የሰሜን ምሥራቅ ግሪንላንድ ብሔራዊ ፓርክ በዴንማርክ ግዛት ስር ነው የሚገኘው:: ስፋቱም 972,000 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል:: ይህም በዓለም በስፋት ቀዳሚ አድርጐታል::
ከፓርኩ ክልል አብዛኛው በረዶ የተነጠፈበት ወይም በበረዶ የተሸፈነ ነው፡ በዴንማርክ ስረወ መንግሥት በግሪን ላንድ ቀጣና በ1925 እ.አ.አ የተመሰረተ ብቸኛው ፓርክ ሲሆን የባሕር ዳርቻዎች እና ከፊል ቀጣናዎቹ በረዶ የሌለባቸው መልከዓ ምድርንም ይዟል::
በቀጣናው 126 በሥም የተለዩ ከፍታ ቦታዎች ወይም ጫፎች (peaks) ይገኙበታል:: በከፍታው ቀዳሚው 2002 ሜትር የተለካው ዊንስትን ጆርግ ተጠቃሽ ነው::
በፓርኩ ክልል በበጋ ወቅት መደበኛ አገልግሎት የሚሰጡ 400 ጣቢያዎች አሉ:: ጣቢያዎቹ የአየር ሁኔታ መከታተያ፣ የምርምር፣ እና የወታደራዊ አገልግሎት ማስተናገጃ ወይም መኖሪያ ናቸው::
ፓርኩን ለመጐብኘት ከዴንማርክ ዋልታ ማእከል ፈቃድ መቀበል ግድ ነው:: ፓርኩን የመቆጣጠር እና ህግጋትን የማስከበር ኃላፊነት ለዴንማርክ ባህር ኃይል ነው የተሰጠው::
የዱር እንስሳት
በፓርኩ ከ500 እስከ 1500 የሚገመቱ “መስክ ኦክስን”፣ የዋልታ ድቦች “ዋልሩስ” ይገኛሉ:: ፀጉራሞቹ “መስክ ኦክስን” የተሰኙት በዓለማችን በብዛት የ40 በመቶዎች መጠለያ ቀጣና ነው:: ከተጠቀሱት በተጨማሪ የአርክቲክ ቀበሮ፣ የአርክቲክ ጥንቸል እና “ቤሉንጋዌል” እንደሚገኙ ድረ ገፆች አመላክተዋል::
በፓርኩ ከሚገኙ ዋና ዋና መስህቦች “ሰሚት ካምኘ” የተሰኘው ሰፈር አንዱ ነው:: ሰፈሩ ከባህር ወለል 3210 ሜትር ከፍታ ላይ የተቆረቆረ በአሜሪካን ኩባንያ የሚተዳደር ተቋም መገኛ ነው::
ኤላ ደሴት – ቀጣናውን በየአቅጣጫው ተዘዋውሮ ለመቃኘት፣ ለበረዶ ላይ መንሸራተቻ እንዲሁም የዱር እንስሳትን ለመመልከት ተመራጭ ነው::
በበጋ ወቅት በቀጣናው የበረዶ ንጣፍ ስለሚቀልጥ በተለያዩ ቀለማት የተንቆጠቆጡ በቅለው፣ አብበው፣ ፈጥነው የሚረግፉ የአበባ ዝርያዎችን ይለብሳል:: በባህሩ ዳርቻ ሆኖ የሚሟሟ ወይም የቀለጠ የበረዶ ቋጥኝ ሲንሳፈፍ መመልከት ለጐብኚዎች ደስታን የሚያጐናፅፍ የቀጣናው መስህብ ነው::
ለሰሜን ምስራቅ ግሪንላንድ ብሔራዊ ፓርክ በቅርበት የምትገኘው ከ500 ያላነሱ ኗሪዎች ያሏት ኦቶክኮርቶሚት የተሰኘች ከተማ ነች:: ለከተማዋ ፍሪዎች አደን እና ቱሪዝም መተዳደሪያቸው ሆኖ ያገለግላል::
ኦቶክኮርቶሚት ከተማ በዓለማችን በጣም በርቀት ወይም በማይደረስ ቀጣና የእንግዶች ማረፊያ የሚገኝባት ከተማ ናት:: ለነጠላ እና ለጥንዶች መኝታ ክፍሎች እና የምግብ አገልግሎትም ይቀርብበታል::
በከተማዋ የሚገኙ ነባር ኗሪዎችን ባህል፣ የመገልገያ ቁስ፣ ግንኙነት ወይም መስተጋብር መመልከቻ ቤተመዘክርም ነው – ኢቶክኮርቶሚት::
ለዘገባችን ፒክ ቫይዘር፣ ዋይልድ ላይፍ ወርልድ ዋይድ፣ ኦሽንዋይድ ኤክስፒዲሽን ድረገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም