“የሴቶች እግር ኳስ በሀገራችን በሂደት እየተሻሻለ እና እያደገ ነው”

0
102

ተወልዳ ያደገችው በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ አራት በተለምዶ አየር ማረፊያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በእውቀት ፋና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች:: በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ ዲፕሎማዋን ሠርታለች:: የዚህ እትም እንግዳችን በተለያዩ ክለቦች የተጫወተችው እና በአሁኑ ሰዓት የባሕር ዳር ከነማ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ የሆነችው ሰርክአዲስ እውነቱ ናት:: መልካም ንባብ!

በእግር ኳሱ ዓለም በተለያዩ ክለቦች በተጫዋችነት እና በአሠልጣኝነት ቆይተሻል፤ ወደ እግር ኳሱ ዓለም እንዴት ልትገቢ ቻልሽ?

ተወልጄ ባደኩበት ባሕር ዳር ከተማ በሰፈሬ የቀድሞ የአውሮፕላን ማረፊያ የነበረ በተለምዶ አየር ሜዳ ተብሎ የሚጠራ ስፍራ አለ:: ሜዳው ከቤታችን ፊት ለፊት ነው ያለው:: ከቤት ስወጣም ይሁን ስገባ ልጆች እግር ኳስ እየተጫወቱ ነው የማያቸው:: ትልቅ ወንድሜም ከሚጫወቱት ልጆች መሃል ነበር:: እኔም ከወንዶች ጋር እግር ኳስ መጫወት ጀመርኩ:: አንድ ቀን የእግር ኳስ ፍቅሬን የሚያውቅ የሰፈሬ ሰው አንድ አሠልጣኝ ሴቶችን ሰብስቦ እያሰለጠነ እንደሆነ ነገረኝ:: ወደ አሰልጣኙ አምርቼ መሠልጠን ጀመርኩ፤ የእግር ኳስ ጉዞዬም በዚሁ ተጀመረ ማለት ነው::

እንደ አርአያ የምታነሻቸው ሰዎች አሉ?

በወቅቱ አርአያ ብዬ የማነሳቸው ከእኛ በእድሜ ከፍ የሚሉ ሴት ልጆችን ነው:: በኳሱ ለረጅም ጊዜ ባይቀጥሉም እነሱን እንደ አርአያ ቆጥሬ ነው ወደ እግር ኳሱ የገባሁት:: በውጪ ሀገር ደግሞ የብራዚሏ ማርታ አድናቂ ነበርኩ:: እንደሷ ውጤታማ መሆንም ነው የምፈልገው የነበረው::

ሴትነት እና እግር ኳስን እንዴት ትገልጭዋለሽ?

ሴትነት እና እግር ኳስ በእኛ የልጅነት ጊዜ አስቸጋሪ ነበር:: ሴት ልጅ ወደ ማጀት እንጂ አደባባይ ወጥታ እግር ኳስ መጫወት አትችልም ነበር:: ሴት ልጅ እግር ኳስ መጫወቷ እንደ ነውር ነበር የሚታየው:: አስቸጋሪ ነገሮች እና ፈተናዎችም ብዙ ናቸው:: ሴት ልጅ እግር ኳስ መጫወቷም የተለመደ አልነበረም:: በኋላ ላይ ልጅ ከወለድኩ በኋላ  ደግሞ ፈታኝ ነገሮች ነበሩት:: ለእግር ኳሱ ከፍተኛ ፍቅር እና የአይበገሬነት ስሜት ያላት ሴት ጫናውን መቋቋም እና በስፖርቱ መቀጠል ትችላለች::

ብዙ ጓደኞቼ ከቤተሰቦቻቸው ተደብቀው ነበር የእግር ኳስ ልምምድ እና ውድድር የሚያደርጉት፤ እኔ ግን እንደ እድል ሆኖ በቤተሰቦቼ ይሄን መሰል ጫና አልነበረብኝም፤ ይህ ሁኔታ ነገሮች ከሌሎች ጓደኞቼ አንጻር ቀላል እንዲሆንልኝ ረድቶኛል፤ በስፖርቱ ልቀጥል የቻልኩትም ካለኝ ፍቅር ባሻገር ቤተሰቦቼ ከተቃውሞ በተቃራኒ በነበራቸው ድጋፍ ነው እላለሁ:: ብዙ ጓደኞቼ እግር ኳሱን አቁመው በሌላ የሕይወት መስመር ውስጥ ገብተዋል::

ትዳር መሥርቼ እርጉዝ በነበርኩበት ሰዓት ትንሽ ከበድ ያለ ነገር ነበር:: በእርግዝና ምክንያት ከአሠልጣኝነቱ ላለመውጣት እና ከስፖርቱም ላለመራቅ ትግል ይጠይቅ ነበር:: እንደምንም ፈተናውን አልፌ በስፖርቱ ቀጥያለሁ::

አሁን ላይ ላሉ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ከበፊቱ አንጻር ቀለል ያለ ሁኔታ ነው ያለው:: ቤተሰብም እግር ኳስ መጫወታቸውን አምኖ ድጋፍ ያደርጋል:: በተለያዩ መንገዶች ይደግፋቸዋል:: በብሔራዊ ሊግ እና በከፍተኛ ሊግ ውድድሮች መኖራቸውም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው:: በክለቦችም ደረጃ ያለው አያያዝ በጣም ጥሩ ነው፤ ከአመጋገብ ጀምሮ እስከ ስልጠና ድረስ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶታል ማለት ይቻላል::

በተጫዋችነት እና በአሠልጣኝት የቆየሽባቸውን ክለቦች እስኪ ንገሪን?

ተጫውቼ ያደኩት እና ብዙ ጊዜ ያገለገልኩት በባሕር ዳር ልዩ ዞን ነው:: የአማራ ክልል ምርጥ ውስጥ በመመረጥም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ላይ በተደረጉ ውድድሮች ተሳትፌያለሁ:: በማሰልጠኑ ዘረፍ ደግሞ የአማራ ልዩ ዞንን እና የአማራ ክልል ምርጥን ለረጅም ዓመታት አሠልጥኛለሁ:: በክለብ ደረጃ ደግሞ ዳሽን ቢራን፣ ጥረት ኮርፖሬሽንን አሠልጥኛለሁ:: በዚህ መካከል ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ ከ17 እና 20 ዓመት በታች ያሉ ልጆችን እንዲሁም የብሔራዊ ቡድኑ ምክትል አሠልጣኝ ሆኜ ሀገሬን አገልግያለሁ:: ከ2012 ዓ.ም እስከ አሁን ድረስ ደግሞ የባሕር ዳር ከነማ የሴቶች እግር ኳስ ክለብን እያሠለጠንኩ እገኛለሁ::

ከተጫዋችነት ጀምሮ አሁን እሳከለሁበት አሠልጣኝነት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ፤ ዝም ብሎ በቀላሉ የደረስኩበት እና ያለፍኩበት አይደለም:: ከግል ተፈጥሯዊ ነገር ጀምሮ እስከ ቤተሰብ ጉዳይ ድረስ ብዙ ፈተናዎችን ያለመታከት አልፌያለሁ:: ፈተናዎችን ሰብሮ እና አልፎ ውጤታማ ሆኖ መገኘት ቁልፍ ጉዳይ ነው:: ሴት ልጅ ትችላለች ከወንድ ልጅ እኩል ናት የሚለው መርህ መምጣቱም ከእኔ ተስፋ አለመቁረጥ ጋር ተዳምሮ አግዞኛል ብዬ አስባለሁ::

በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ያለበትን ደረጃ እንዴት ትገመግሚዋለሽ?

የሴቶች እግር ኳስ በሀገራችን በሂደት እየተሻሻለ እና እያደገ ነው:: ቀደም ባሉ ጊዜያት የሴቶች ክለቦች አልነበሩም:: አሁን ላይ 14 የሴቶች እግር ኳስ ክለቦች አሉ:: በእነዚህ ክለቦች ውስጥ ከተጫዋቾቹ ባሻገር አሠልጣኞች፣ የህክምና ባለሙያዎች፣ አጋዥ አሠልጣኞች፣ እና ሌሎች የቡድኖቹ አባላት ይካተታሉ:: ይህ ከስፖርቱ እድገት በሻገር ለሴቶች የሥራ እድል ከመፍጠር ጋርም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፤ ምክንያቱም ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ እና ከጥገኝነት እንዲወጡ ያስችላልና::

በውድድሮች ደረጃም ታችኛው ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ እና የውስጥ ሊግ የተባሉ ውድድሮች ይካሄዳሉ:: ይህም የስፖርቱን እድገት አመላካች ነው:: እንደ ሀገር ብሔራዊ ቡድናችንም በተለይ በፊት ከነበረው አንጻር የተሻለ ውጤት የሚያመጣበት ሁኔታ ነው ያለው::

ሴቶች የእግር ኳስ ተጫዋቾቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሀገር ወጥተው እየተጫወቱ ነው:: ለአብነት እነ ሎዛ አበራ፣ አረጋሽ ካሳ እና ሌሎች በውጪ ሀገራት ክለቦች እየተጫወቱ መገኘቱ ለስፖርቱ እድገት አመላካች ነው::

ከወንድ እግር ኳስ ተጫዋቾች አንጻር ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች በቂ ክፍያ የላቸውም ተብሎ ይነሳል፤ ስለዚህ ምን ትያለሽ?

እውነት ነው ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ከወንዶቹ እኩል አይከፈላቸውም፤ አሠልጣኞችም እንደዚሁ:: ቀደም ባሉት ጊዜያት ሴቶች በጣም የወረደ ክፍያ ነበር የሚከፈላቸው:: ያም ሆኖ አሁን ላይ የተሻለ ነገር አለ:: እንደየ ክለቡ አቅም እና ገቢ ከቀድሞው የተሻለ ይከፈላል:: በጣም አደገ ባይባልም መስተካከል የሚያስፈልገው ሆኖ መሻሻሎች መኖራቸው ግን አይካድም::

የምታሰለጥኝበት መንገድ እና የምትከተይው ስልትስ ምን ይመስላል?

እኔ የማሠለጥንበት መንገድ እና ስልት ተጫዋቾች አጫጭር የኳስ ቅብብሎሾችን መሥርተው ወደ ተጋጣሚ ቡድን በማምራት ውጤት ማምጣት ነው:: ኳስ ይዞ መጫወት እንደ ስልት እየተጠቀምኩ እስከ አሁን የመጣሁበት ነው:: ታዳጊ ልጆችን በማብቃት እና በእነሱ ላይ እምነት ጥሎ መሥራት እንደ ጽንሰ ሀሳብ የያዝኩት ነው:: በዚህ መንገድ ውጤታማ ሆኜበታለሁ ብየም አስባለሁ:: በዚህ መንገድ ከ17 ዓመት በታች እና ለብሔራዊ ቡድኑ ብዙ ልጆችን አስመርጫለሁ::

ለሴቶች የምታስተላልፊው ምልዕክት ካለ?

ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት እኛ ሴቶች ከወንዶች እኩል በተሰማራንበት መስክ ውጤታማ መሆን እንደምንችል ነው:: ጊዜው ሴት ወንድ የሚባል ልዩነት የማያስፈልግበት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል:: እኔ ሁለት ልጆቼን አርግዤ በነበሩት ጊዜያት እንኳ ማሠልጠኔን አላቋረጥኩም ነበር:: ምክንያቱም እችላለሁ የሚለው መንፈስ ውስጤ ስላለ ነው:: እችላለሁ  የሚለውን መርህ ሴቶች እንደ ሕይወት መመሪያ ሊያደርጉት ይገባል:: ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የመጋቢት 1  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here