የሳዑዲ ስፖርት ገበያ

0
162

ሳዑዲ አረቢያ በመካከለኛው ምሥራቅ በፍጥነት እያደገች ያለች ሀገር ስትሆን ከ34 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት ይገመታል። ሀገሪቱ ምጣኔ ሀብቷን ለማሳደግ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ በማፍሰስ ላይ ትገኛለች። ሳዑዲ ታላላቅ የስፖርት ሁነቶችን እና መድረኮችን በማዘጋጀት የውጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ  በትኩረት እየሠራች ነው።

የሀገሪቱ የስፖርት ሚኒስቴር ልዑል አብዱላዚዝ ቢን ቱርኪ አል ፋይሰል ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሳዑዲ አረቢያ በስፖርቱ ዘርፍ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ እያፈሰሰች መሆኗን ከቢቢሲ ስፖርት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። እንደ ሚኒስቴሩ ገለፃ ሳዑዲ አረቢያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አምስት ቢሊዮን ፓውንድ ገንዘብ ለስፖርት ዘርፉ አውጥታለች።

አልጋ ወራሹ ሙሀመድ ቢን ሳልማን ስፖርት የሀገራቸውን አጠቃላይ ምጣኔ ሐብት በአንድ በመቶ ማሳደጉን ተናግረዋል። አልጋ ወራሹ ልዑል ሀገራቸው በነዳጅ ዘይት ላይ ያላትን ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ለመቀነስ ታስቦ በዕቅድ እየተሠራ ነው ብለዋል።እ.አ.አ. እስከ 2030 የሚቆይ አዲስ ዕቅድ ይዘው እየሠሩ ሲሆን “ራዕይ 2030” የሚባል አዲስ የስፖርት ፍኖተ ካርታም ነድፈዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስፖርቱ ዘርፍ የሳዑዲ አረቢያን ያህል በጀት መድቦ እየሠራ ያለ ሀገር ማግኘት ይከብዳል። ሳዑዲ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሰብአዊ መብት አያያዝ በተለይ ደግሞ ለሴቶች ነፃነት ትነፍጋለች በሚል በተደጋጋሚ በምዕራባውያን ክስ ይቀርብባት እንደነበረ አይዘነጋም። አሁን ላይ ግን ማሻሻያዎችን አድርጋ ሴቶች መኪና መንዳት እንዲችሉ እና ስቴዲየም ገብተው ውድድሮችን እንዲመለከቱ ፈቅዳለች። አሁን ደግሞ የጎደፈውን ገጽታዋን በስፖርት ለመቀየር እየሠራች መሆኗን መረጃዎች አመልክተዋል።

የ2022ቱን የዓለም ዋንጫ ጎረቤቷ የሆነችው ትንሿ ኳታር በስኬት ማዘጋጀቷን ተከትሎ ሳዑዲ ፊቷን ወደ ስፖርቱ እንድታዞር ምክንያት ሆኗል። ለዘርፉም ረብጣ ቢሊዮን ዶላሮችን ፈሰስ እያደረገች ነው። የሳዑዲ አረቢያ ማርሽ ቀያሪው የስፖርት አቢዮትም ከዚህ ይጀምራል። እ.አ.አ በ2021 የሳዑዲ ባለሀብቶች የእንግሊዙን ክለብ ኒውካስትል ዩናይትድን በመግዛት የስፖርት ኢንቨስትመንቱን መቀላቀላቸውን ይፋ አድርገዋል።

በዚህ ብቻ ሳያቆሙ ከፈረንጆች 2023 ጀምሮ በርካታ የአውሮፓ የእግር ኳስ ኮከቦችን ወደ ሳዑዲ ፕሮ ሊግ በማስኮብለል እግር ኳሳቸውን ለማሻሸል እየተጉ ነው። እ.አ.አ በ2023 ወርሀ ጥር ክርስቲያኖ ሮናልዶ የሳዑዲውን ክለብ አልናስርን መቀላቀሉን ተከትሎ በሳዑዲ ፕሮ ሊግ አዲስ የእግር ኳስ አብዮት ተቀስቅሷል።

የእርሱን ፈለግ በመከተል ኔይማር ጁኒዬር፣ ካሪም ቤንዜማ፣ ሳዲዮ ማኔ፣ ንጎሎ ካንቴ እና የመሳሰሉት  በርካታ ታላላቅ የእግር ኳስ ኮከቦች  መዳረሻቸውን አልናስር፣ አልሂላል፣ አል አህሊ፣ አል ኢትሀድ እና አል ኢትፋቅ አድርገዋል።

የታላላቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በሳዑዲ ክለቦች መገኘት ለእግር ኳሱ እድገት ከሚያበረክተው አወንታዊ አስተዋጽኦ ባሻገር የሀገሪቱን ገጽታ ይገነባል። ይህ ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ በ2030 በፈረንጆች የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት በምታደርገው እንቅስቃሴ ያግዛታል ተብሎ ይገመታል።

ሀገሪቱ ከዚህ ጎን ለጎን  የታላላቅ የስፖርት ሁነቶች እና መድረኮች መዳረሻ እየሆነች መምጣቷንም ዘ አትሌቲክ አስነብቧል። የሀገሪቱ መንግሥት ለስፖርት ዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት የስፖርት ሁነቶችን እና መድረኮችን መሳብ ችሏል። በቂ የስፖርት መሰረተ ልማቶች መኖራቸው እና ከተትረፈረፈው የነዳጅ ሀብቷ ውድድሮችን ስፖንሰር ማድረጓ የስፖርት ሁነቶች ወደ ሀገሪቱ ሊጎርፉ እንደቻሉ ነው የተዘገበው።

በ2023 እ.አ.አ የዓለም ክለቦች ዋንጫን ማዘጋጀቷ አይዘነጋም። በማንቸስተር ሲቲ እና በብራዚሉ ክለብ ፍሉሚንሴ መካከል የተደረገውን የዓለም ክለቦች ዋንጫ የእንግሊዙ ክለብ ዋንጫውን ማንሳቱ የሚታወስ ነው።

በቀጣይ በፈረንጆች 2027 የእስያ ዋንጫን ለማዘጋጀት ዝግጅት መጀመሯንም መረጃዎች አመልክተዋል። ሳዑዲ አረቢያ ከዚህ በፊት የጣሊያን እና የስፔን ሱፐር ዋንጫን ማዘጋጀቷ የሚታወስ ነው። ይህም ሀገሪቱ በስፖርት ኢንቨስትመንት የደረሰችበትን ደረጃ ያሳያል ብሏል መረጃው።

በቀደሙት ጊዜያት ታላላቅ የቡጢ ስፖርት ሁነቶች የሚደረጉት በአሜሪካ ላስ ቬጋስ ከተማ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ላስቬጋስ እ.አ.አ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ታላላቅ የስፖርት ሁነቶችን ማስተናገድ እንደጀመረች ይነገራል።

በተለይ የቡጢኞች ቀዳሚ ምርጫም ነበረች ይባላል ላስ ቬጋስ ከተማ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በቡጢኞች ዐይን ከቬጋስ ይልቅ ሪያድ ገዝፋ መታየት ጀምራለች። አሁን ላይ ቬጋስ ከተማ በሪያድ የተበለጠችም ትመስላለች።

የሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድም አዲሷ የቡጢኞች መፋለሚያ ከተማ ሆናለች። በ2019 እ.አ.አ አንቶኒ ጆሹዋ የመካከለኛዋ ምሥራቅ ሀገርን ከጎበኘ በኋላ ከአንዲ ሩዚ፣ ከዲዎንታይ ዋይልደር፣ ከታይሰን ፉሪ እና ከመሳሰሉት ጋር ግጥሚያውን በሪያድ አድርጓል። እንደ ቡጢኞች አስተያየትም ከሚያገኙት ከፍተኛ ገንዘብ በተጨማሪ ሀገሪቱ ለውድድር ምቹ መሆኗን ተናግረዋል።

የባህረ ሰላጤው ሀገራት መሪዎች እና ንጉሦች ለፈረስ እሽቅድድም ስፖርት ከፍተኛ ፍቅር እንዳላቸው ይነገራል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኳታር ከዚህ በፊት የዘርፉን ትልቅ ሁነት ያዘጋጁ ነበር። ሳዑዲ አረቢያም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግዙፉን የፈረስ እሽቅድድም ውድድር ማዘጋጀት ጀምራለች። ለመድረኩም 20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓ ተዘግቧል።

እ.አ.አ በ2021 የሳዑዲ ባለሀብቶች ኒውካስትል ዩናይትድን በገዙበት ዓመት በሳዑዲ አረቢያ በየ ዓመቱ የሚደረግ ግዙፍ የጎልፍ የውድድር መድረክ ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል። ይህ ዜና ለመካከለኛው ምሥራቅ የጎልፍ አፍቃሪ መልካም ዜና ሲሆን በሌላው ዓለም ዘንድ ግን የተደበላለቀ ስሜትን ፈጥሮ አልፏል።

ዓለም አቀፉ የጎልፍ ማህበር ከሚያዘጋጃቸው ግዙፍ የጎልፍ ቱር ውድድሮች ጋርም ትልቅ ፉክክር ውስጥ ገብቷል። ላይቭ ጎልፍ (live Golf) ለተባለው አዲስ  ውድድር ሳዑዲ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓም ተነግሯል።

በአሜሪካ እና በበርካታ የአውሮፓ ሀገራት ተወዳጅ የሆነውን የክሪኬት ውድድር ሳዑዲ አረቢያ በሀገሯ ማዘጋጀት ከጀመረች ሰንበትበት ብላለች። ፈርጣማ የሀብት ክንዷን በመጠቀም ይህንን ውድድር ወደ ራሷ ማምጣቷን ነው የዘአትሌቲክ መረጃ የሚያመለክተው። በመረጃው መሰረት የሳዑዲው ግዙፉ የዘይት ኩባንያ አራምኮ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የዓለም አቀፉ ክሪኬት ስፖንሰር ሆኗል። ታላላቅ የክሪኬት ውድድሮችም በባህረ ሰላጤዋ ሀገር መደረግ ጀምሯል።

እ.አ.አ 2021 ሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፎርሙላ አንድ ውድድርን ያዘጋጀችበት ወቅት ነው። ይህንን የዓለም ሻምፒዮና ካዘጋጀች በኋላ ሌሎች የገልፉ ሀገራት ባህሬን፣ ኳታር እና አቡ ዳህቢን የመሳሰሉትም በስፖርቱ ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል።

የፎርሙላ አንድ ውድድርን በማዘጋጀት ለመካከለኛው ምሥራቅ ያስተዋወቀችው ሳዑዲ አረቢያ አሁን ደግሞ ሌላ የሞተር ስፖርት ውድድር ፎርሙላ ኢ (Formula e) የሚባል መድረክ ማስተናገድ ጀምራለች።

ከዚህ በተጨማሪ ታላላቅ የሜዳ ቴኒስ ውድድሮችም በሳዑዲ አረቢያ መደረግ ጀምረዋል። በተለይ የዓለም የሴቶች የቴኒስ ማህበር የሚያዘጋጀው ውድድር  በተዳጋጋሚ ተደርጓል። እንደ ዘ አትሌቲክ  መረጃ የ2024ቱ የሴቶች የቴኒስ የቱር ውድድር ፍፃሜም በቀጣይ የሚከናወን ይሆናል። ይህ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ታህሳስ ወር የዓለማችን ቁጥር አንዱን የኖቫክ ጆኮቪች እና የዓለም ቁጥር ሁለቱን የካርሎስ አልካሬዝን ፍልሚያ ታስተናግዳለች።

ሌላው ሳዑዲ ከምታስተናግዳቸው ውድድሮች መካከል ትግል (wrestling) ይገኝበታል። በ2014 እ.አ.አ ለመጀመሪያ ጊዜ አልጋ ወራሹ ሙሀመድ ቢን ሳልማን ሁነቱ በሀገራቸው እንዲዘጋጅ ማድረጋቸውን ታሪክ ያስታውሳል።

ከ2018 እ.አ.አ ጀምሮ ግን በብዙዎች የሚወደደውን ይህንን ስፖርት በቀጣይ 10 ዓመታትም በሀገራቸው እንዲደረግ መፈራረማቸውን መረጃዎች አመልክተዋል። ከእነዚህ ሰፖርቶች በተጨማሪ ሳዑዲ አረቢያ ኦሎምፒክን ለማስተናገድ ፍላጎት ያላት ሲሆን ሌሎች የአትሌቲከስ ወድድሮችን ግን በቋሚነት ለማዘጋጀት ከፕሬዝደንቱ ሰባሰቲያን ኮ ጋር ንግግር ጀምረዋል፡፡

ለዘገባችን ዘ አትሌቲክ እና ዘ ጋረዲያንን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here