንነት ላይ መሆን ማንቸስተር ሲቲን አስፈሪ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል። አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላም በቀሪ ጨዋታዎች ነጥብ እንደማይጥሉ አስረግጦ ተናግሯል። በኳታር ንጉሣውያን ቤተሰብ ረብጣ ቢሊዮን ዶላሮች የሚዘወረው ክለብ አድፍጦ ከኋላ እየተከተለ አርሰናልን እና ሊቨርፑልን እያስበረገጋቸው ይገኛል። በመጨረሻዎቹ ሳምንታት የሚጠበቀውን ያንን አስፈሪ ሞገሱንም እየገለጠ ነው። ኦፕታ አናሊስትም የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንቸስተር ሲቲ እንደሚያነሳው ግምቱን አስቀምጧል። 39 ነጥብ 7 በመቶም ግምት አግኝቷል- ማንቸስተር ሲቲ።
በዚህ ተወዳጁ እና አጓጊው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የክለቦቹ ወድቆ መነሳት ተመልካችን ያዝናናል እንጂ ለክለቦቹ እጅግ አስፈሪ ነው። በዚህ አስደናቂ ፉክክር መሳሳት የሚያስከፍለው ዋጋ አደገኛ ነው፣ አሁን የመጨረሻው ምዕራፍ እየተገለጠ በመሆኑ ከጀርባ ለዋንጫ ያደፈጠ ቡድን በጆሯቸው ላይ እየተነፈሰ ነው። እናም ፍርሀት እና ስጋቱ አይሏል። ከመጋረጃ ጀርባ በጥሩ መንገድ እንደተዘጋጀ ተውኔት የፕሪሚየርሊጉ አስደናቂው ትዕይንት አሁንም ቀጥሏል።
ስካይ ስፖርት ፣ ኦፕታ አናሊስትን እና ቢቢሲ ስፖርትን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም