የስኬት ቁልፎች

0
135

“አልችለውም! የሚባል ቃል በውስጣችን ካለ መቼም ቢሆን አንችለውም፤ ስኬትንም ያጠፋል። በመሆኑም ይህን አስተሳሰብ እጥራለሁ! አደርገዋለሁ! በሚል አዎንታዊ ቃል መቀየር ስኬትን ያቀርባል::” ይህ አባባል የዕውቋ የሥነ ልቦና ምሁር እና ማይንድ ሴት – ዘ ኒው ሳይኮሎጂ ኦፍ ሰክሰስ (Mindset:The New Psychology of Success) የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ካሮል ድዌክ (Carol S. Dweck) ነው። የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ዕድገት ተኮር አስተሳሰብን (Growth Mindset) በተመለከተም ሰፊ ጥናት አድርጋለች።

ስኬትን መነሻ በማድረግ ስለሥነ ልቦና ዝግጅት ማንሳታችን ወቅቱ የአንደኛው ወሰነ ትምሕርት ማጠቃለያ ፈተና ለመስጠት ትምሕርት ቤቶች በዝግጅት ላይ ናቸውና ነው፤ እኛም በፈተና ወቅት የተማሪዎች ዝግጅት ምን መሆን እንዳለበት የተለያዩ ጥናቶችን ልናጋራችሁ  ወደናል።

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ካሮል ድዌክ የጥናት ውጤቱን መነሻ አድርጋ እንዳስነበበችው የማሰብ ችሎታ በትጋት የሚያድግ፣ በተለይ ደግሞ ተማሪዎች ላይ ፍርሃትን በማስወገድ ለፈተና ጠንካራ ዝግጅት እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል።

ሳይኮሎጂ ቱዴይ (www.psychologytoday.edu) እንዳስነበበው ደግሞ የፈተና ቀላልም ከባድም የለውም። ፈተና የሚለው ቃሉ በራሱ ሰዎችን በተለይ የተማሪዎችን ሥነ ልቦና ጫና ላይ ይጥላል። ይሁን እንጂ በቀላሉ ከጫናው መውጣትም ይቻላል።

ከድረ ገጹ ያገኘነው     መረጃ እንደሚያመለክተው ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ዋና ባለቤቶቹ ራሳቸው ተማሪዎቹ   ናቸው። ወላጆችን እና                     አስተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻዎችም ለተማሪዎች ውጤት ማማር ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው።

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ካሮል ድዌክ እንደምትመክረው ፈተና የዕውቀት እንጂ የማንነት መለኪያ አለመሆኑን መረዳት ለተረጋጋ አዕምሮ ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ አዎንታዊ አስተሳሰብን ማዳበር ይገባል። “አልችልም!” የሚለውን ስሜት “ውጤታማም እሆናለሁ!” በሚል አዎንታዊ ንግግር መተካት ይገባል ትላለች።

ሌላው መሠረታዊ ነገር የሥነ ልቦና ዝግጅት ነው። ለዚህ ደግሞ ጭንቀትን መቆጣጠር ቁልፉ ጉዳይ ነው። የጭንቀት ስሜት ሲመጣ ጥልቅ ትንፋሽ መውሰድ (Deep Breathing) እና አጭር የእግር ጉዞ ማድረግ አዕምሮን ያድሳል።

ከዚህ በተጨማሪም ለጥናት  የጊዜ ሰሌዳ ማውጣት እና ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል። ሁሉንም የትምህርት አይነቶች በፍትሐዊነት የሚያካፍል የጥናት መርሀ ግብር (ፕሮግራም) ማዘጋጀት፣   ዝም   ብሎ በማንበብ ፋንታ ራስን በራስ መፈተን እና ነጥቦችን በቀላሉ መረዳት በሚያስችሉ ቃላት መጻፍ  ለስኬት ያበቃሉ።

በተማሪዎች የፈተና ወቅት ዝግጅት ዙሪያ ጥናት ያደረገው ሌላው የሥነ ልቦና ምሁር ካል ኒውፖርት (Cal Newport) ነው። ሀው ቱ ቢካም ኤ ስትሬት ኤ ስቱደንት (How to Become a Straight-A Student) በሚል መጽሐፉ ጥልቅ ትኩረት ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ያስችላል ይላል። ምክንያም ጥልቅ ትኩረት ካለ መረበሽን እና መጨነቅን ያስቀራል፤ ከዚህ በተቃራኒው ሐሳብን በመሰብሰብ በሙሉ ትኩረት እንዲያነብ ያደርጋል:: ይህም የተሸለ ውጤት ለማስመዝገብ ያስችላል::

እንደ ካል ኒውፖርት በቂ እንቅልፍ አለማግኘት ትኩረትን ያሳጣል። በቂ እንቅልፍ ማግኘት ደግሞ የተማሪዎችን ውጤት ከ20 እስከ 40 በመቶ ሊያሻሽል ይችላል። እንቅልፍ የተጠናውን መረጃ ከአጭር ጊዜ ትውስታ ወደ ረጅም ጊዜ ትውስታ (Long-term memory) ለማሸጋገርም ወሳኝ ነው። በመሆኑም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቂ እንቅልፍ ማግኘት አስፈላጊ ነው ይላል።

ትኩረትን የሚከፋፍሉ ተግባራት ለምሳሌ ማህበራዊ ሚዲያ መጠቀምን በፈተና ወቅት መገደብ እንደሚገባ ምሁሩ ይመክራሉ። የወላጆች እና የአስተማሪዎች ድጋፍ ደግሞ ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው። እነዚህን ባለድርሻዎች “ለተማሪዎች ውጤታማነት የጀርባ አጥንት” ሲል ነው ምሁሩ የሚገልጻቸው። መረጋጋትን መፍጠር፣ ከመጠን ያለፈ ጫና አለማሳደር እና ማበረታታት የእነዚህ ባለድርሻዎች ዋና ኃላፊነት ነው። ተማሪዎች በራስ መተማመናቸው እንዲጎለብትም        አዎንታዊ ቃላትን በመጠቀም ማበረታታት ይገባል።

ፈተና የተማሪ ዕውቀትን፣ ችሎታን እና ተግባራዊ አቅምን ለመመዘን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሣሪያ ነው። ነገር ግን ፈተና ተማሪውን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ አይደለም፤ የወላጆች፣ የመምህራን እና የትምህርት ቤት ትብብር ውጤት ነው፤ ሦስቱ አካላት በመተባበር ሲሠሩ ተማሪዎች በሥነ ልቦና፣ በትምሕርት እና በባሕርይ ይጠናከራሉ።

በወላጆች፣ በትምሕርት ቤት እና በማሕበረሰብ መካከል ስላለው ትብብር (School-Family-Community Partnerships) ጥናት ያደረጉ ፕሮፌሰር ጆይስ ኤፕስታይን (Joyce Epstein) እነዚህ ባለድርሻዎች ለተማሪዎች ስኬት ያላቸውን ወሳኝ ሚና በዝርዝር አስቀምጠዋል።

ወላጆች በፈተና ወቅት ለልጆቻቸው የሥነ ልቦና ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ ነው። ተማሪዎች ብዙ ጊዜ ጫና ይሰማቸዋል፤ ይህም ፍርሀትን እና ጭንቀትን ሊፈጥር ይችላል። በዚህ ወቅት ወላጆች ልጆቻቸውን በማበረታታት፣ “ትችላለህ! ትችያለሽ!” በማለት ኃይል መስጠት ይገባቸዋል።

በተጨማሪም ልጆቻቸው የሚያነቡበትን ሰዓት መደበኛ ማድረግ፣ ጸጥታ ያለው የመማሪያ አካባቢ ማዘጋጀት እና የእንቅልፍ ሰዓታቸውን መከታተል ከወላጆች ከሚጠበቁ ቁልፍ ተግባራት መካከል ናቸው:: ለተማሪዎች ውጤት መሻሻልም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ወላጆች ከመምህራን ጋር በመግባባት ልጆቻቸውን መከታተል ይገባቸዋል። የልጅን ድክመት ወይም ችግር ተገንዝቦ እንዲፈታ መርዳትም ይገባል።

ተማሪዎችን ለፈተና በትምሕርት እና በሥነ ልቦና ማዘጋጀት ደግሞ ከመምህራን ይጠበቃል:: ከፈተና በፊት የተማሪዎችን የመማሪያ ክህሎት በመገምገም የተለያዩ የጥናት መንገዶችን ማመላከትም ይገባቸዋል። ለምሳሌ በአጠቃላይ ግምገማ ፈተናዎችን፣ የልምምድ ጥያቄዎችን እና ሌሎች ጥያቄዎችን በቡድን   እንዲሠሩ ማድረግ ተማሪዎችን በተግባር ያጠናክራሉ።

በተጨማሪም መምህራን ተማሪዎች ላይ አላስፈላጊ ጫና ማሳደር አይገባቸውም፤ ለምሳሌ ስለ ፈተና እና  አጠቃላይ ስለ ትምሕርት ክብደት ሳይሆን ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ማንበብ ለተሻለ ውጤት እንደሚያበቃቸው እና በተስፋ እንዲመለከቱ ይመራሉ። እያንዳንዱ ተማሪ የተለየ አቅም እንዳለው በመገንዘብ ማበረታታትም ይገባል።

ትምህርት ቤት ለፈተና የሚያስፈልገውን አጠቃላይ አካባቢ ያዘጋጃል። የፈተና መርሃ ግብር በግልጽነት ለወላጆችና ለተማሪዎች መነገር፣ የፈተና ሕጎች እና ሥርዓቶች መገለጽ አስፈላጊ ነው።  ይህ ሲሆን ተማሪዎች በሰላም እንዲፈተኑ ያግዛል።

 

መረጃ

 

የፈተና ወቅት ዝግጅት

የጊዜ ሰሌዳ ማውጣት።

ንቁ ተሳትፎ ማድረግ፤ ዝም ብሎ በማንበብ ፋንታ ራስን በራስ መፈተን።

ጤናማ እንቅልፍ እና አመጋገብ።

የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ (Psychological Readiness)

አዎንታዊ አስተሳሰብን ማዳበር (አልችልም የሚለውን ስሜት ማስወገድ)።

ጭንቀትን መቆጣጠር፦ ጭንቀት ሲሰማ ጥልቅ ትንፋሽ መውሰድ እና የእግር ጉዞ ማድረግ።

ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮችን (ማሕበራዊ ሚዲያ) ማስወገድ።

መረጋጋት።

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የጥር 11  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here