የሰብአዊ መብቶች ፎረም ተመሠረተ

0
135

በአማራ ክልል የሰብአዊ መብቶች ፎረም ተመሥርቷል።  ፎረሙ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን፣ ፍትሕ ቢሮን፣ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያን፣ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽንን፣ የሃይማኖት ተቋማትን እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ ነው።

 

በፎረሙ ምሥረታ የተገኙት የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ  ብርሃኑ ጎሽም እንዳሉት ሰብዓዊ መብቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣  የማይጣሱ እና የማይገፈፉ በመኾናቸው ሊጠበቁ ይገባል።

መሠረታዊ መብቶችን ለማክበር እና ለማስከበር ደግሞ ዓለም አቀፍ ሥምምነቶች በሀገሪቱ ሕግ ተካትተው  እየተሠራ ይገኛል።  ይሁን እንጂ በክልሉ በተፈጠረው ግጭት የዜጎች ሰብአዊ መብቶች ጥሰት ማጋጠሙን አንስተዋል።

 

ለዚህ ደግሞ በጸጥታ፣ በፍርድ ቤት እና  በፍትሕ ተቋማት እና በሰብዓዊ መብቶች  ላይ የሚሠሩ አካላት በተናበበ  እና በተቀናጀ መንገድ ባለመሥራት የተፈጠረ መኾኑን ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታት  የሰብዓዊ መብት ፎረም ማቋቋም ማስፈለጉን ገልጸዋል።  ፎረሙ  የፍትሕ ተቋማት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተቀናጀ መንገድ ሰብዓዊ መብቶችን  አክብረው እንዲያስከብሩ አቅም እንደሚኾን ገልጸዋል።

 

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሙሉዓለም ቢያዝን የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔዎች እና በሀገራት ሥምምነቶች መሰረት ጥበቃ የተደረገላቸው መኾናቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያም በ1987 ዓ.ም በጸደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ልዩ ጥበቃ እንደተደረገለት አንስተዋል። ሕግ አውጭው፣ ሕግ አስፈፃሚው እና ሕግ ተርጓሚው ሰብዓዊ መብቶችን  የማክበር እና የማስከበር  ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።  ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም የራሳቸውን  ሚና እንዲወጡ  ጠይቀዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባሕር ዳር ቅርንጫፍ  ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፊቶል ሲያኮር በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት መድረሱን አንስተዋል።

 

አሁንም ንጹሐን ሰዎች ችግር ውስጥ መኾናቸውን ገልጸዋል። የታጠቁ ኀይሎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን የጀመረውን የሰላም ጥረት ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ  ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በክልሉ ብሎም በኢትዮጵያ  ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ   የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መኾኑን ገልጸዋል።

 

የሰብአዊ መብቶች ፎረም መቋቋሙ መንግሥታዊ  እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች  በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ  በትብብር እንዲሠሩ አቅም እንደሚኾን ተናግረዋል።

የሰብዓዊ መብቶች ፎረም ገንቢ ውይይቶችን ለማመቻቸት፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን  እና የሰብዓዊ መብቶችን ዘላቂነት ለማረጋገጥ እንደሚያገለግል  ተገልጿል።

(ዳግማዊ ተሰራ)

በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here