የራስ ጤና  እንክብካቤ

0
62

ሰዎች የጤና ዕክል ሲያጋጥማቸው የጤና ተቋማት ከመሄዳቸው በፊት በራሳቸው በቤት ውስጥ ህመማቸውን ለማስታገስ የሚያከናውኑት ተግባር የራስ ጤና እንክብካቤ ይባላል::ተግባራቱ ታዲያ በአሁኑ ወቅት የጤና ሥርዓቱን በማገዝ ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ነው የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ ያደረገው::ድርጅቱ በዚሁ መነሻነት ለራስ ጤና እንክብካቤ ማድረግ የሚያስችል መመሪያን በማጽደቅ ወደ ሥራ ከገባ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

 

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደገለጸው ራስን የመንከባከብን ጣልቃ ገብነት (Self-care interventions) የግለሰቦችን፣ የቤተሰቦችን እና የማሕበረሰብን ጤናማነትን ያሳድጋል::በሽታን ለመከላከል ይረዳል::በሽታን መቆጣጠር፣ ራስን ማከም፣ ለሰዎች እንክብካቤ ማድረግ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተጨማሪ ሕክምና ማግኘትን ያጠቃልላል፡፡

 

ለራስ ጤና እንክብካቤ ማድረግ ለአብነት የስኳር በሽታ ሕሙማን መድኃኒታቸውን ራሳቸውን በራሳቸው መርፌ በመውጋት የሚወስዱበት፣ ሰዎች የራሳቸውን የደም ግፊት፣ በደም ውስጥ የሚገኘውን የስኳር እና የሰውነት የሙቀት መጠናቸውን ለክተው የሚያውቁበት ሂደት ነው::ከዚህ በተጨማሪም አንዲት ሴት ነፍሰ ጡር በምትሆንበት ጊዜ ጤነኛ  በጤና ባለሙያ የሚለግሳትን ምክር መተግበሯ በራስ ጤና እንክብካቤ ውስጥ ይካተታል:: የራስ ጤና እንክብካቤ ሰዎች በቀጣይ ጤናቸውን በተመለከተ ማድረግ ስላለባቸው ነገር ቆም ብለው እንዲያስቡም ይጠቁማል፡፡

 

ከተጀመረ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረው ዓለም አቀፉ ራስን የመንከባከብ ቀን በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በየዓመቱ ሐምሌ 24 የሚከበር ሲሆን በየቀኑ ሰዎች ስለራስ ጤና እንክብካቤ ማድረግ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በመረዳት እና በመገንዘብ ያሳልፋሉ፤ ራሳቸውንም ይመረምራሉ፡፡

ኢትዮጵያም ከጤና አጠባበቅ ጋር ተያይዞ  እውቀትንና ግንዛቤን የሚጨምር በሽታን በመከላከል እና በመቆጣጠር ላይ ያተኮረ ከዓለም የጤና ድርጅት መመሪያ የተቀዳ ብሔራዊ የራስ ጤና አጠባበቅ መመሪያ አላት።  መመሪያው የእናቶች ጤና፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ አፍላ ወጣትነት  እና የወጣቶች ጤና ላይ ያተኩራል:: የክትባት አገልግሎቶች ላይም  አጽንዖት ይሰጣል።

 

መመሪያው የራስ ጤና እንክብካቤ ተግባራትን በመደገፍ ቤተሰብ እና ማሕበረሰብ የሚኖራቸውን ሚና አጉልቶ ያሳያል። ሰዎች የራሳቸውን ጤና  ሲንከባከቡ የጤና ባለሙያውን ጊዜ ይቆጥባሉ::ባለሙያው ወሳኝ እና ግዴታ የጤና ባለሙያ እገዛ ከሚያስፈልጋቸው ሕሙማን ጋር እንዲቆይ፣ እንዲያግዝ ያስችለዋል::

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው የራስ ጤና እንክብካቤ ተግባራዊ እየሆነ ያለው በጤና ባለሙያ እና ያለ ጤና ባለሙያ እገዛ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለው በባለሙያ እገዛ ሲሆን ለአብነትም አንዲት ሴት በራሷ  የማሕጸን በር ካንሠር ምርመራ ማድረግ እንድትችል በባለሙያ ምክር እና እገዛ ይደረግላታል:: ከማሕጻኗም  የጤና ባለሙያው እንዴት ፈሳሽ  መውሰድ እንደምትችል ያሳያትና ራሷ ተግባራዊ ታደርገዋለች፡፡

 

ሰሞኑን በባሕር ዳር ከተማ የራስ ጤና እንክብካቤ ቀንን ምክንያት ያደረገ ምክክር ተካሂዷል፤ በምክክሩ በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ማክሰኚት ወረዳ ውስጥ በሚገኙ የጤና ተቋማት ላይ የተደረገ ጥናት ቀርቧል::በወረዳው በምንዝሮ ጤና ጣቢያ፣ በጤና ኬላዎች እንዲሁም በገጠር በሚኖሩ ሰዎች  መካከል የማሕጸን በር ጫፍ ካንሠር ቅድመ ምርመራን በራሳቸው እንዲመረምሩ  ከተለዩ ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ባሉ 399 ሴቶች ውስጥ 14 ነጥብ ሰባቱ ምልክቱ እንደታየባቸው ነው የተመላከተው፡፡

ታዲያ ይህ ውጤት ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይ  ክልሉ የማሕጸን በር ካንሠር ምርመራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳያ ሆኗል ነው የተባለው፡፡

 

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ  ምክትል ኃላፊ አበበ ተምትም በምክክሩ ላይ እንዳሉት ግጭት ባለባቸው  አካባቢዎች በክልሉ ተግባራዊ የሆነው የራስ ጤና  እንክብካቤ መርሐ ግብር ማኅበረሰቡ የራሱን ጤና እንዲጠብቅ አቅም እየሆነ ነው። በተለይም ደግሞ የእናቶችን፣ የወጣቶችን እና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ  ያግዛል።  በቀጣይም  ለጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት በትኩረት ይሠራበታል።

 

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት  የድንገተኛ፣ ሥነ ምግብ እና ሥነ ተዋልዶ ጤና እንክብካቤ ባለሙያ ፍሬወይኒ ገብረ ሕይወት እንደተናገሩት የራስ ጤና እንክብካቤ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የራሱን ጤና በራሱ እንዲጠብቅ የሚያስችል ነው። ራስን የመንከባከብ መርሐ ግብርም በአማራ ክልል በሚገኙ 16 ወረዳዎች በሙከራ (ፓይለት) ደረጃ  ተግባራዊ ተደርጓል። ይህም ማኅበረሰቡ  ራሱን በመጠበቅ ሊከሰት የሚችለውን በሽታ ቀድሞ እንዲከላከል፣ ችግር ከተከሰተ ደግሞ ቀድሞ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ሕክምና እንዲያገኝ  የሚያስችል ነው።

 

በተያያዘም ራስን መንከባከብ በተጨናነቁ የጤና ሥርዓቶች ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ፣ አስፈላጊ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ እና የጤና ውጤቶችን ለማሻሻል ሚናው ላቅ ያለ ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2030 እ.አ.አ 18 ሚሊዮን የሚገመቱ የጤና ባለሙያዎች እጥረት ያጋጥማል ተብሎ ይጠበቃል::ይህም ድንገተኛ አደጋዎች ሲከሰቱ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል እንዳለ ሆኖ ማለት ነው::በአሁኑ ወቅት ደግሞ 130 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የጠቆመ ሲሆን በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ወደ 400 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች አስፈላጊ የጤና አገልግሎት እያገኙ እንዳልሆነ ነው ድርጅቱ የገለጸው።

 

ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከተለመደው የጤና ተቋም ምላሽ የተሻገረ አዳዲስ ስልቶችን መፈለግ ያሻል። የራስ ጤና እንክብካቤ ደግሞ የተሻለ እና አማራጭ ያልተገኘለት መፍትሔ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡

በተጨማሪም አንድ ግለሰብ፣ ቤተሰብ እና ማሕበረሰብ የራሱን ጤና እና ደኅንነት ለመጠበቅ ትርጉም ባለው መልኩ መሳተፍ በሚኖርበት ጊዜ የራስ እንክብካቤ ያግዙታል።

 

በኢትዮጵያ የጤና ሥርዓቱ በሰው ኃይል፣ በመሠረተ  ልማት ዝርጋታ ጉድለት፣  አስፈላጊ ግብአቶች  ባለመሟላት፣ በአቅርቦት እጥረት እንዲሁም በገንዘብ እጥረት ይፈተናል::በተለይም  የተሟላ የጤና አገልግሎት ክፍተቶች  በእናቶች፣ በአራስ (ጨቅላ) ሕጻናት፣ በልጆች፣ በታዳጊ ወጣቶች ጤና እና የስነ ምግብ አገልግሎቶች ላይ ተባብሶ ታይቷል። በመሆኑም የራስ እንክብካቤ ተደራሽ ሲሆን ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች የመቅረፍ አቅም ይኖረዋል።

 

በኢትዮጵያ የራስ ጤና ክብካቤ የጀመረው በ2023 እ.አ.አ በሙከራ ደረጃ ሲሆን የተሞከረው በአዲስ አበባ በስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ነው::ውጤቱም ጥሩ እንደሆነ ነው በምክክሩ የተገለጸው::

የጤና መሠረተ ልማት እጥረት ወይም ውስንነት ባለባቸው በችግር በተጎዱ አካባቢዎች ራስን መንከባከብ ከጤና ጋር የተያያዙ ውጤቶችን ለማሻሻል ትልቅ ሚና ይጫወታል። በራስ የሚመራ ወይም በራስ የሚተዳደር የጤና መረጃን ማዘጋጀት ግላዊነትን (privacy) ያስጠብቃል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ለሥነ ተዋልዶ ጤና ራስን የመንከባከብ ጣልቃገብነት ለተጠቃሚው እና ለጤና ሥርዓቱ ወጪዎችን የመቀነስ አቅም አለው።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የራስ እንክብካቤ ጣልቃገብነት መደበኛውን ከጤና ተቋማት የሚያገኙትን አገልግሎት ሊያቋረጥ እንደማይገባ ነው በመመሪያው የተገለጸው።

ለራስ ጤና እንክብካቤ ማድረግ የስፖርት እንቅስቃሴንም የሚያካትት ሲሆን እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው::የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለልባችን፣ ለአዕምሯችን እና ለአካላችን ከፍተኛ የጤና ጠቀሜታ እንዳለው ልብ ይሏል፡፡

 

ጤየራስን ጤና ለመጠበቅ፡

*አካላዊ እንቅስቃሴ የመንፈስ ጭንቀትንና የጭንቀት ምልክቶችን ለመቀነስ ይረዳል፡፡

* ለነፍሰ ጡር እና ከወሊድ በኋላ ሴቶች በሳምንት 150 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቢያደርጉ ይመከራል፡፡

* ለአዋቂዎችና ዕድሜያቸው ከፍ ላሉ ሰዎች በሳምንት ከ150 እስከ 300 ደቂቃዎች፣ ለወጣቶች እና ለሕጻናት ደግሞ በቀን 60 ደቂቃ እንዲንቀሳቀሱ ይመከራል፡፡

* ዕድሜያቸው ለገፉ  ሰዎች በሳምንት ሦስት ቀን እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡

* ከእንቅስቃሴ በተጨማሪም ጤናማ አመጋገብን ማዳበር፣   ያልተፈተጉ የእህል ዘሮችን (ስንዴ፣ ገብስ፣ አጃ…) እና ለውዝ መመገብ ይገባል፡፡  በምግብ ገበታ ላይ ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች አይጥፉ፡፡

* ሌላው የአዕምሮ ጤንነታችንን መንከባከብ ሲሆን  ጥሩ የአዕምሮ ጤና ለአጠቃላይ ጤንነታችን እና ደኅንነታችን ወሳኝ ነው፡፡

ምንጭ፡- የዓለም ጤና ድርጅትና አዳም

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሐምሌ 28  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here