የሱዳን ግጭት እና የሰላም ተስፋዉ

0
168

በዓለማችን ትልቁ ኢሰብዓዊ አደጋ ደቅኖ ያለ ነገር ግን ዓለማቀፍ ትኩረት የተነፈገው፣ የተረሳው የሱዳን ችግር በቅርቡ ማነጋገር ጀምሮ ነበር። በቅርቡ በአሜሪካ አነሳሽነት የችግሩ አሳሳቢነት ለመንግሥታቱ ድርጅት ቀርቦ የመፍትሄ ውሳኔ የተላለፈበት አበይት ክስተት ከተዘገበ ወዲህ መንግሥታት በተናጠል ጉብኝት ማድረግ ጀምረዋል።

ከጦርነቱ መጀመር ወዲህ የውጭ ጉብኝት ሲያደርግ የመጀመሪያው የሆነው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሱዳኑ ከጄኔራል አልቡርሃን ጋር በፖርት ሱዳን ተገናኝተው ተወያይተዋል። ሁለቱ መሪዎች እየተካሄደ ባለው ግጭት እና ለሰላም አስተማማኝ መንገዶችን መፈለግን በተመለከተ መወያየታቸውን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።

እንደ ሱዳን ትሪቡን ዘገባ ዐቢይ አሕመድ ፖርት ሱዳን እንደደረሱ በጄኔራል አልቡርሃን  ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።   የሉዓላዊነት ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ መሰረት አልቡርሃን ለጎብኚው ጠቅላይ ሚንስትር ሱዳን ውስጥ ስላለው ሁኔታ በማብራራት፣ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በመንግሥታቸው እና በተቋማት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በስሱ አብራርተውላቸዋል።

አልቡርሃን እንደተናገሩት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ  በንፁኃን ሱዳናውያን ላይ ጉዳት እየፈፀመ፣  በመንግሥት መሰረተ ልማት ተቋማትን በማውደም እና ብሔራዊ ተቋማትን ኢላማ በማድረግ እያወደመ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ የተመለሱ ሲሆን የሰላምን አስፈላጊነት ለልማት አፅንኦት ሰጥተዋል። የሀገራቱ ችግሮች ያለምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በውስጥ መፈታት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በተጨማሪም “እውነተኛ ወዳጅ በችግር ጊዜ የሚደርስ ነው፣ “ በማለት ከሱዳናውያን ጋር ያላቸውን ወዳጃዊ ስሜት አለው። ኢትዮጵያ ለሱዳን መንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ደረጃ ያላትን የማይናወፅ ድጋፍ በማረጋገጥ እና ጦርነቱ እንደሚቆም ያላቸውን መተማመን ገልፀውላቸዋል። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትም ከምንጊዜውም በበለጠ የጠነከረ እንደሚሆን ገልፀውላቸዋል።

ሁለቱ መሪዎች በሱዳናውያን ቀውስ እና ጦርነቱን በሚቋጭበት ሁኔታ በዝግ ስብሰባ ተወያይተዋል።

የሱዳን እና የኢትዮጵያ መሪዎች በምስራቃዊ ሱዳን ባለው ሁኔታ ዙሪያም፣ በፈጥኖ ደራሹ በገዳሪፍ ጥቃት ሊፈጽም እንደሚችል እና ግጭቱ ወደ ኢትዮጵያ የመዛመት አቅም ያለው መሆኑን ያካተተ ውይይት ስለማድረጋቸው የተለያዩ ዘገባዎች ወጥተዋል።

ምንጮች እንዳመለከቱት የጠቅላይ ሚስትር ዐቢይ አሕመድ ፖርት ሱዳንን መጎብኘት ተከትሎ ከሱዳን የአሜሪካ ተወካይ፣ እና ከሳኡዲ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የስልክ ጥሪዎች ተደርገውላቸው ተነጋግረዋል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሱዳን ጦርነት ውስጥ ከየትኛውም ኃይል ጋር እንዳማትወግን ስትገልጽ ቆይታለች። ይህ በሱዳን ሰላም ለማምጣት ለተደረገው ጉዞ ለሱዳን መረጋጋት የኢትዮጵያው መሪ የሚያከናውኑት ጥረት ቀጣይ እርምጃ መሆኑን  ነው።

ሁለቱን የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ወደ ሰላም ለማምጣት ያለመው የአዲስ አበባው ውይይት ለአምስት ቀናት እንደሚቆይ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ሰኔ 14 ቀን  2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ገልጾ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ ሐምሌ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ፖርት ሱዳን አየር ማረፊያ ሲደርሱ፣ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር እና የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሌተናንት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና ሌሎች ባለሥልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፖርት ሱዳን ያደርጉት ጉብኝት ሱዳን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ከገባች በኋላ በአንድ ሀገር መሪ የተደረገ ይፋዊ ጉብኝት ነው ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከጄኔራል አል ቡርሃን ጋር ውይይት ከማድረጋቸው በተጨማሪ በኢትዮጵያ እያካሄዱት እንዳለው ሁሉ እዚያም ችግኝ ተክለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ከሱዳን የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ፓናል እና ከኢጋድ ጋር በመተባበር በሱዳን ያለውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለመቋጨት፣ ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ወደነበረበት ለመመለስ እና ሕዝብ መራሽ መፍትሄ ለማግኘት ይህ ውይይት ትኩረት እንደሚያደርግ የምክር ቤቱ መግለጫ አስታውቋል።

ከአዲስ አበባው ቀደም ብሎም በግብፅ መዲና ካይሮ ውይይት እንደሚደረግም የአፍሪካ ኅብረት ከሳምንታት በፊት ባወጣው መግለጫው አመልክቶ እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ ያስረዳል።

ምክር ቤቱ “ጎረቤት አገራት ከአፍሪካ ኅብረት እና ከኢጋድ ጋር በመሆን ለሱዳን በተጀመረው ሰላም የማምጣት ጥረት ላይ ላላቸው ሚና ምስጋናውን” ገልጿል።

የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር በኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የሚመራ ኮሚቴ በማቋቋም በአጭር ጊዜ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪዎች መካከል የሚደረጉ ውይይቶችን እንዲያመቻች ተልዕኮ እንደተሰጠው መግለጫው አክሏል።

ምክር ቤቱ “ወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ጦርነቱን እያባባሱ ያሉ የውጭ ተዋንያን ከተግባራቸው ይቆጠቡ” ሲልም አሳስቧል።

በሙሴቬኒ የሚመራው ኮሚቴ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እና ከአፍሪካ የመረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት (ሲ አይ ኤስ ኤስ) ጋር በመተባበር “ለተፋላሚዎች ወታደራዊ፣ የገንዘብ እና የፖለቲካዊ ድጋፍ የሚሰጡ የውጭ አካላትን የመለየት ኃላፊነት ተሰጥቶታል” ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here