በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው እና ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው በትጥቅ የታገዘ ሁከት (ብጥብጥ) የአማራ ክልል በምጣኔ ሐብት ወደ ኋላ እንዲመለስ፣ የሕዝቡ ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲላላ እና ስነ ልቦናው እንዲጎዳ እያደረገ ነው:: ኗሪነታቸውን በምዕራብ ጎጃም ዞን ያደረጉ ግለሰብ ከአንድ ዓመት በላይ የተሻገረው ግጭት በዕለት ተዕለት ሥራቸው እና በአጠቃላይ የመኖር ህልውናቸው ላይ የከፋ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል:: በተለይ ችግሩ ሕጻናት ላይ እያሳደረ ያለው ጠባሳ ከፍተኛ መሆኑን በስድስት ዓመት ልጃቸው ላይ ያስተዋሉትን ስሜት ያስረዳሉ::
“ልጄ ክፉኛ ተጎድቷል:: አሁን እስካለበት ዕድሜ ሲደርስ መሳሪያን በቁመናው ካልሆነ እንዴት እንደሚተኮስ፣ ምን አይነት ድምጽ እንደሚያወጣ የሚያውቀው ነገር አልነበረም:: ካለፈው ዓመት ጀምሮ የምንኖርበት አካባቢ ሰላም የለም፤ በየጊዜው ጦርነት አለ፤ ሰዎች ከቤት ይወሰዳሉ፤ መንገድ ይዘጋል:: ይሄን ሁሉ ነገር የተመለከተው ታናሹ ልጄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንኳን እንግዳ ሰው ከዚህ በፊት የሚያውቀው ሰው እንኳ መሳሪያ ይዞ ወደ ቤት ከመጣ ለምን መጡ፣ መጣ ሊገድለን ወይስ ሊወስደን ብሎ ለመደበቅ ይሞክራል:: የጠብመንጃ ጩኸት ሲሰማ ይረበሻል” በማለት ጦርነቱ እየፈጠረባቸው ያለውን የከፋ ጉዳት አስታውሰዋል::
ለአብነት ጦርነቱ በልጃቸው ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ አነሱ እንጂ በሚኖሩበት የገጠር ቀበሌ ባለፈው ዓመት ሁሉም ሕጻናት ከትምህርት ውጪ ሆነው መክረማቸውን አንስተዋል:: ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱት አንጻራዊ ሰላም ወዳለባቸው አካባቢዎች ተሰደዋል። ቀሪዎችም በአሁኑ ወቅት ትምህርት ይጀመር ቢባል እንኳ ያሳለፉት ሕይወት ተረጋግተው ትምህርታቸውን በመከታተል የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ ተብሎ እንደማይታሰብ ተናግረዋል::
በአጠቃላይ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው ሁከት በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል:: ለግብርና ሥራቸው ምርታማነት የሚያስፈልጉ የግብርና ግብዓትን በሚፈለገው ጊዜ አቅርበው እንዳይጠቀሙ፣ ያመረቱትን ወደ ገበያ እንዳያቀርቡ፣ ለዕለት የሚያስፈልጋቸውን ፍጆታ እንዳያሟሉ አድርጓቸው መቆየቱን አስታውሰዋል::
ከአንድ ዓመት በላይ የተሻገረው ግጭት አርሶ አደሩ ተረጋግቶ ወደ ሥራው እንዳይገባ፣ ተማሪው ትምህርቱን እንዳይማር፣ ሠራተኛው በነጻነት ተንቀሳቅሶ በመሥራት ኑሮውን እንዳያሻሽል፣ የታመመው ወደ ጤና ተቋም ሂዶ እንዳይታከም ከማድረግ ውጪ ለውጥ ባለማምጣቱ አሁን ላይ ችግሩን ተነጋግሮ መፍታት እንደሚገባ ጠይቀዋል:: በዚህም ታጣቂ ኃይሎች ሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በመገንዘብ ቀዳሚ አላማቸውን ንግግር እንዲያደርጉ፣ መንግሥትም ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የጀመረውን ጥረት ዕውን ለማድረግ እንዲተጋ ጠይቀዋል::
በእርግጥም በአማራ ክልል ያጋጠመው የሰላም እጦት ያስከተለው ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሐብታዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ከፍተኛ ነው:: ችግሩ አሁንም መልስ አጥቶ ቀጥሏል፡- ለዚህ አብነቶችን እንመልከት:: ባለፈው ዓመት ከሦስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እንደከረሙበት እና ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸው ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ጠቁሟል::
ክልሉ በ2017 ዓ.ም ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን በመመዝገብ ለማስተማር ማቀዱ ይታወሳል:: ይሁን እንጅ እስከ መስከረም ስምንት ቀን 2017 ዓ.ም በክልሉ መመዝገብ የተቻለው 2 ሚሊዮን 295 ሺህ 150 ተማሪዎች ብቻ መሆኑን ቢሮ ኃላፊዋ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ገልጸዋል። በዚህም አገላለጽ መሠረት ከ4 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች አሁንም ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም:: ከፍተኛ የተማሪ ቁጥር ይኖርባቸዋል ከሚባሉት የክልሉ አካባቢዎች መካከል ሦስቱ የጎጃም ዞኖች ሲሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች የተመዘገበው የተማሪ ቁጥር ከ10 በመቶ ያልበለጠ መሆኑን ኃላፊዋ ጠቁመዋል:: ይህም ችግሩ አሁንም የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ማሳያ ነው::
የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በጤናው ዘርፍ ያሳደረው ተጽእኖም ከፍተኛ ሆኖ ይነሳል:: የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ጥቅምት 09 ቀን 2017 ዓ.ም ገምግሟል:: የቢሮ ኃላፊዉ አብዱልከሪም መንግሥቱ በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ክልሉ በውስብስብ የጤና ችግር ውስጥ እንዲያልፍ እያደረገው መሆኑን አንስተዋል:: ለአብነት የወባ ወረርሽኝ ካለፉት ጊዜያት በተለየ መልኩ መጨመሩን አስታውቀዋል። ከክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በ2016 ዓ.ም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ወገኖች በወባ በሽታ ተይዘዋል፤ በ2017 ዓ.ም ሦስት ወራት ብቻ በወባ የተያዙት ከ600 ሺህ በላይ ወገኖች ናቸው::
የሰላም መደፍረሱ በጤና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ችግር መፍጠሩ ተነግሯል:: በክልሉ የእናቶች የወሊድ የጤና አገልግሎት 55 በመቶ መሆኑን ሲገልጹ፣ ቀሪዎቹ እናቶች በቤታቸው እንዲወልዱ ተገደዋል። ችግሩ በግብዓት አቅርቦት፣ ስርጭት እና አጠቃቀም ላይ ጉድለት እንዲፈጠር ማድረጉም ተመላክቷል::
የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር እና የደብረታቦር ከተማ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ውይይት ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም አካሂደዋል:: የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ ባጋጠመው የሰላም መታጣት ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው፣ ወላዶች እና ሌሎችም በመንገድ መዘጋጋት ምክንያት ለከፋ እንግልት እና ጉስቁልና እንዲዳረጉ አድርጓል:: ይህ ችግር አሁንም ቀጥሎ የሕዝቡ እንግልት እንዳይቀጥል የሕዝቡን ሁለንተናዊ ችግር በሚፈቱ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል:: የዞኑ ሕዝብ ለሰላም ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው ያሉት አስተዳዳሪዉ አሁንም ለሰላም ባለቤት በመሆን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ክልሉን ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን አስታውቀዋል:: ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ሥራዎች መሠራታቸውን እና ይህም ክልሉን ወደ አንጻራዊ ሰላም ማሸጋገሩን ጠቁመዋል:: አሁንም የክልሉን ሰላም ወደነበረበት አስተማማኝ የሰላም ሁኔታ ለመመለስ የሰላም እና የውይይት መንገዶች ክፍት መሆናቸውን አስታውቀዋል:: ይሁን እንጂ አሁንም ከሰላም በተቃራኒ ጎን ቆመው ሕዝብን እረፍት ለመንሳት በሚጥሩ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ከመምህራን እና የትምህርት ዘርፍ ኀላፊዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተወያዩበት ወቅት ማንኛውም ዘርን መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ ለሀገር የማይጠቅም በመሆኑ ማኅበረሰቡ ከዚህ የተሳሳተ አዙሪት ራሱን በማላቀቅ ለሀገር ክብር እና ሉዓላዊነት ዘብ እንዲቆም ጠይቀዋል::
የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በጋራ የሚፈቱ እንጅ በተናጠል የሚፈቱ እንዳልሆኑ ሁሉም በአጽንኦት ሊረዳው እንደሚገባ ጠቁመዋል::
የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊው እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አደም ፋራህ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ጊዜያት በነበሩ የመንግሥት ሥርዓቶች የሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ያልተረጋገጠበት፣ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎች ምላሽ ያላገኙበት፣ ቁልፍ ፖለቲካዊ ተቃርኖዎች እና ችግሮች ያልተፈቱበት እንደነበር አስታውሰዋል:: እያጋጠሙ ላሉ ተቃርኖዎች እና ችግሮች መፍትሄው የፖለቲካ ለውጥ ማካሄድ መሆኑን መጠቆማቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል:: የፖለቲካ ሪፎርሙ ተቃርኖዎችን ሊያስታርቅ የሚችል የመሐል ፖለቲካን የሚከተል፣ የሕዝብን ሁለንተናዊ ጥያቄ የሚመልስ፣ የሀገሪቱን ሰላም እና ደኅንነት ሊያረጋግጥ የሚችል ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል:: ለዚህም እውን መሆን ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓትን እና ተቋማትን መገንባት እንዲሁም መምራት የሚችል አመራር ያስፈልጋል::
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ከአሚኮ ጋር በስልክ በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ የዘመናት የአብሮነት ሂደት ውስጥ የሃሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች ነበሩ:: ልዩነቶች ሲሰፉ ሀገራዊ መልክ መያዛቸው ደግሞ የአብሮነት ፈተና እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል:: ባለፉት ዘመናት የሃሳብ ልዩነቶችን ለመቋጨት ግጭትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ መኖሩን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ ይህ ግን ያልተገባ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለ አስታውሰዋል፤ አሁንም የዓለም ሥነ መንግሥት የጸናው በደም መስመር ነው ብለው የሚያምኑ የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚዎች በኢትዮጵያ ምድር መኖራቸውን ጠቁመዋል::
በሀገር እና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ ሳንካዎችን ለማምከን ግን ዋና መውጫ መንገዱ ሀገራዊ ምክክር ማድረግ ነው:: ቃል አቀባዩ በሃሳብ የፀናች እና በምክክር የቀናች ሀገር መገንባት ምክክር ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ አስፈላጊ እና ጊዜውም አሁን መሆኑን ጠቁመዋል:: በመሆኑም ምክክሩ ግቡን መትቶ ሀገር ወደ አንድነት እንድትመጣ ከተፈለገ “በሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል” የሚሉ ሁሉም በቅንነት፣ በትጋት እና በትብብር ሊደግፍ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም