የሴቶች ቀን ሲታወስ

0
145

ከዓለም ሕዝብ ግማሾች ሴቶች ናቸው። ሴት ሕይወት አስቀጣይ፣ ትውልድ አተካኪ፣ ምርጥ እናት፣ እህት ሚስት … ናት። ያለ ሴቶች ምድራችን ጎደሎ ናት ብንል ማጋነን አይሆንም። ሴት በታሪክ ውስጥ ብልህ የሀገር መሪ፣ ግንባር አያጥፌ የጦር አዝማች፣ ድንቅ ወታደር፣ ዲፕሎማት፣ ፖለቲከኛ እንዲሁም ተመራማሪ በመሆን የማይተካ ሚና ለዚህ ዓለም አበርክታለች። ይሁን እንጂ የባህል፣ የማህበረሰብ ስር የሰደደ ኋላቀርነት አስተሳሰብ ሴቶችን ያገለለ እና መብቶቻቸውን ያላከበረ አድሏዊ አመለካከት በመላው የዓለማችን ክፍል ሰለባዎች ሆነው ለረጅም ዘመናት ቆይተዋል፤ ታሪክ እንደሚያሳየው። ተሰሚነት ባያገኙም የእኩልነት መብታቸው እንዲከበር ባልተደራጀ መልኩ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ የሴት ሰራተኞች እንቅስቃሴዎችን ተከትሎ የዓለም የሴቶች ቀን በተለምዶ ማርች 8 የሚለው ዓለማቀፋዊ ዓመታዊ በዓል አድርጎ የማክበር እሳቤው የተጠነሰሰው።

በ1857 እ. ኤ. አ በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ ሴት የጋርመንት ሰራተኞች በአደባባይ ወጥተው በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ከባድ የስራ ጫና በመቃወም የተንቀሳቀሱበት ታሪካዊ ክስተት የትግል እርሾ ተደርጎ ይወሰዳል። ይህን የሴቶች የትግል ክስተት ለማስታወስ ታሳቢ ያደረገ የተባለለት የመጀመሪያው የሴቶች ቀን እ ኤ አ በ1909 የካቲት 28 ቀን ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ መከበሩን ታሪክ ያስታውሳል። ቴሬሳ ሜልኬል በተባለች የማህበረሰብ አንቂ አነሳሽነት የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ ያስተባበረው ዝግጅት ነበር።  በወቅቱ የሥራ ሰዓት መሻሻልን፣ የተሻለ ክፍያንና ሴቶች በምርጫ መሳተፍ አለባቸው የሚሉትና መሰል ሀሳቦችን በማንገብ ነበር የተቃውሞ ሰልፍ ያካሄዱት። ይህንን ተከትሎም እ. ኤ. አ የካቲት 28 ቀን 1909 ብሔራዊ የሴቶች ቀን እንዲኖር ተወስኗል።

እ.ኤ.አ ነሀሴ 1910 ኮፐንሀገን ከተደረገው ዓለማቀፍ ሶሺያሊስቶች ሁለተኛ አጠቃላይ ኮንፈረንስ ቀደም ብሎ የዓለም አቀፍ ሴት ሶሺያሊስቶች ኮንፈረንስ ተደርጎ ነበር። በተወሰነ ደረጃ በአሜሪካ ሶሻሊስቶች በመነሳሳት  ጀርመንን ወክለው የተገኙት ክላራ ዘትኪን፣ ካቴ ዱንከር፣ ፓውላ ታይዴ እና ሌሎችም ዓመታዊ የሴቶች ቀን እንዲወሰን ሀሳብ አቀረቡ። በተለይ  የሴቶች መብት ተሟጋቿ ክላራ ዜትኪን ቀኑ ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን ሀሳብ አመንጭታ ነበር።

አሜሪካውያን የየካቲት ወር የመጨረሻ ሳምንት እሁድን የሴቶች ቀን አድርገው ማክበርን ቀጠሉ። ሩሳዉያን በበኩላቸው የሴቶች ቀንን እ. ኤ  አ. በ1913 በየካቲት ወር የመጨረሻውን ቅዳሜ አክብረው ነበር። በ1914 ደግሞ ጀርመን የሴቶችን ቀን  ማርች ስምንት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ አክብሩት።

እ.ኤ.አ. በ1945 በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር በወንዶች እና በሴቶች መካከል የእኩልነት መርህን ለማረጋገጥ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ስምምነት ተደረገ። በፈረንጆቹ መጋቢት 8 ቀን1975 የሴቶች ቀን በተባበሩት መንግሥታት በይፋ ተከበረ።

ከሁለት ዓመታት በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ተወያይቶ ካሳለፈው ውሳኔ በኋላ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዓለም አቀፍ በዓል ሆኖ በአባል ሀገራቱ በየዓመቱ መጋቢት 8 እንዲከበር ተደርጓል። ከዚያ እለት ጀምሮም በየዓመቱ እየተከበረ ይገኛል።

የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት አካባቢ የሩሲያ ሴቶች “ዳቦና ሰላም” በሚል ሰልፍ አደረጉ። በወቅቱ የነበረው ንጉሣዊ ሥርዓት ስልጣን የለቀቀ ሲሆን ጊዜያዊ አስተዳዳሪውም ሴቶች በምርጫ እንዲሳተፉ  ፈቀደ።

ዕለቱ መከበር የጀመረው ከአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ በኋላ ቢሆንም ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና የለውም። በዓለም ላይ ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በ80 አገራት ይከበራል።

በሩሲያ ዕለቷ ሶስት አራት ቀናት ሲቀራት የአበቦች ሽያጭ በዕጥፍ ይጨምራል። በቻይና የሀገሪቷ ምክር ቤት በሰጠው ምክር መሰረት ሴቶች በዚያች ቀን ግማሽ ቀን ብቻ እንዲሰሩና ግማሽ ቀን እንዲያርፉ ቢደረግም በርካታ አሰሪዎች ይህንን ሁልጊዜም አይከተሉትም ተብሏል።

በጣልያን “ላ ፌስታ ዴላ ዶና” ተብላ የምትጠራው ይህች ዕለት ሚሞሳ ተብላ የምትጠራውን አበባ ስጦታ በመለዋወጥ ያከብሯታል። ይህ ባህል መነሻው ባይታወቅም ምናልባት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በሮም እንደተጀመረ ይታመናል።

በአሜሪካ ሙሉ የመጋቢት ወር “የሴቶች ታሪክ ወር” የሚል ዕውቅና ተሰጥቶታል። በሀገሪቱ መሪዎች ዘንድ ዕውቅና በተሰጣት በዚች ወርም የአሜሪካ ሴቶች አስተዋፅኦ ይዘከራል።

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ፣ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ከስርዓተ-ፆታ አድልዎ የፀዳ የተሻለ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚሉ ሀሳቦችን በማራመድ ይከበራል::

በተጨማሪም ሴቶችን ለማክበር፣ የሴቶች እኩል መብትን ለማረጋገጥ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ያለሙ መልዕክቶች ለማስተላለፍ የበዓሉ መከበር አስፈላጊ መሆኑም ይጠቀሳል።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ስጦታዎችን በመሰጣጣትና የተለያዩ ሥርዓቶችን በማካሄድ ይከበራል:: በሴት ደራሲያን የተፃፉ መጻሕፍትን ስጦታ በማበርከት፣ ስለ ሴቶች መብት እና የፆታ እኩልነት በማስተማር፣ የሚወዷቸውን በሴቶች የተደረሱ ፊልሞችን በመመልከት እና በሌሎችም ሴቶችን የሚያበረታቱ ተግባራት በመከወን ይከበራል።

ምንጭ ፦  ቢቢሲ፣ ሂስትሪ ዶት ኮም፣ ዋልታ እና ሌሎችን ተጠቅመናል።

(መሠረት ቸኮል)

በኲር የመጋቢት 1  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here