የሰብል አሰባሰቡ በግጭት ውስጥ

0
133

ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት የአማራ ክልል ከ34 በመቶ በላይ ድርሻ አለው፤ ከዚህ በተጨማሪም ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ላይ ክልሉ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ባለ ጸጋ ነው:: ለአብነትም ሰሊጥ፣ ቡና፣ ቅመማ ቅመም እና መሰል ምርቶች በስፋት ይመረቱበታል:: ለዚህ ደግሞ ሁሉም አይነት የአየር ንብረት ያለው መሆኑ ነው::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ክልሉ በግጭት አዙሪት ውስጥ ከገባ አንድ ዓመትን ተሻግሯል፤ ይህም ክልሉን እና ነዋሪውን ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ዳርጎታል:: ችግሩም ከክልሉ ባሻገር እንደ ሀገር ከፍተኛ ጉዳትን እያስከተለ ይገኛል:: በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት ክፉኛ እየተጎዱ ከሚገኙ ዘርፎች መካል የግብርና ሥራ ይጠቀሳል፤ አርሶ አደሩ ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን ከማድረጉም በላይ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ አላስቻለም:: የግብርና ምርቶች ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተደራሽ ባለመሆናቸው ለኑሮ ውድነቱ ምክንያት ሆኗል::

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ እንዳስታወቀው በዘንድሮው የምርት ዘመን ከአምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታ በላይ መሬት ታርሶ በተለያዩ የሰብል ዘሮች ተሸፍኗል፤ በዚህም ከ169 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል::

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በስልክ መረጃ ያደረሱን አርሶ አደሮች እንዳሉን በችግር ውስጥም ሆነው በዘር የሸፈኑትን ሰብል እየሰበሰቡ ነው፤ ከዚህ ባለፈም ለበጋ መስኖ ልማት እየተዘጋጁ መሆኑን ነግረውናል:: በተመሳሳይ ከፍተኛ የሰሊጥ ምርት አምራች የሆነው በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከአምስት መቶ ሺህ በላይ የቀን ሠራተኞችን እንደሚፈልግ አስታውቋል፤ በአሁኑ ወቅትም የደረሱ ሰብሎች እየተሰበሰቡ መሆኑን ነው ያገኘነው መረጃ የሚያመላክተው።

በሌላ በኩል ምርት ከተጠቃሚ እስኪደርስ እስከ 35 በመቶ ብክነት እንደሚከሰት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይህም ከፍተኛ የምርት መቀነስን ያስከትላል። በመሆኑም ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም፣ የምርት ብክነትን የሚቀንሱ ስልቶችን መተግበር እንደሚገባ ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት። ለአብነትም የምርት ብክነትን ለማስቀረት ዘመናዊ የሰብል መሰብሰቢያ ማሽኖች (ኮምባይነሮች) እንዲቀርብለት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጠይቋል። ሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ጥያቄ ነው የሚያቀርቡት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰብል ምርትን በስፋት፣ በፍጥነት እና በጥራት መሰብሰብ እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳስቧል። ይህን በማድረግም በምርት ዘመኑ ለማምረት የታቀደውን ምርት ማሳካት እንደሚቻል ነው የገለጸው። እንደ ክልል አምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ያስታወሰው ቢሮው፣ በዘር የተሸፈነውን ሁሉንም ማሳ ሳያንጠባጥቡ በአግባቡ መሰብሰብ እንደሚገባ አሳስቧል። ለስኬቱም በየደረጃው ያሉ የግብርና አመራሮች እና ባለሙያዎች አርሶ አደሩን መደገፍ እና ክትትል ማድረግ ይገባል ብሏል።

በአብዛኛው  በክልሉ ምርት የሚሰበሰበው በሰው ጉልበት ነው። በመሆኑም አርሶ አደሩ የቤተሰቡን ጉልበት አስተባብሮ በባለሙያ ምክረ ሀሳብ መሠረት ምርትን በጥራት መሰብሰብ እንደሚገባ ጠቁሟል። የምርት ብክነትን በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነሮችን መጠቀም ይገባል ያለው ቢሮው ምርቱ ወደ ጎተራ እስኪገባ እና ወደ ተጠቃሚ እስኪደርስ የድህረ ምርት ተግባራትን ተግባራዊ ማድረግ  እንደሚገባ አሳስቧል።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ጥቅምት 18  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here