የሰላም ካውንስሉ ጥሪ

0
257

ክልሉ ውስጥ በተከሰተው ግጭት የምዕራብ እና የምስራቅ ጎጃም እንዲሁም የሰሜን ሸዋ ዞን  ነዋሪዎች እንደተናገሩት ለበርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት የዳረገው የአማራ ክልል ግጭት ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖው አሁንም ድረስ እንደቀጠለ መሆኑን  ገልጸዋል።

የክልሉ ምጣኔ ሀብት በእጅጉ  እየተዳከመም ይገኛል። ግጭቱ በግብርናው፣ በጤናው፣ በትምህርቱ፣ በቱሪዝሙ፣ በኢንዱስትሪው፣ በኢንቨስትመንቱ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራው፣ በንግዱ እና በትራንስፖርቱ … ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። ከዚህ በፊት ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት ክልሉን በእጅጉ ጎድቶታል። አሁን ላይ በክልሉ እየተካሄደ ያለዉ  ውጊያ በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ቀውስ ፈጥሯል። በፀጥታው ችግር ምክንያት በትምህርት ዘመኑ ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ የክልሉ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ማሳወቁ የሚዘነጋ አይደለም። ከሶስት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉም መረጃዉ አክሏል። ነገር ግን የአማራ ክልል የሰላም ካዉንስል (የሰላም ምክር ቤት) ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም እንዳስታወቀዉ ከሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነዋል::

ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መሠረት የሆነው የግብርናውን ዘርፍም በእጅጉ ፈትኖታል። አርሶ አደሮች ተረጋግተው እንዳያርሱ እና በቂ ምርት እንዳያመርቱ አድርጓቸዋል። አርሶ አደሮቹ በጦርነት ውስጥ ሆነው ያመረቱትን ምርት ገበያ ሄደው በሰላም እና በተሻለ ዋጋ እንዳይሸጡ ሆነዋል። ይህም እየናረ ለመጣው የኑሮ ውድነት ምክንያት ሆኗል። ሰዎች በልተው ለማደር ተቸግረዋል። በሰላም ወጥተው በሰላም እንዳይገቡ ሆነዋል።  በተራዘመ ግጭት ውስጥ መቆየታቸው ለከፋ ቀውስ እየዳረጋቸው መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለፁ ይገኛሉ። መጠፋፋቱ እና ደም መፋሰሱ በአጭር ጊዜ እንዲቆም በተደጋጋሚ እየጠየቁ ነው።  ለመደራደር ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠሩ፤ ሁሉም አካላት የሰላም ጥሪና የድርድር ሃሳቦቻቸውን በተግባር ያሳዩ ብለዋል። ህዝቡን ለስቃይ እና ለመከራ የዳረገው ግጭት በድርድር መቆም እንዳለበት አመላክተዋል። እንደልብ መውጣት እና መግባት አልተቻለም። ሰላም ናፍቆናልም ብለዋል። “በቀን ሥራ እንዳንሠራ፤ ማታም በሰላም  እንዳንተኛ ሁሌም በስጋት ውስጥ ነን” ብለዋል። ግጭቱ ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ነው የተናገሩት። ችግሩን በቅን ልቦና፣ በውይይት እና በድርድር እንዲፈታ እየጠየቁ ነው። ይህ ግጭት አስቸኳይ መፍትሔ ካልተሰጠው፣  ከዚህ የበለጠ ጉዳት ሊያስተናግድ ይችላል የሚል የብዙዎች ስጋት ሆኗል።  ታጥቀው ጫካ የገቡ የፋኖ ሀይሎች እና መንግስት ተኩስ አቁመው ችግሮችን በውይይት እና በእርቅ እንዲፈቱ እና  ሰላማዊ ኑሮ መኖር እንደሚሹም  ገልጸዋል።

ግጭቱ በስፋት ከተከሰተባቸው የአማራ ክልል ዞኖች መካከል የምዕራብ ጎጃም ዞን አንዱ ነው። ባለፉት አስር ወራት ብቻ በነበረው ግጭት ምክንያት ከደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት ባሻገር ከአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት መውደሙን ነው የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር ለአሚኮ ያስታወቀው። በተመሳሳይ የሰላም ካዉንስሉ እንደገለጸው በአሁኑ ወቅት በርካታ የክልሉ አካባቢዎች በመንግሥት እና የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ለማስመለስ ጫካ በገቡ ፋኖዎች መካከል በሚካሄደዉ በትጥቅ የታገዘ  ግጭት ሳቢያ የሕዝብ ሀብት፦ ከ12 እስከ 13 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት ወድሟል፤ ንጹኃን ተገድለዋል፤  የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ክፉኛ ተጎድቷል፤ የግልና የመንግስት ተቋማት ባለሙያዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ምክንያት የአገልግሎት አሰጣጥ ክፉኛ ተዛብቷል ብሏል።

በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት የመንገድ ኘሮጀክቶች በተሟላ አቅም እና በወቅቱ ወደ ሥራ እንዳይገቡ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) ናቸው። በመንገድ መሠረተ ልማቱ ዘርፍ መሥራት የሚገባውን ሥራ እንዳንሠራ ችግር ፈጥሯል ነው ያለዉ። ቀደም ባሉት ጊዚያት  በተሠሩ አምስት ድልድዮች ጉዳት እንደደረሰባቸው የገለፁት ቢሮ ኃላፊው በጀት በመመደብ ተጠግነው አገልግሎት እንዲሰጡ  ተደርጓል ብለዋል። ሌላው ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ጥናት መምህር እና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ገድፈው ሰውነት በክልሉ ያጋጠሙ ተከታታይ ግጭቶች ያስከተሉት ዘርፈ ብዙ ውድመት፤ የክልሉን ተወዳዳሪነት ወደ ኋላ የሚያስቀር፤ ለትውልድም ጫና የሚፈጥር ነው ብለዉታል። ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ እስካሁን እየወደመ ያለውን የክልሉን ሀብት እንደገና ለመጠገን ረጅም ዓመታትን እንደሚወስድ አመላክተዋል። ከችግሩ ለመውጣት እና የተረጋጋ ክልል እንዲሆን ሁሉም ሚናውን  መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያዊ እሴት የሆነውን የመደማመጥ እና የመነጋገር ባሕልን የተከተለ የመፍትሔ አማራጭ መተግበር እንደሚገባ ረዳት ፕሮፌሰር ገድፈው ሰውነት ገልፀዋል።

በግጭት ውስጥ ያሎ ነዋሪዎች ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት ከመዳረጋቸው በተጨማሪ፣ የሚቀምሱት አጥተው የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ፈላጊ ሆነዋል። አርሰው እንዳላበሉ፤ ጠምቀው እንዳላጠጡ የሰው እጅ ጠባቂ ሆነዋል። ብዙዎቹ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ:: ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው ካምፕ የሚገኙ ቁጥራቸው በርካቶች ናቸው።

በክልሉ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ላይ  የመከረው የሰላም  ኮንፈረንስ በክልሉ ነፍጥ አንስተው ለሚታገሉ ታጣቂዎች ባስተላለፈው መልዕክት   «ጥያቄያችሁን በሰላማዊ መንገድ ለውይይት እና ለድርድር በማቅረብ የወገናችሁን ስቃይ ለመቀነስ እንዲቻል መገዳደል ይብቃን ብላችሁ ወደ ወገናችሁ እንድትቀላቀሉ» ብሏል:: የአማራ ክልልን ከገባበት ቀውስ ለማውጣት ውይይት እና ድርድር የመፍትሔ መንገድ ነው ተብሏል።

በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በማለም በባሕር ዳር ከተማ በተካሔደው የሰላም ኮንፈረንስ ማጠቃለያ መድረክ ባለ ዓስር ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ነው የተጠናቀቀው። በአማራ ክልል ሰላም እንዲሰፍን የክልሉ ባለሥልጣናት በትጥቅ ከሚፋለሙት ጋር ለመደራደር ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግሥት በኩል ዝግጁነት አስታዉቋል።

“ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት በአማራ ክልል ለተፈጠረው ጦርነት የመፍትሔ ሃሳብ ያመጣሉ ተብለው ከተመረጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ከሰኔ 17/2016 ዓ.ም እስከ ሰኔ 18/2016 ዓ.ም በተደረገው የባሕር ዳር ኮንፈረንስ ከመከረ በኋላ ዘላቂ ተኩስ ለማቆም ንግግር እና ድርድር እንዲያደርጉ ኮንፈረንሱ መወሰኑ እና ለዚህ ሂደትም 15 አባላት ያሉት አመቻች የሰላም ካውንስል መርጧል። በመሆኑም የተመረጠው የሰላም ካውንስል ሲወያይ ከቆየ በኋላ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም መግለጫ አውጥቷል። በግጭቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል አጋጥሞት ይገኛል ብሏል። በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት አጠቃላይ ሀገራችንን ለጉዳት እና ወደ ባሰ ድህነት አረንቋ እየወሰዳት መሆኑን አብራርቷል።

በሰለጠነ ንግግር እና ድርድር አለመፈታታቸው ወይም የሚፈቱበት ሂደት ግልጽ ፍኖተ ካርታ አለመቀመጡ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ ይላል ካውንስሉ። በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ “የወንድማማቾች መገዳደል ይብቃ”ም  ብሏል። ለዚህ ቀውስ እና ምስቅልቅል ሁነኛ መፍትሔ ሀቀኛ ምክክር፣ ውይይት እና ድርድር ነው:: አሁንም እየተነሳ ያለው የውይይት እና የድርድር ሂደት ግብ እንዲመታ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል:: ለዘላቂ ሰላም ድርድር የማይተካ ሚና ይጫወታልና ድርድሩ ፈጥኖ ወደ ተግባር በመግባት እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት ማቆም አስፈላጊ ነው::

ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሶስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ሥብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ደ/ር) እንደተናገሩት መንግስት በሰለጠነ መንገድ ችግሮችን በውይይት እና በድርድር እንዲፈቱ ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስታውቋል::

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here