በዕለት ውሏችን እና አዳራችን “ሰላም አደራችሁ! ጤና ይስጥልን!” የሚሉ የአንደበት ማፍታቻ ቃላት የቱን ያህል ዋጋ እንዳላቸው የምንረዳው ሁለቱም ሲርቁን ነው። ሰላም ከነጠፈ ሁሉ ነገር ይደርቃል። ሰላም ከሌለ ጤና ይታወካል፣ ዕድገት አይታሰብም፣ መኖርም በራሱ ከባድ ይሆናል።
እንደ አማራ ክልል ሰላም ከታጣ 360 ቀናት አልፈዋል። ሰላም በሌለበት ሁኔታ አንዷ ቀን እንደ ዓመት ትረዝማለች። በዚህ ሁኔታ በሰቆቃ፣ በስጋት እና በድንጋጤ ዓመት ታለፈ። ያም ሆኖ ግን አሁንም ሰላምን ለማምጣት መሠረታዊ የሚባል ሥራ እየተከናወነ አይደለም። ድርድርም፣ ንግግርም፣ ውይይትም ከተፋላሚ ኃይላት ጋር ገና አልተጀመረም።
ፍረጃው፣ መገፋፋቱ፣ መከፋፈሉ እና ተኩሱ ቀጥሏል። የጤናም ሆነ የትምህርት ተቋማት አሁንም አደጋ ላይ ናቸው። ግጭቱ ወደ ቀጣዩ ዓመት ከተሻገረ ደግሞ ቁስሉ እየበዛ፣ ቀውሱ እየተውሰባሰበ፣ ቂም እና በቀሉ እየከረረ ሂዶ የበለጠ ደም መፋሰስ እና ውድመት ሊመጣ ይችላል። በለው! ፍለጠው! ቁረጠው! ደምስው! … የሚሉ ጦርነት አፋፋሚ ቃላት አሁንም ኃላፊነት የጎደላቸው አንዳንድ የመገናኛ ብዙኀን አየሩን ይዘውታል። በአንጃ መፈራረጅ እና መቧደን በዝቷል፡፡
እየተካሄደ ባለው የዕርስ በርስ ግጭት ወንድም ከወንድሙ በተለያየ ጎራ ተሰልፎ ተጋድሎ በጋራ የሀዘን ድንኳን ላይ የሚገናኝበት አውድ ተፈጥሯል። ገዳይ እና ተገዳይ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው። ለዚህ ሁሉ ቀውስ ምንጩ ፖለቲካዊ ስብራት መሆኑ ግልፅ ነው።
ፖለቲካዊ ስብራቱ ቢጠገን ኑሮ ከግጭት በፊት መወያየት፣ መነጋገር እና መደራደር ይቻል ነበር። ተቋማት ነፃ እና ገለልተኛ፣ አካታች፣ ሁሉን አገልጋይ እና ፍትሐዊ ቢሆኑ ለሕዝብ ስለሚታመኑ ግጭቱን መቀነስ ይቻላቸው ነበር።
የፖለቲካ ስብራትን ፈጽሞ በውጊያ መጠገን ስለማይቻል አሁንም ሀቀኛ ውይይት፣ ድርድር እና ንግግር ማድረግ የግድ ይላል። ችግሩ ውስብስብ በመሆኑ ሁሉን አቃፊ ንግግር እና ውይይት አስፈላጊ ነው። ሰላም ሊመጣ የሚችለው በተወሰነ ቡድን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በሁሉም አካላት ትብብር እና ተሳትፎ በመሆኑ ለሰላም ሁሉም አካላት አዎንታዊ ሚና ሊጫወቱ ግድ ይላል።
በአማራ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ እልባት ለመስጠት ጦርነት አባባሽ እንጂ ችግር ፈቺ አይሆንም፡፡ ችግሩ ሊፈታ የሚችለው በፖለቲካዊ ውይይት እና ድርድር በመሆኑ ከእነዚህ መርህ ማፈንገጥ ልክነት አይኖረውም፡፡
ሰላም የሰፈነባቸው ሀገራት ከዕርስ በርስ ጦርነት የወጡት እና ወደ ዘላቂ ሰላም የተሻገሩት በንግግር እና እርቅ ነው፡፡ ንግግር ሲኖር የተበደለው ተክሶ፣ አጥፊውም ይታረማል፡፡ የጋራ ነገ በጋራ ውይይት ይዘጋጃል፡፡ የአንድ ሀገር ዜጎች የትናንት ትዝታ እንዳላቸው ሁሉ የጋራ ነገ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይሄ ሲሆን አብሮ መኖር፣ ለሕግ የበላይነት መቆም እና ሰላማዊ ማህበረ -ፖለቲካ ለመገንባት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ለዚህ ሁሉ ደግሞ ቁልፉ ጉዳይ በሀቅ ተነጋግሮ ለተፈጠረው ቀውስ እልባት መስጠት ነው፡፡
በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም