የሳቅ ምንጩ ቻርሊ ቻፕሊን

0
250

ቁጡ እና ነጭናጫ ባህሪ ነበረው ይባላል። በሕይወት ዘመኑ 81 ፊልሞችን ሠርቷል። እ.ኤ.አ ከ1914 እስከ 67 በነበሩት ዓመታት የሠራቸው በድርጊት የተሞሉ ድምጽ አልባ ፊልሞች ቻርሊንን የሳቅ ምንጭ አድርገውታል። ሞደርን ታይምስ፣  ሲቲ ላይትስ፣ ዘ ግሬት ዲክታተር፣ ዘኪድ፣ ጎልድ ራሽ እና ሌሎቹም ፊልሞች ጎልተው ይጠቀሱለታል። ፊልሞቹ አጫጭር ናቸው።  ብዙዎቹ ከ26 ደቂቃ የሚበልጡ አልነበሩም። አንድ ፊልምን ለመሥራት አስቦ የሚፈልገው ዓይነት ሐሳቡ እስካልተሠራ ድረስ ለመደጋገም ችግር አልነበረበትም። ለስራ ጥራት እና ተወዳጅነት አብዝቶ በመድከም የሚያምን ሰው ነበር ይባላል። የ20ኛው ክፍለ ዘመን የሳቅ ምንጭ ኮሜዲያን ቻርሊ ቻፕሊን። እንዲያውም አንዳንዶቹ ፊልም አባካኙ ቻርሊ ይሉታል። ይቀርጻል፤ ያየዋል፤ አይጥመውም፤ ፊልሙን ጥሎ እንደገና መቅረጽ ይጀምራል። ካልጣመው ደጋግሞ ብዙ ፊልሞችን ለመቅዳት የሚከብደው ይሉንተኛ ሰው አልነበረም። ተዋናዮች ይሰለቹበት ነበር። እሱ ግን አይሰለችም። “ተዋናዮች መተው ነው የሚፈልጉት፤ የሚተውት ነገር ባይተዋቸው እነሱ ራሳቸውን ይተዋሉ” ብሎ ተናግሯል።

ከ1914 እስከ 22 ባሉት ዓመታት ቻርሊ ኪይ ስቶን፣ ኢሳኒ፣ ሙቹዋል እና ናሽናል ስቱዲዮ ከተባሉ የፊልም ድርጅቶች ጋር ሰርቷል። በእነዚህ ዓመታትም 65 ፊልሞችን አበርክቷል። በዚህ ጊዜ በሳምንት ከ150 ዶላር ክፍያ በመነሳት እስከ 1,200 ዶላር ክፍያ በሳምንት በማሳደግ ሀብታም መሆን ቻለ። ከ1915 እስከ 16 ባለው ጊዜ ኢሳኒ ከተሰኘው ኩባንያ ጋር 14 ፊልሞችን በመስራቱ ደሞዙ በሳምንት 10ሺህ ዶላር ደረሰ። 150ሺህ ዶላር ጉርሻም አገኘ። በመቀጠልም የግሉን ስቱዲዮ ከፍቶ የፊልም ዳይሬክተር እና ተዋናይ፣ አዘጋጅ፣ ጸሐፊ፣ አቀናባሪ፣ ሙዚቃ ተጫዋች ሆነ። ቻርሊ በ26 ዓመት ዕድሜው  ሙቹዋል ከተባለው የፊልም ኩባንያ ጋር ባደረገው ስምምነት 670 ሺህ ዶላር በዓመት ይከፈለው ነበር። በዚህም  በወቅቱ ከባለጸጋዎች ዝርዝር ውስጥ  መግባት ችሏል።

ቻርሊ በግሉ ፊልም ጽፎ  ማዘጋጀት የጀመረው በ1923 “ውመን ኦፍ ፓሪስ” በተሰኘው ፊልሙ ነበር። ጎልድ ራሽ፣ ሲቲ ላይትስ እና ሰርከስ የሚሉ ፊልሞቹንም እስከ 1931 በመስራት ለሕዝብ አደረሰ።  ዘ ሰን ድረገጽ “በዚህ ጊዜ  ድምጽ አልባ ፊልሞች የሚሰሩበት ጊዜ እያበቃ ቢመጣም እንኳን ፣ ቻርሊ ግን ትራምፕ የሚል ገጸ ባህሪውን ተላብሶ ቀጠለ” ይላል። በ1940 “ዘ ግሬት ዲክታተር” በሚለው ፊልሙ ላይ ቻርሊ መንታ ገጸ ባህሪያትን ወክሎ ተጫውቷል። በዚህም የአዶልፍ ሂትለርን ዘረኝነት እና ጭካኔ ለማሳየት ሞክሮበታል ይላል ዘ ሰን። ይህ ፊልም ቻርሊ ለመጀመሪያ ጊዜ በድምጽ የሰራው ፊልሙ ነው። በፊልሙ ማጠናቀቂያ ላይ ሰብዓዊነት እና ሰላም ለምድር ያስፈልጋል በሚል ቋጭቶታል። ይህንን ሀሳብ የምንጊዜም ጠንካራ መልእክቱ ነው ይሉለታል። ይህም የምንጊዜም አይረሴ ጠንካራ ፊልም እንዲሆን አድርጎታል ይላል ዊዲንግ ማጋዚን ድረገጽ። ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ትችቶችን በድምጽ አልባ ፊልሞች በማሳየት ሳቅ መፍጠር እና ማሳየት የቻለ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ባለ ብዙ ተሰጥኦ ጥበበኛ ነው ቻርሊ። በዘመኑ አንድም ቃል ሳይናገር የሰዎችን ስሜት ከፍ እና ዝቅ ማድረግ የቻለ ሰው ነው። እ.ኤ.አ በ1952 ቻርሊ በአውሮፓ ጉዞ በማድረግ ሥራዎቹን  ያሳይ ነበር። ኮሚዩኒስት ነህ በሚል ወደ አሜሪካ እንዳይገባም ክልከላ ተደረገበት። በ1910 ተዘዋውሮ የሠራባት አሜሪካ ከዓመታት በኋላ አትድረስብኝ አለችው። በ1972 ቻርሊ ለፊልም ኢንዱስትሪው ላበረከተው አስተዋጽኦ አሜሪካ ልታመሰግነው ጠራችው። ከሀያ ዓመታት በኋላ አሜሪካ መግባት ቻለ። ይሁን እንጂ ሕይወቱ እስካለፈበት 1977 ድረስ በስዊዘርላድ ለመኖር ተገዷል።

ትልቅ ሸፋፋ ጫማ፣ ፍጥጥ ያለ ዓይን፣ ባርኔጣ፣ ከአፍንጫው በታች የተከማቸች ጺም፣ ሰፊ ሱሪ እና አጭር ኮት አድርጎ ከዘራውን ይዞ በፍጥነት ሲጓዝ፣ ሲተውን የሚታወቀው ቻርሊን የሚወክለው ገጸ ባህሪ ትራምፕ ይባላል። ይህ ገጸ ባህሪ እንኳን በድርጊት ታጅቦ ይቅርና ሲመለከቱትም የማሳቅ አቅም አለው። ይህ አኳዃኑ በብዙዎች ዘንድ የተወዳጅነት እና አይረሴነትን አቅም ሰጥቶታል። የቋንቋ ድንበርን  ተሻግሮ  በመላው ዓለም ለመሰማት ችሏል። ቀልድ እና ቧልትን ለማህበራዊ ንቃት መሳሪያነት ተጠቅሞበታል።  በስምንት ዓመት ከጓደኞቹ ጋር ስራውን በዳንስ ቡድን ውስጥ የጀመረው ቻርሊ በ88 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል። ቻርሊ ስለ ቀልድ ፊልም ሲናገር “ፊልም ለመስራት ቆንጆ ሴት፣ ፓርክ እና ፖሊስ ብቻ ነው የሚያስፈልገኝ” ብሏል። ፖሊሱ ይጠብቀዋል፣ ፖርኩ የቀረጻ ቦታው ነው። ቆንጆዋ ሴቷ ምን እንደሆነች ለመገመት ያስቸግራል። ለትወና ከሆነ ከወንዶችም ጋር ብዙ ሰርቷል። እና ታዲያ ሴቷን በልዩነት ለምን ፈለጋት? ራሱ ያውቅ። ለፊልም ስራዎቹ በኦስካር ተሸልሟል። የእንግሊዝ ንግሥት አልሳቤት ሁለተኛም ክብር ሰጥተውታል። እንዲያውም ያን ጊዜ የበለጠ ዝናው በመላው ዓለም ተሰምቷል። ምናልባት ከዚህ ጊዜ በኋላ ሊሆን ይችላል ቀጥሎ የምታነቧትን ንግግር የተናገራት። “ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መኖር ያልሰሙ ሰዎች ሁሉ ያውቁኛል” ሲል ዝናውን ተናግሯል። የኦስካር ሰዎች ሲሸልሙትም ብዙም አልተደሰተም። ስለ ኮሜዲ ስራ ሲናገር “ ሕይወት በቅርበት ስትታይ ጨፍጋጋ ናት። ቀልድ ግን ራቅ ብሎ መመልከት ነው” ይላል።

የቻርሊ ቻፕሊን ሥራዎቹ  ዛሬም ድረስ ሳቅን ፈጥረው የማዝናናት እና የማስተማር አቅም እንደያዙ ቀጥለዋል። ድህነት፣ ኢ ፍትሐዊነት እና የመደብ ትግልን በፊልሞቹ ለማሳየት ሞክሯል። ባዮግራፊ ድረገጽ እንዳሰፈረው ቻርሊ ከሆሊውድ ጋር እንዲሰራ ግብዣ ቀርቦለት ያውቃል። ይሁን እንጂ ቻርሊ በራሱ መንገድ ቀልድ ለማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ ፍትሕ እና እኩልነት መሳሪያነት ለመጠቀም በማሰብ ፈቃደኛ አልሆነም። ሆሊውድ የሚያሳየውን ዘረኝነት ያቆም ዘንድ ዘ ግሬት ዲክታተር ፊልም ትልቅ ቁንጥጫ ነበር የሚሉ ብዙ ናቸው። በዚህ ፊልም ጀርመን በአይሁዶች ላይ የምታደርሰውን ዘረኝነት እና ጭካኔ ለማሳየት ሞክሯል። በ1936 የወጣው “ሞደርን ታይምስ”  ፊልሙ የፋብሪካ ሰራተኞችን አስቸጋሪ ሕይወት ያሳየበት ነው። በፊልሙ ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ ግጭቶች፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ኢፍትሐዊነት፣ ጭካኔ እና የማሽን አደጋዎችን አሳይቶበታል።

ፈረንሳይ ውስጥ በ1889 የተወለደው ቻርሊ ቻፕሊን በድህነት እና ፍቅር ማጣት ነው ያደገው። እናቱ ሙዚቀኛ፣ አባቱ ደግሞ የመድረክ ሰው ነበሩ። አባቱ የአልኮል ሱሰኛ እና እናቱ ደግሞ የአዕምሮ በሽተኞች በመሆናቸው ራሱን ለማኖር ሲል በጎዳናዎች ያገኛቸውን ሥራዎች በመስራት አድጓል። ልጅነቱ ሳቅ እና ፍቅር የራቀው ነበር። ቀልዶቹ በውስጡ ያጣውን ሳቅ ለመፍጠር የሰራቸው ናቸው በማለት ፊልሞቹን ሒስ የሚሰሩባቸው ብዙዎች ናቸው። እሱም ሲናገር “ሳቅ የሌለበት ቀን የባከነ ነው” ይላል።

ቻርሊ ቻፕሊን በትዳር ሕይወቱ በዕድሜ ታናናሽ ሴቶችን በማግባት ተደጋጋሚ ታሪኩ ላይ ሰፍሯል። የመጀመሪያ ሚስቱ የኪነ ጥበብ ሰው ነበረች። የፍቅር ግንኙነቱ ተጀምሮ ሳለ አረገዘች። ሚልደልድ ሃሪስ ትባላለች፤ 16 ዓመቷ ነበር። በ1918 ተጋብተዋል። በሀገሪቱ ሕግ ከ18 ዓመት በታች የሆነች ሴት ማግባት ስለማይቻል ጋብቻው በስውር ተከናውኗል። የተረገዘው ልጅ በተወለደ በቀናት ውስጥ በመሞቱ ጋብቻቸውም ብዙ አልቆየም። ከሁለት ዓመት በኋላ ተለያዩ።

ሊታ ግሬይ የቻርሊ ሁለተኛ ሚስት ነበረች።  ይህችም ሴት ዕድሜዋ 16 ነበር። ዘ ኪድ እና ጎልድ ራሽ በተሰኙት ፊልሞች ውስጥ አብራው ሰርታለች። በ1924 ተጋብተው  በ1927 እስኪለያዩ ሁለት ልጆችን ወልደዋል። በፍርድ ቤት ከፍተኛ ክርክር ተደርጎበት ትዳራቸው ፈርሷል። ፓውሌቲ ጎዳርድን ሦስተኛ ሚስቱ አድርጎ ሲያገባ እሷ የ25 ዓመት ሴት ነበረች። ጊዜው 1936 እ.ኤ.አ ነበር። ሞድርን ታይምስ እና ዘዲክታተር በሚሉ ፊልሞች ላይም አብረው ሰርተዋል። ኦና ኦኒልን ደግሞ ለአራተኛ ጊዜ በ1943 አገባት። ይህችም ልጅ የ18 ዓመት ታዳጊ ነበረች። ከዕድሜ ልዩነት በቀር ፍቅር እና ደስታ ነበራቸው። ቻርሊ በዚህ ጊዜ 53 ዓመቱ ነበር። ኦና ቻርሊንን ያገኛት አሁንም ለሕዝብ ሳይደርስ በቀረ ፊልሙ ላይ ለመስራት በተዋወቁበት ጊዜ ነበር። ይህች ሴት እና ቻርሊ የሕይወት ዘመናቸውን በሙሉ አብረው ኖረዋል። በአስቸጋሪ ጊዜውም ሁሉ አብራው ነበረች። ስምንት ልጆችን ወልደዋል። ቻርሊ በአጠቃላይ 11 ልጆች ነበሩት።

“ልጅነቴ አሳዛኝ ነበር። አሁን ግን ትዝታ ሆኗል። ልክ እንደ ሕልም ይታየኛል” ያለን የሳቅ ምንጩ ቻርሊ ቻፕሊን በተወለደ በ88 ዓመቱ ለረጅም ዓመታት በኖረበት ስዊዘርላንድ በ1977 እ.ኤ.አ ሕይወቱ አልፏል። አሻራ ያለው ሰው ለካንስ አይሞትም። አይረሳም። ፊልሞቹን ዛሬም ሚሊዮኖች ይዝናኑባቸዋል።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ጥቅምት 18  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here