የሴቶችን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ

0
81

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማሳደግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሴቶች እና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ለ49ኛ ጊዜ “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ በመግለጫቸው እንዳሉት የቀኑ መከበር የሴቶችን ሁለንተናዊ የትግል እንቅስቃሴ ውጤት ለመዘከር፣ብሎም ሰፋፊ ንቅናቄዎችን ለማድረግና ለማሕበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል።
መንግሥት የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም የአመራርና ውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን ለማሳደግ እየወሰደ ባለው ጠንካራ እርምጃ አበረታች ለውጦች መምጣታቸውንም ገልጸዋል።
የኢዜአ ዘገባ እንዳመላከተው የሴቶችን አደረጃጀት በማጠናከር ግንባር ቀደሞችን ከመፍጠር ጎን ለጎን የቁጠባ ባሕልን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ለሴቶች የብድር አገልግሎትን በማመቻቸት በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ መደረጉንም ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
ቀኑን በማስመልክት 45 ሺህ ሴቶች በቦንድ ግዢ እንዲሳተፉ በማድረግ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቂያ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዚህም 22 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።
ሴቶች በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሳትፏቸውን በማጠናከር በሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት ላይ ጉልህ ሚና ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንንም አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
ቀኑን በመላ ሀገሪቱ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፣ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2017 ደረስ በተለያዩ ዝግጅቶ እንደሚከበር ጠቁመዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here