የሰላም ዋጋው ስንት ነው? የሰላምን ጣዕም እና የጦርነትን አስከፊነት ከሰላማዊ ሕዝብ ይልቅ በጦርነት ውስጥ ያለፈ እና የቀመሰው ሁሉ ይበልጥ ይገነዘበዋል::
ሰላም ጠፍቶ ጦርነት በሚነግስበት ዘመን ሀብትና ንብረት ቀርቶ ሕይወትም ዋስትና ያጣል::
ለዚህ እውነት ማሳያ ከህልውና ስጋት አንፃር የአማራ ክልል ሕዝብ፣ ከኢኮኖሚ ድቀት አኳያ ደግሞ የእኛን ሀገር ጨምሮ አፍሪካውያን ህያው ምስክር ናቸው::
በልማታዊ ምጣኔ ሀብት የትምህርት መስክ እስከ ኘሮፌሰርነት ያበቃ ዕውቀት የተካኑት ሰር ፖውል ኮሊር የሦስተኛው ዓለም ሀገራትን በድህነት እንዲኖሩ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል ጦርነት ዋነኛው መሆኑን ያሰምሩበታል:: “የእነዚህ ሀገራት የእርስ በርስ ግጭት በተራዘመ ቁጥር ከግጭቱ የሚያተርፉ አካላት እየበረከቱ ስለሚመጡ ሠላምን ከማስፈን ይልቅ ጦርነቱን በማባባስ የሀገራቱን ኢኮኖሚ እንዲወድም ያደርጉታል” ይላሉ::
ኘሮፌሰር ፖውል ለአፍሪካ ድህነትና ኋላቀርነት ዋነኛ መንስኤ ያደረጉት የእርስ በርስ ግጭት እና ጦርነት በሌሎች ሀገራት ተከስቶ የማያውቅ ሆኖ አይደለም፣ እንደ እኛ ያልደኸዩት:: በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች የሚከሰቱ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በኃይል ከመፍታት ይልቅ ለውይይትና ለድርድር ቅድሚያ በመስጠት ሠላማዊ መፍትሄን ስለሚያስቀድሙ እንጂ!
የሕንድ የነፃነት አባት የሚባሉትን ማህተመ ጋንዲን እንደ አብነት ብናነሳ የሕንድን ፀረ – ቅኝ ግዛት ትግል በድል የተወጡት ሰላማዊ መንገድን መርጠው ነው:: ሠላማዊ ትግል ዋጋ እንደሚያስከፍል ቢታወቅም በጦርነት ከሚደርሰው ኪሣራ ግን ሊበልጥ አይችልም:: ከዚህም በላይ ደግሞ በሰላማዊ ትግል የተገኘ ድል በጦርነት ከሚገኘው ይልቅ ዘላቂነት ያለው መሆኑ ችላ ሊባል አይገባውም ነው የሚሉት የግጭት አፈታት ሥነ ዘዴ ባለሙያዎች::
ክቡሩን የሰው ልጅ ህይወት የሚቀጥፍ፣ ሀብት እና ንብረት የሚያወድም ጦርነት ከሰላማዊ ትግል በላይ ሚዛን የሚደፋው የሰላማዊ ትግል አማራጭ በሮች ሁሉ ሲከረቸሙ ብቻ ነው::
የነፃነት ታጋዩ ማህተመ ጋንዲ “ጉልበት የእንስሳት እንደሆነ ሁሉ ሰላም የሰው ልጆች መንገድ ነው” ይላልና ከእንስሳት የምንለይበትን ባህርይ አሳልፈን ሳንሰጥ ፍቅር እና ሠላምን እናስቀድም፤ በጉልበት የተገኘ ድል ከሽንፈት እኩል መሆኑንም አንርሳ፤ ውጤቱ ጊዜያዊ ብቻ ነውና! ጋንዲ “ደካማ ይቅር ማለት አይችልም፤ ይቅርታ የትልቅነት እና የጥንካሬ ምልክት ነው” እያለ ለሰላም የተጋውን ያህል የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግም “ጨለማ ጨለማን አያስወግድም፤ ጨለማን የሚያስወግደው ብርሀን ብቻ ነው፤ ጥላቻ ጥላቻን አያጠፋም፤ ፍቅር ጥላቻን ያጠፋል” በማለት የሰላም እና ፍቅርን አስፈላጊነት ሲሰብክ ነው የኖረው::
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ኘሬዝዳንት የነበሩት ኔልሰን ማንዴል ደግሞ የፍቅር፣ የሰላም፣ የይቅር ባይነት፣ የአንድነት እና የመልካም አመራር ሰጭነት እና የለውጥ አመራር ምሳሌ ሆነው የሚጠቀሱት በተለየ ተአምር ሳይሆን በሰላም ወዳድነታቸው ነው። ለ27 ዓመት በእስር ከቆዩበት ሮቢን ደሴት ከእስር ሲለቀቁ ለመላው ዓለም ባሰሙት ንግግር ሳይቀር “ከሁለም በላይ ለሰላም እና ለእርቅ ሁሉም እኩል ሆኖ ለሚኖርበት ሀገር መፈጠር ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል” ሲሉ ነው ያሳሰቡት::
ማንዴላ የሰላምን እና የእርቅን ዋጋ አስቀድመው የተገነዘቡ ነበሩና ለ27 ዓመት በግዞት ያሰቃያቸውን አፓርታይዳዊ መንግሥት መበቀልም ሆነ መፋለምን ከቶውንም አላሰቡትም::
ወደ ሀገራችን ነበራዊ ሁኔታ ስንመለስ ግን ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ካለፉት ዘመናት የጦርነት ታሪካቸው እና ዳፋው አንጻር የጦርነትን አስከፊነት እና የሰላምን ጥቅም ከራሳቸው ተሞክሮ በውል የተገነዘቡ እና ነጋሪ የማያሻቸው ቢሆንም እንደ አለመታደል ሆኖ እነሆ ዛሬም ድረስ ከጦርነት አዙሪት መውጣት አልተቻላቸውም::
የወደቀው ሥርዓት ትሩፋት በሆነው ሀሰተኛ ትርክት ሳቢያ በሕዝብ መካከል የተፈጠረውን ቁርሾ እና የተሳሳተ ግንዛቤ እስካላጠሩ ድረስ አንድ አይነት (ተመሳሳይ) ሀገራዊ ራዕይ ያለው ትውልድ መፍጠር አዳጋች መሆኑም ስውር አልነበረም::
ይህንን መሠረታዊ ሀሳብ የተገነዘበው እና ስልጣኑን ከኢህአዴግ የተረከበው መንግሥት ታዲያ የሀይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሠላም እናቶች እና ሕዝባዊ ማህበራት የሚሳተፉባቸው የሰላም ኮንፈረንሶችን እያዘጋጀ ዴሞክራሲን በመገንባት፣ ፍትህን በማስፈን፣ ግጭትን በመከላከል እና ሰላምን በማስፋፋት ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ ሲያስጨብጥ ቆይቷል::
ለአብነት ያህል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለአንድ ቀን ከመዋጋት ለዘመናት መወያያት ሀገርን እንደሚያሻግር መግለጻቸውን ማስታወስ በቂ ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነት ምንም ትርፍ እንደሌለው በተለይ አምራች የሆነው ወጣት ኃይል እየረገፈና ሀገራችን ኢትዮጵያም ለጦርነት የምታወጣው ከፍተኛ ገንዘብ የኢኮኖሚ አቅሟን ክፉኛ እንደሚፈታተነው አፅንኦት ሰጥተው ነበር የተናገሩት::
ይኸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ እምነት እና ፍላጎት ከንግግር አልፎ በተግባር የሚከወን ለማድረግም በዐሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የሰላም ዘርፍ ልማት የሀገራችን እና የሕዝቧን ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ እንዲሁም አብሮነትን እና የሕግ የበላይነትን ማስፈን የሚሉት የዕቅዱ ዋና ዋና ዓላማዎች ሆነው ነው የተቀመጡት:: የዜጎችን የውስጥ ሠላም ዕድገት በ2022 ዓ.ም ወደ 88 በመቶ የማድረስ ግብም በልማት ዕቅዱ መቀመጡን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያመላክታል::
የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ በማህበረሰቡ፣ በፖሊስ እና በጸጥታ ተቋማት መካከል መተማመንን ደግሞ 95 በመቶ የማሳደግ ዕቅድ ተይዞ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሠራ መሆኑን ያተተው የኢዜአ ዘገባ በቀጣናው ባሉ ሀገራት መካከል ግንኙነት እና ትብብርን በማጠናከር ድንበር ዘለል የተደራጁ ወንጀለኞችን ሽብርተኝነተን ሳይቀር በ2022 ወደ ሁለት ነጥብ አምስት በመቶ የመቀነስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ተንትኗል:: ይህ ደግሞ ለሠላም መረጋገጥ የሚኖረውን ፋይዳ ከፍ ያደርገዋል:: በዚህ መልክ ታቅዶበት በትኩረት መሠራቱ ደግሞ በየአቅጣጫው ለሠላም የሚከፈለው መስዋዕትነት አስፈላጊ እና ከሁሉም በላይ መሆኑን ያመላክታል::
በተለይ አማራ ክልል ደግሞ አማራን በጠላትነት በፈረጀው ህወሀት ከተፈፀመበት ሰብአዊ እልቂት እና ኢኮኖሚያዊ ድቀት ገና ሳያገግም ለዳግም ጦርነት ተዳርጎ ዜጐች ለእልቂት ሲጋለጡ በዘለቀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ምጣኔ ሀብቱ ደቋል፤ ልማት ተቋርጧል፤ ወጣቶች ከትምህርት ተቋማት ተለያይተዋል፤ ኗሪዎችም መድረሻ አጥተዋል::
መንግሥት ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሠላም በሚል መሪ ሀሳብ በመላው አማራ ክልል ሕዝባዊ የሠላም ኮንፈረንስ እንዲካሄድ ማድረጉ በራሱ ትልቅ እርምጃ ነው:: ከከተማ አስተዳደር እስከ ቀበሌ በዘለቀው በዚሁ ኮንፈረንስ ላይ የተሳተፉት የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግልዎች፤ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች በሠላም እጦት ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድሙት መድረሱን በመጥቀስ ከዚህ በኋላ ተፋላሚ ሀይሎች እና መንግሥት ጦርነቱን አቁመው እንዲደራደሩ ነው የጠየቁት::
በምክክር ከቂም ይልቅ ይቅርታ፣ ከጠብ ይልቅ ፍቅር፣ ከጦርነት ይልቅ ሰላም እንደሚገኝ በየደረጃው ካሉ የብልፅግና አመራሮች ጋር የተወያዩት እነዚሁ የህብረተሰብ ክፍሎች የአማራን ህዝብ የህልውና እና የፍትህ ጥያቄዎች በጠመንጃ ሳይሆን በውይይት ለመፍታት መንግሥትም ሆነ የፋኖ ሃይሎች ፈቃደኛ እንዲሆኑ ጥሪአቸውን አቅርበዋል::
ታላቁ የነፃነት ተጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ፡-
“እንደ እህት እና ወንድም በጋራ መኖርን መለማመድ አለብን፤ ይህን ማድረግ ከተሳነን በጋራ እንጠፋለን” ማለቱን ልብ ብለን የጋራ አሽናፊነትን ለሚያጐናፅፈው ሰላማዊ ውይይት ልንዘጋጅ ይገባል::
በተለይ ደግሞ መግቢያችን ላይ ያነሳናቸው እንግሊዛዊው ኘሮፌሰር እንዳሉት ለሠላም መስፈን ከግጭት አትራፊ የሆኑ የጦርነት ደላሎች ከድርጊታችሁ ቢታቀቡ ሠላም ይነግሳል ይላሉ!!
(ጌታቸው ፈንቴ)
በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም