ልዩ የሆነ የድምፅ እና የሙዚቃ ስልቱ በብዙ አርቲስቶች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ጀምስ ሁከት በበዛበት የግል ሕይወቱ፣ በማህበራዊ እንቅስቃሴው እና በዜማ ስራዎቹ ይታወቃል:: አሜሪካ ቤቴ ናት፣ ጥቁር እና ኩሩ ነኝ በሚሉ ዘፈኖቹ በጥቁሮች ላይ የሚደርሱ የዘር መድልዖዎችን ተቃውሟል::
እ.አ.አ በ1933 በደቡብ አሜሪካ ገጠር ውስጥ ተወልዶ፤ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ አድጓል። ያገኘውን ማንኛውንም አይነት ስራ በመስራት የኢኮኖሚ ጥያቄውን ለማሸነፍ ሞክሯል:: ለወታደሮች ይጨፍር፣ ጥጥ ይለቅም፣ መኪና ያጥብ እና ጫማ ይጠርግ ነበር።
ብራውን በኋላ ላይ የልጅነት ድህነቱን እንዲህ ሲል አስታውሷል “በሶስት ሳንቲም ጫማ መጥረግ ጀመርኩ፣ ከዚያም ወደ አምስት ሳንቲም፣ ቀጥሎም ወደ ስድስት ሳንቲም ከፍ አለ። አስር ሳንቲም ደርሼ አላውቅም። እውነተኛ ሱሪ ያገኘሁት በዘጠኝ ዓመቴ ነበር:: ግን እንደሚሳካልኝ አውቅ ነበር” ሲል ተናግሯል::
በ12 ዓመቱ በቂ ልብስ ባለማግኘቱ ከትምህርት ቤት ተባሯል። ይህን አስከፊ እውነታ ለማምለጥ ጀምስ ወደ ሃይማኖት እና ሙዚቃ ዞረ። በቤተክርስቲያን መዘምራን ውስጥ ዘመረ:: እዚያም ኃይለኛ እና ልዩ የሆነ ስሜታዊ ድምፁን አዳበረ።
በ16 ዓመቱ መኪና በመስረቁ ታሰረ። የሶስት ዓመታት እስራት ተፈረደበት። በእስር ላይ እያለ ብራውን የእስር ቤት የወንጌል መዘምራንን አደራጅቶ መርቷል። ጀምስ በእስር ቤት ውስጥ ከታዋቂው አር ኤንድ ቢ ዘፋኝ እና ፒያኖ ተጫዋች ከቦቢ ባይርድ ጋር ተገናኘ:: ይህ ጓደኝነታቸው እና የሙዚቃ አጋርነታቸው በሙዚቃ ታሪክ ውስጥ በጣም ፍሬያማ እንዲሆን አስችሎታል::
በ1955 ዘጎስፔል ስታር ላይተርስ ባንድን ተቀላቅሎ በአስደናቂ ችሎታው እና በትዕይንት አቀራረቡ ቡድኑን በፍጥነት ተቆጣጠረው።
እ.አ.አ በ1956 ፌመስ ፍሌምስ ባንድ ፕሊስ ፕሊስ የተሰኘውን ዘፈን ተቀርጾ ለሕዝብ አደረሰ:: ስሜታዊ እና ልብ የሚነካው ዜማ ብዙዎችን አስደነቀ:: ይህ ዘፈን በአር ኤንድ ቢ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ ምርጥ 6 ዝርዝር ውስጥ ገባለት::
ቦቢ በርድ የተባለው ጓደኛው ሲናገር “የጀምስ በኋላ ላይ ያያችሁት ዳንስ በዚያን ጊዜ ከሚያደርገው ጋር ሲነፃፀር ምንም አይደለም። ጄምስ በቆመበት ቦታ ተገልብጦ እግሩን መዘርጋት ይችል ነበር። እንደ ጂምናስቲክም ደጋግሞ ይገለባበጥ ነበር። ‘ምን ነክቶሃል? ለመቅዳት ጊዜው ሲደርስ እኮ ራስህን ገድለህ ትገኛለህ’ እንለው ነበር።” ሲል የጀምስ ብራውን አቅምን ይመሰክራል።
ሊትል ሪቻርድ በሚያቀርበው የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ጀምስ ብራውን በመድረኩ ስራውን ካቀረበ በኋላ ነበር ነገሮች በፍጥነት የተለወጡት። ሊትል ሪቻርድ ሴቶችን ያሳብዳቸው እና ያስጮሃቸው ነበር። ተደጋጋሚ ሊትል ሪቻርድ ይዝፈን ይባል ነበር። በዚህ የተበሳጨው ጀምስ ራሱን ለማስበለጥ ተዘጋጀ። እ.አ.አ በ1955 ሪቻርድ በ”ቱቲ ፍሩቲ” ዝነኛ ሆኖ መድረክ ላይ ወጣ። ጄምስ ብራውን ዕድሉን ተመለከተ።
የጀምስ ስሜት ማሸነፍ ላይ አተኩሯል። “በህይወቴ እንደዚህ ጠንክሮ የሚሰራ ሰው አይቼ አላውቅም፤ ከተለማመድነው ነገር በላይ ወደ ሌላ ነገር ይገባል። እሱን መከተል ከባድ ነበር። ሁልጊዜም ይገፋፋል፣ ይገፋፋል፣ ይገፋፋል” በማለት ጓደኛው በርድ ያስታውሳል።
አሁንም ይቀጥላል “በእርግጥ መጮህ የጀመረው እና እስከሚፈነዳ ድረስ መደነስ የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር። እሱ ሪቻርድን መብለጥ ነበረበት። አድናቂዎች መጀመሪያ ላይ ‘ሪቻርድን እንፈልጋለን!’ እያሉ ይጮሁ ነበር። በመጨረሻ ግን ሁልጊዜም ለጄምስ ብራውን ይጮሁ ነበር” ሲል።
ጀምስ ብራውን ከዚህ በኋላ የሚያዝ ሰው አልነበረም። አዘፋፈኑ፣ ዳንሱ፣ አለባበሱ፣ እንቅስቃሴው፣ መድረክ አያያዙ ሁሉ የሚያስደንቅ ሆነ።
እ.አ.አ በ1958 ወደ ኒውዮርክ ተዛውሮ ትራይ ሚ የተሰኘውን ዘፈን ለቀቀ። ዘፈኑ በአር ኤንድ ቢ የሙዚቃ ሰንጠረዥ 1ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የጀምስን የሙዚቃ ዝና አስጀመረለት። ብዙም ሳይቆይ ሎስት ሰም ዋን፣ ናይት ትሬን፣ እና ፕሪዝነርስ ኦፍ ላቭ የተሰኙ ተወዳጅ ዘፈኖችን አስከተለ:: በተለይ ፕሪዝነርስ ኦፍ ላቭ በፖፕ የሙዚቃ ዘርፍ 10ኛ ደረጃ ውስጥ ገባ። በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በሳምንት አምስት ወይም ስድስት ምሽቶች ትርኢት ያቀርብ ነበር::
በጥቅምት ወር 1962 በሃርለም በሚገኘው የአፖሎ ቲያትር የቀጥታ ኮንሰርት አልበም ቀረጸ:: ላይቭ አት ዘ አፖሎ በሚል መድረክ ላይ በቀጥታ የተቀዳው አልበም ጀምስን ታላቅ የንግድ ስኬት አረጋገጠለት:: በፖፕ አልበሞች ሰንጠረዥ ላይ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠ::
ጀምስ ብራውን በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ብዙዎቹን ተወዳጅ እና ዘመን አይሽሬ ነጠላ ዜማዎቹን ቀርጿል:: ከእነዚህም መካከል አይ ፊል ጉድ፣ ፓፓ ጎት ብራንድ በራንድ ኒው ባግ፣ ኢት ኢዝ ማንስ ወርልድ የሚሉት ይጠቀሱለታል::
እ.አ.አ በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ብራውን ለማህበራዊ ጉዳዮችም የበለጠ ጉልበት መስጠት የጀመረበት ጊዜ ነው። በ1966 ዱ ኖት ቢ ኤ ድሮፕ አውት የተሰኘውን ዘፈን አወጣ:: ይህም ዘፈን ለጥቁር ማህበረሰብ ትምህርት ላይ የበለጠ ትኩረት እንዲያደርግ የሚያሳስብ ቁጭት ያለበት እና ስሜታዊ ጥሪ ነበር። በሰላማዊ ሰልፍ ብቻ አጥብቆ የሚያምን ሰው ነበር:: ታሪኩን ያሰፈረው ባዮግራፊ ገጽ “ለማንም ሰው ጠመንጃ እንዲያነሳ አልነግረውም” ብሎ መናገሩን ጽፏል::
በፈረንጆች አቆጣጠር ሚያዝያ 5 ቀን 1968 ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር የተገደለበት ቀን ነበር:: በማግስቱ በመላ ሀገሪቱ ሁከት እየተቀጣጠለ ነበር:: ጀምስ በቦስተን ሁከትን ለመከላከል ሲል ያልተለመደ የቀጥታ የቴሌቪዥን ኮንሰርት አቀረበ። ኮንሰርቱን ያዘጋጀውም ሁከት እና ግርግርን ለመቀነስ ነበር ይባላል:: ይህ ጥረቱ ተሳክቶ ወጣት የቦስተን ነዋሪዎች ኮንሰርቱን በቴሌቪዥን ለመመልከት ቤታቸው ተቀመጡ:: በወቅቱ ከተማዋ ከሁከት ተርፋለች። ከጥቂት ወራት በኋላ ጀምስ ሰይ ኢት ላውድ እና አይ አም ብላክ ኤንድ ፕራውድ የተሰኙትን የትግል ዘፈኖች ሰራ:: እነዚህ ዘፈኖች በተለይ ጥቁር ትውልዶችን አንድ ያደረጉ እና ያነሳሱ ሆነው ይጠቀሳሉ።
እ.አ.አ በ1970ዎቹ ጀምስ በርካታ ተወዳጅ ዘፈኖችን ሰርቷል:: ሴክስ ማሽን እና ጌት አፕ ኦፍ ዛት ቲንግ የሚሉት ይጠቀሱለታል:: በ1970ዎቹ መጨረሻ ላይ በገንዘብ ችግር ምክንያት ሥራው ቀንሷል:: ጀምስ በ1985 ያወጣው ሊቪንግ ኢን አሜሪካ የተሰኘው ዘፈኑ የአስር ዓመታት ውስጥ ትልቁ ስኬቱ ነበር። በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ጀምስ ቀስ በቀስ ወደ ዕፅ ሱሰኝነት እና ድብርት ውስጥ ገባ። ፖሊስ ላይ በመተኮሱ በ1991 በይቅርታ ከመለቀቁ በፊት 15 ወራት በእስር አሳልፏል።
ከእስር ቤት የወጣው ጀምስ ወደ ኮንሰርት ስራው ተመለሰ። ምንም እንኳን ከቀድሞው በጣም የቀነሰ ቢሆንም አነቃቂ እና ጉልበት የተሞሉ ኮንሰርቶችን ያቀርብ ነበር። በፈንጆች አቆጣጠር በ1998 ጠመንጃ በመተኮስ እና ፖሊስን በማሳደድ ሌላ ግጭት ውስጥ ገባ:: ከዚህ ክስተት በኋላ ለ ዘጠና ቀናት የዕፅ ማገገሚያ ማዕከል እንዲገባ ተፈረደበት።
ብራውን በሕይወቱ አራት ጊዜ አግብቶ ስድስት ልጆች ወልዷል። በ2004 ብራውን በሚስቱ ቶሚ ራኢ ሃይኒ ላይ በፈጸመው የቤት ውስጥ ጥቃት ክስ እንደገና ታሰረ:: በወቅቱ “ሚስቴን በጭራሽ አልጎዳም። በጣም እወዳታለሁ” ብሎ ነበር:: ጀምስ ብራውን እ.አ.አ በታህሳስ 25 ቀን 2006 በሳንባ ምች ታሞ ከአንድ ሳምንት በኋላ በ73 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል::
ጀምስ ብራውን “ሁልጊዜ እንደምለው፣ ሰዎች እኔ ማን እንደሆንሁ ማወቅ ከፈለጉ ማድረግ ያለባቸው ሙዚቃዬን ማዳመጥ ብቻ ነው” ሲል ተናግሯል:: ለ50 ዓመት በጣም ተጽዕኖ ፈጣሪ የሙዚቃ ሰው ሆኖ ኖሯል:: የሶል ሙዚቃ አባት፣ የፈንክ ፈጣሪ፣ የሂፕ-ሆፕ አያት ተብሎ ይጠራል:: ሚክ ጃገር፣ ማይክል ጃክሰን፣ አፍሪካ ባምባታ፣ ጄይ ዚ፣ ዴቪድ ቦዊ፣ ብሩኖ ማርስ እና ሌሎች አርቲስቶች ላይ ተጽእኖውን አሳርፏል::
ትሪትል ማን ገጽ የጄምስ ብራውንን አልበሞችን በሚመለከት ሲጽፍ በትንሹ 58 አልበሞችን አውጥቷል ይላል:: አራት የገና አልበሞችንም ሰርቷል ይላል:: ላይቭ አት አፖሎ፣ ላይቭ አት አፖሎ 11 እና ሴክስ ማሽን የተሰኙ ሦስት በቀጥታ ስርጭት የተቀረጹ አልበሞች የጀምስ ብራውንን አቅም የሚያሳዩ ነበሩ ይላል:: ጀምስ በ1992 የግራሚ የህይወት ዘመን ስኬት ሽልማት አሸንፏል።
ማረፊያ
እስከዚህም ፍቅርሽ
እስከዚህም ፍቅርሽ:
ከሰንደል ጭስ በላይ:
ደምቆ የማይገዝፈው:
ምንሽን ልፃፈው ?
እስከዚህም ፍቅርሽ
በጧት የረገፈው:
ከዕድሜ እሬሳ ውጭ
ዋኝታ ምኑን ታውጣው
ነብሴ ከባለፈው ?
እስከዚህም ፍቅርሽ:
ዘመን ያሳረጠው:
ምኑን አስታውሼ
ሣጌን እየማኩኝ :
እንባዬን ልዋጠው ?
እስከዚህም ፍቅርሽ
ሲነድፍ ያለሰንኮፍ:
መታሁ ቢልም ለኮፍ:
እንኳንና ሰምበር
ስምሽስ ማን ነበር ?
ገጣሚ ኑረዲን ኢሳ
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም