የሰው ልጅ ከአካባቢው ጋር ተስማምቶ እንዲኖር…

0
121

“በተፈጥሮ ውስጥ ሁሉ ነገር እርስ በርሱ የተቆራኘ ነው። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በቀደሙት ዘመናት ለሠራናቸው ከባድ ስህተቶች ዋጋ በመክፈል ላይ ነን” ይለናል አፍሪካን ዋይልድ ላይፍ በድረ ገጹ። መረጃው አክሎም አብዛኞቹ የሰው ልጅ ድርጊቶች በቅን ልቦና የተደረጉ መሆናቸው አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የምናደርጋቸው ነገሮች በከባቢያችን ላይ ምን ዓይነት ውጤት እንደሚያስከትሉ አስቀድሞ ለማወቅ የሚያስችል እውቀት ላይኖረን ይችላል። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ውድመት ተፈጽሟል። የደቡብ አውስትራሊያ ቤተ መዘክር ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ቲም ፍላነሪ (prof.Tim Flannery) “በዚህች ሀገር የህያውያን (ፍጥረታትን) ሚዛን እጅግ በማናጋታችን መተዳደሪያችን በሆነው መሬት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰናል። በዚህ ምክንያትም የገዛ ራሳችንን ሕልውና አደጋ ላይ ጥለናል” ብለዋል።

ለሰው ልጆች ተፈጥሮ የቸረቻቸው በርካታ ፀጋዎች ቢኖሩም ፀጋዎችን በጥንቃቄ ባለመያዝ ብዙዎችን ዋጋ አስከፍሏል። በመሆኑም ተፈጥሮን መጠበቅ፣ መንከባከብ እና ማልማት ለተሻለ ህይወት መሠረት እንደሆነም ምክረ ሐሳባቸውን አስቀምጠዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ባለሙያው ላንተይደሩ ተስፋዬ የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም ሲባል የተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅ፣ መንከባከብ እና ለጥቅም ማዋል መሆኑን ያብራራሉ። የአማራ ክልል በበርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች  የታደለ፣ ለሰብል ልማት እና ለእንስሳት እርባታ ምቹ የአየር ንብረት ባለቤት የሆነ፣ ሳቢ እና ማራኪ  ገፅታን የተላበሰ ድንቅ ምድር መሆኑን ያብራራሉ። ተፈጥሮ የቸረችውን ፀጋ  የበለጠ ማልማት እና ማጎልበት ደግሞ ከህዝቦቹ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ፍጥረታት በሙሉ ጤንነታቸው እና ደህንነታቸው ተጠብቀው እንዲኖሩ የተፈጥሮ ሃብታችን በመጠበቅ እና በመንከባከብ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባልም ብለዋል። ባለፋት ዓመታት የደን ልማት፣ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ፣ የተፋሰስ እና መሠል ተግባራት ሲከናወን እንደቆየ አስረድተዋል። በተፈጥሮ የሚገኙ እንደ አፈር፣ ውኃ፣ እፅዋት እና ሌሎች የተፈጥሮ ፀጋዎችን መጠበቅ፣ ማልማት እና መጠቀም ተገቢ ነው። የሰው ልጅ ምንጊዜም ቢሆን  ነገን እያሰበ መኖር፣ አስቀድሞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት እና የመፍትሔ ሀሳቦችን በማመንጨት ወደ ተሻለ ህይወት ሊለውጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሊሠራ እንደሚገባም አክለዋል። የተፈጥሮ ሃብትን በአግባቡ ባለመጠበቅ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ እንዳይዘንብ በማድረግ፣ የመሬት መንሸራተት እና ናዳ እንዲከሰት በማድረግ ማህበረሰቡን አደጋ ላይ እየጣለው ይገኛል። በመሆኑም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በ1950 እና በ1960 ዎቹ ሰፊ የደን ሽፋን እንደነበር ያስታወሱት ባለሙያው ከዛ ወዲህ በተሰጠው አነስተኛ ትኩረት የደን ሽፋኑ በእጅጉ አሽቆልቁሎ እንደነበር ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ባለፉት ስድስት ዓመታት ለአረንጓዴ አሻራ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እየተሻሻለ እንደመጣ እና የተራቆተው መሬት በደን እየተሸፈነ መሆኑን ያብራራሉ። ወደፊትም ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑንም በማከል። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። የደን ሽፋኑ እና የጽድቀት መጠኑም ቢሆን በየጊዜው እየተሻሻለ የመጣ መሆኑን ማየት  ተችሏል ብለዋል። ይህም የሆነው ማህበረሰቡ/አርሶ አደሩ/ በእኔነት ስሜት ተንከባክቦ በመሥራቱ የተገኙ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል። ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ከተከላ በኋላም ባለቤት እየተሰጠው ለትውልድ ተሻጋሪ በሚሆን የልማት ቅብብሎሽ እና በልማቱም  ራሱ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ መሆኑን ማሳየት ተችሏል ብለዋል። በተለይም የስነ ህይወታዊ የአፈር ጥበቃ ሥራዎች ሲከናወኑ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ያላቸውን አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም የሳር ዝርያዎችን በመዝራት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደሚቻልም አመላክተዋል።

የአፈር እና ውኃ ጥበቃ፣ የአንድ ጀንበር አረንጓዴ  አሻራ ተከላ እና እንክብካቤ ሥራዎች እየተሻሻሉ መጥተዋል። በተሠራው የአረንጓዴ አሻራ ሥራም ክልሉ ካሁን በፊት ከነበረው 13 ነጥብ 9 በመቶ የደን ሽፋን ወደ 16 ነጥብ ሶስት በመቶ መድረሱን ገልፀዋል። ከዚህ በፊት ተመናምነው የነበሩ ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን መልሶ በማልማት አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል። የደን ሽፋኑ እየጨመረ  በመምጣቱም ተሰደው የነበሩ የዱር እንስሳት እንዲመለሱ በር እንደከፈተ አስረድተዋል።

ህብረተሰቡን በማነቃነቅ እና ሰፊ ርብርብ በማድረግ በተሠሩ ሥራዎች የአፈር ክለትን በመቀነስ፣ ለምነቱን መጨመር፣ በተለያዩ የማልሚያ ስትራቴጂዎች ደንን በማልማት የደን ሽፋን መጠንን በማሳደግ እንዲሁም የገፀ ምድር እና የከርሰ ምድር ውኃን ማበልፀግ እንደተቻለ አብራርተዋል። የውኃ ምንጮች እየጎለበቱ በመምጣታቸውም ለመስኖ ልማት ሥራ ጠቀሜታቸው እየጎላ መምጣቱን አስረድተዋል። ይህም ምርታማነትን በማሳደግ ለውጦች ታይተዋል ነው ያሉት።

በ2017 ዓ.ም የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራን በስኬት ለመፈፀም ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሲከናወን ቆይቷል። በተፋሰስ ልየታ፣ የልማት መሳሪያዎችን በማዘጋጀት፣ የቀያሽ አርሶ አደሮች ስልጠና በመስጠት፣ የባለሙያ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት፣ በአጠቃላይ በሰው ኃይል እና በማልሚያ መሳሪያዎች ልየታ እና በሌሎችም ተግባራት በቂ ዝግጅት መደረጉን ባለሙያው አብራርተዋል።

በበጋ ወራት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ፣ ችግኝ በዓይነት እና በመጠን በተገቢው መንገድ ማፍላት፣ የተጎዱ እና የተሸረሸሩ መሬቶችን የመለየት እና የማልማት ሥራዎች ይከናወናሉ። በክረምት ወራት ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ ልማት (የችግኝ ተከላ) የሚከናወን ሲሆን የተራቆቱ እና በደን ያልተሸፈኑ አካባቢዎችን በደን ለመሸፈን ርብርብ የሚደረግበት ወቅት ነው ብለዋል።

በመሆኑም በዘንድሮው  የተፋሰስ ልማት ከጥር ወር ጀምሮ ወደ ተግባር ተገብቷል። በዚህም በዘጠኝ ሺህ 87 ተፋሰስ ለማልማት ታቅዶ ስምንት ሺህ 600 የሚሆነው ተለይቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። እንዲሁም 370 ሺህ 648 ሄክታር መሬት ላይ  የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎችን ለማከናወን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። ከዚህ ባሻገር መጤ እና አደጋኛ አረሞችን ለማስወገድ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው 4 ሚሊዮን 144  ሺህ 998 ማህበረሰብ  ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት። በክልሉ በ2017 ዓ.ም “የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ለዘላቂ ምርታማነት ዕድገት” በሚል መሪ ሀሳብ የተቀናጀ የማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል። ተፋሰስን ካለማን ዘላቂ የሆነ ምርታማነትን ማምጣት እንደሚቻል ያመላክታል ብለዋል። ከጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር እንደሚገባም አመላክተዋል።

ባለፉት ዓመታት ግብርና ቢሮ የሠራቸውን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎችን መነሻ በማድረግ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና አማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት “የተፈጥሮ ሃብት ከየት ወደ የት” በሚል ጥናቶችን ማካሄዳቸውን የተናገሩት ባለሙያው በዚህም አበረታች ለውጦች መገኘታቸን ገልፀዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ  ሰፊ የውኃ አማራጮች መገኘታቸውን፣ የተመናመኑ ደኖች እንዲመለሱ ማድረጉ እና የሰብል ምርታማነት ከፍ እንዲል አስተዋፅኦ ማበርከቱን አመላክተዋል። የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃ እና አጠቃቀም ዓመቱን ሙሉ የሚሠራ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

እርከን የሚሠራባቸው ቦታዎች የመሬት ከፍታቸው የተለዩ እና በጥናት የተረጋገጡ መሆን እንዳለባቸው አስረድተዋል። እንዲሁም የመሬቱ ተዳፋትነት የተለየ እና የባለሙያ ምክረ ሐሳብን መከተል ይገባል። እርከን ሰርቶ መልሶ የማፍረስ እና የመድፈን ችግሮች አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ያነሱት አቶ ላንተይደሩ  አርሶ አደሩ የሠራቸውን እርከኖች ከማፍረስ ተቆጥቦ መሬቱን መጠበቅ እና መንከባከብ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል። ባለፈው ዓመት በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት እና አለመረጋጋት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ማከናወን እንዳልተቻለ አመላክተዋል። በዚህ ዓመትም በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት እንቅፋት ሊሆን ስለሚችል አርሶ አደሩ ባለሙያው ወደ አካባቢው በማይደርስባቸው አካባቢዎች በባለቤትነት ስሜት እንዲያከናውን አሳስበዋል።

በመጨረሻም የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ተግባራት  ዓመቱን በሙሉ የሚሠራ መሆኑን በመረዳት ለተሻለ ህይወት እና ምርታማነትን ለመጨመር ሁሉም መረባረብ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ  ሃብት ጥበቃ ውጤታማ ሊያደርጓት የሚችሉ  ፖሊሲዎችን እና አዋጆችን ቀርጻ እየሠራች መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ሀገር አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ንቅናቄን ባስጀመሩበት ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም ነው።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ እንዳሉት 50 በመቶ የሆነው የደጋማው የሀገራችን ክፍል በአስቸጋሪ የአፈር መሸርሸር የተጋለጠ ነው ብለዋል።  መንግሥትም ይህንን ችግር በመረዳት ለመፍትሔው እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

የአፈር ጥበቃ እና የአረንጓዴ አሻር መርሐ ግብርን ተግባራዊ በማድረግ የደን ሽፋንን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉንም  ጠቅሰዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ.ር)  ኢትዮጵያ  በየዓመቱ አንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን ቶን አፈር በመሸርሸር  እንደምታጣ አመላክተዋል። ባለፉት 20 ዓመታት 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ መልሶ እንዲያገግም ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

አጠቃላይ እንዲያገግም ከተደረገው መሬት 24 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኅብረተሰቡ  አቅም እንዲገነባ የተደረገ ነው ብለዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here