በ2016 ዓ.ም ጥቅምት ወር መጀመሪያ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ መደረጉ ይታወሳል:: ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አለመግባባቶች እና ጥያቄዎች ሁሉ በንግግር ሲፈቱ ድሉ የሁሉም መሆኑን ተናግረዋል:: ፕሬዝዳንቷ በየትኛውም አካባቢ የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን እና ግጭቶችን በማቆም የሠላም አማራጮችን ከመጠቀም ውጪ የተሻለ አማራጭ የለም ነበር ያሉት።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ እንዳሉት አደጉ የምንላቸው ሀገራት ዛሬ ላይ የደረሱት ልዩነቶች ስለሌሏቸው አይደለም፤ ልዩነቶቻቸውን በማቻቻል ከግጭት በመለስ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ስለቻሉ ነው ብለዋል። ልዩነትም አንድነትም ተፈጥሯዊ ነው። የሰው ልጅ የመልክ፣ የእምነት፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የመኖሪያ አካባቢ፣ የአስተሳሰብ ልዩነት አለው፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የሚያደርጉት የሰውነት ጉዳዮችም አሉ።
“ወሳኙ ነገር ልዩነትን እንደ ጌጥ አንድነትን እንደ ማስተሳሰሪያ ኃይል እና አቅም መጠቀሙ ነው። ትናንት ለነገ ዕንቅፋት መሆን የለበትም፤ ትምህርት እንጂ። የትናንት ታሪክ የአብሮነት መገንቢያ ነው። የልዩነት መነሻ እንዳይሆን መሥራት ይገባል። እየተደማመጥን እየተመካከርን፣ ለሃሳብ እና ለውይይት በራችንን ክፍት እያደረግን እንጓዝ። ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እናጠንከር፤ ለሀገራችን መፃኢ ዘመን በጋራ እንትጋ። ከትናንት ይልቅ ጉልበታችንን እና ጊዜያችንን በነገ ላይ እናውል። ይህ ነው የዚህ ትውልድ ትልቁ ኃላፊነት” ሲሉ ነበር የገለፁት።
ኢዜአ የፍትሕ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ደግሞ አለመግባባታቸውን ቁጭ ብለው ነገሮችን በታሪክ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ዙሪያ ተነጋግረው በመፍታት የቻሉ ሀገራት ዛሬ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በመነጋገር ችግሮቻቸውን የፈቱ በርካታ ሀገራት በአሁኑ ወቅት ሰላም ሰፍኖባቸው የተሻለ እድገት ላይ የደረሱ ናቸው። ከዚህ በተቃራኒው በጦርነት ችግርን ወይም ግጭትን ለመፍታት ማሰብ እርስ በእርስ ከመጠፋፋት የሚያንስ አይደለም። በጦርነት ውስጥ የትኛውም አካል አሸናፊ አይሆንም፤ አሸናፊነት የሚመጣው በንግግር ችግርን መፍታት ሲቻል እንደሆነ ዘገባው ያመለክታል።
በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የፀደቀው የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ፣ የሽግግር ፍትሕ ሀገራት የተለያዩ መደበኛ እና ባህላዊ ወይም መደበኛ ያልሆኑ የፖሊሲ እርምጃዎችን እና ተቋማዊ አሠራሮችን በመጠቀም የተፈጸሙ ጥሰቶችን፣ ክፍፍሎችን እና አለመመጣጠኖችን ለማስወገድ እንዲሁም ለደኅንነትም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ፣ ለማህበራዊ እና ለኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚደረግ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ሂደት እንደሆነ ይገልጻል። የሽግግር ፍትሕ በግጭት፣ በጦርነት ወይም ጨቋኝ ሥርዓት በነበረበት ወቅት ለተፈፀመ ጥቃት መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እና በደል የተሟላ መፍትሔ መስጠት መቻል ነው።
በማህበረሰቡ ውስጥ በስፋት ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምላሽ የሚሰጥበት አካሄድን ደግሞ በሽግግር ፍትሕ ማምጣት ይቻላል በሚል ተቋቁሟል:: በኢትዮጵያ ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበው እና በፖሊሲ አማራጭ ዝግጅት ሂደት ላይ የሚገኘው የሽግግር ፍትሕ በአራት ዋና ዋና ምክንያቶች አስፈላጊ መሆኑን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል። አንደኛው ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሀገራዊ አውድ ሲሆን በዚህም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ አለመረጋጋት፣ ግጭት እና የእርስ በርስ ጦርነት ተከስቷል። ይህም ዜጎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀል ያጋለጠ መሆኑ በገፊ ምክንያትነት ይጠቀሳል። ለነዚህ ችግሮች ከዚህ በፊት የተሰጡ ምላሾች ሙሉ አለመሆናቸው የአጥፊዎችን እና የተጎጂዎችን ቁጥር ማብዛቱ፣ የበደሎች መደራረብ እና የጥፋቶች ማህበረሰባዊ ቅርጽ መያዝ በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት እና አካሄድ ፍትሕ መስጠትንም ሆነ ይቅርታ እና እርቅን ማከናወን አላስችል ማለቱ የሽግግር ፍትሕ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል።
የሽግግር ፍትሕ በአንድ ጊዜ የሚያልቅ ሳይሆን ጊዜ የሚጠይቅ እና ዓመታትን ሊወስድ የሚችል ነው። ይህም ለተበዳዮች ፍትሕ በመስጠት፣ ካሳ በመክፈል፣ የወደሙ ንብረቶችን መልሶ በመገንባት እና በመሰል ሂደቶች ሊፈጸም ይችላል።
የሽግግር ፍትሕ ሀገራት ከብጥብጥ፣ ከፀብ እና ከጥላቻ አዙሪት እንዲወጡ በማድረግ በኩል የማይተካ ሚና እንዳለው የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች ያሳዩናል። ይህም በዋናነት ሙሉ ፍትሕ የሚሰጥበትን መንገድ በመዘርጋት ዘላቂ ሰላም፣ እርቅ፣ መረጋጋት እና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓትን መገንባት የሚቻልበትን ሁኔታ የሚመለከት ነው።
ሁለተኛው የተሳካ የሽግግር ፍትሕ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ማለትም ባለፉ በደሎች ይቅር ለመባባል፣ እርቅ ለማውረድ፣ ሕዝብን ለማቀራረብ፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ለተፈጸመ በደል ዕውቅና ለመስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ነው።
ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ የተሳካ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ሳይተገበር የዴሞክራሲ ሽግግርም ሆነ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን አይቻልም የሚል ነው።
የመጨረሻው በገፊ ምክንያትነት የሚጠቀሰው ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሽግግር ፍትሕ ወሳኝ በመሆኑ ነው።
ኢትዮጵያ በነዚህ ምክንያቶች የሽግግር ፍትሕን ለማስፈን እየሠራች መሆኑ በበርካቶች ዘንድ በአዎንታዊነት ይነሳል። በተለይ የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ካደረጉ ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ ለውጤታማነቱ ከተሠራ በእርግጥም አይነተኛ መፍትሔ ነው። ደቡብ አፍሪካ፣ ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በቅርቡ ደግሞ ጋምቢያ የሽግግር ፍትሕን ለችግሮቻቸው መፍቻነት ከተጠቀሙ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም